December 11, 2023 – Konjit Sitotaw 

” በሕግ መጠየቅ ምን ችግር አለው፤ ነገር ግን ሕግ የታለና በሕግ ይጠይቁኛል። ከጠየቁኝ ደግሞ ዝግጁ ነኝ ” – አቶ ታዬ ደንደአ

አቶ ታዬ ደንደአ ከሰላም ሚኒስትር ዴኤታነት መነሳታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ከደረሳቸው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጠንካራ ትችት ከሰነዘሩ በኃላ ማምሻውን ለ ” ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ” ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።

አቶ ታዬ ደንደአ በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከሥልጣን የተሰናበቱት በአገሪቱ ያለው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ በማቅረባቸው እንጂ ሌላ ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል።

” ስለእርቅ ስለተናገርኩ ጦርነት ይቁም ስላልኩ እንጂ ሌላ ምክንያት የለም ” ያሉት አቶ ታዬ፣ ” በጦርነቱ ጊዜ ጦርነቱን ስደግፍ፣ ሲያበረታቱኝ ነበር። ሕዝቡ ይታረቅ ስንል ነው ያመማቸው። ጠርተው አላናገሩኝም። በአካል አልተገናኘንም ” ሲሉ ተናግረዋል።

ስንብታቸውን በተመለከተ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ያሰፈሩትን ጠንካራ ቃላትን የተጠቀሙት ትችትን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ታዬ ደንደአ ፤ ” ይሄ እውነት ነው። ለሰው አያዝኑም። የሰው ልጅ ሞቶ አውሬ እየበላው ስለ ፓርክ ያወራሉ። ሰው የሚበላው አጥቶ እየሞተ በብዙ ገንዘብ ቤተ መንግሥት ያስገነባሉ ” በማለት ወቅሰዋል።

በማህበራዊ ገፃቸው በፃፉት ትችት በሕግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ነገር ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ታዬ ለዚህ ዝግጁ መሆናቸውን ፤ ነገር ግን ይህ የሚሆንበት ዕድል እንደሌለ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

” በሕግ መጠየቅ ምን ችግር አለው ታዲያ። ነገር ግን ሕግ የታለና በሕግ ይጠይቁኛል። ከጠየቁኝ ደግሞ ዝግጁ ነኝ። ” ብለዋል። አቶ ታዬ በሕግ የሚያስጠይቃቸው ጉዳይ ይኖር ይሆን ?

የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆነው በጠንካራ ትችታቸው የሚታወቁት አቶ ታዬ ሰሞኑን በተከታታይ የሰነዘሯቸው አስተያያቶች ለስንብታቸው ምክንያት ይሆናል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ፤ ” ከዚህ ጋር የሚገናኝ አይመስለኝም። ከፓርቲያችን መርሆች ውስጥ ነጻነት አንዱ ነው። ከዚህ መርህ በተቃራኒ መቆም ተገቢ አይደለም። እኔ ስናገር የነበረው ይህንን መርህ መሠረት በማድረግ ነው ” ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ሆነ ሰላም ሚኒስቴር እስካሁን ስለጉዳዩ ያሉት ነገር የለም። ነገር ግን አቶ ታዬ ከስልጣን መሰናበታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

መረጃውን ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ነው የተገኘ ነው ።