
12 ታህሳስ 2023
የቱርክ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰኞ ዕለት አንድ የእግር ኳስ ክለብ ኃላፊ ዳኛ መመታቸውን ተከትሎ የከፍተኛው ሊግ እግር ኳስ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አዟል።
አንካራጉጁ የተባለው ክለብ ፕሬዝደንት ፋሩክ ኮቻ የመሐል ዳኛው ሐሊል መሙት ሜለርን በቡጢ መትተዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህን ድርጊት የፈፀሙት ቡድናቸው 1-0 እየመራ በ97ኛው ደቂቃ በተቀናቃኙ ክለብ ሪዜስፖር አንድ ጎል ከተቆጠረበት በኋላ ነው።
“ሁሉም የሊጉ ጨዋታዎች ለጊዜው ተቋርጠዋል” ሲሉ የቱርክ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊቀ-መንበር ሜህሜት ቡዩኬክሲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
“ይህ ጥቃት በቱርክ እግር ኳስ ታሪክ እጅግ አሳፋሪው ነው” ብለዋል።
ዳኛው ሜለር ተመትተው ወድቀው ሳለ ሌሎች ሰዎችም መጥተው በተኙበት ደብድበዋቸዋል፤ አነስተኛ ስብራትም ደርሶበቸዋል።
ከዚህ በኋላ የክለብ ኃላፊዎችና ተጫዋቾች የተሳተፉበት ከፍተኛ ግርግር ተነስቷል።
የቱርክ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር አሊ የርሊካያ የክለቡ ኃላፊ አደጋ ደርሶባቸው ሆስፒታል ቢሆኑም ሕክምና ካገኙ በኋላ “በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ” ገልጠዋል።
ሚኒስትሩ አክለው በተፈጠረው ክስተት የተሳተፉ ሌሎች ሰዎች እንዲሁ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ተናግረዋል።
- ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የባይናንስ ማስታወቂያ በመሥራቱ የ1 ቢሊዮን ዶላር ክስ ተመሠረተበት30 ህዳር 2023
- ግራናዳ ከቢልባዎ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመልካች በመሞቱ ምክንያት ተቋረጠ11 ታህሳስ 2023
- ጆኒ ቬጋስ፡ የእግር ኳስ ከዋክብት የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳመር የሚደውሉለት ኢትዮጵያዊ15 ህዳር 2023
የ37 ዓመቱ ሜለር በቱርክ አሉ ከሚባሉ ዳኞች አንዱ ሲሆን ለፊፋ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን የሚዳኙ፤ አልፎም በአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር ጉምቱ ከሚባሉ ዳኞች ተርታ የሚሰለፉ ናቸው።
ዳኛው ሆስፒታል ገብተው ሕክምና ቢያገኙም “ለሕይወታቸው የሚያሰጋ አደጋ እንዳልደረሰባቸው” ሐኪሞች ተናግረዋል።
ነገር ግን ጭንቅላታቸው ውስጥ አደጋ ደርሶባቸው እንደሆነ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደርግላቸው ተሰምቷል።
ብዙዎችን ካስደገነጠው ክስተት በኋላ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ባሰሙት ንግግር “ዳኛው ላይ የደረሰውን ጥቃት አወግዛለሁ፤ ቶሎ እንዲያገግሙም እመኝላቸዋለሁ” ብለዋል።
“ስፖርት ማለት ሰላምና ወንድማማችነት ነው። ስፖርት ከአመፅ ጋር አይዛመድም። በቱርክ ስፖርት አመፅ እንዲስፋፋ በፍፁም አንፈቅድም” ሲሉ ተናግረዋል።
በቱርክ ሱፐር ሊግ የሚጫወተው ኤምኬኢ አንካራጉጁ በለቀቀው መግለጫ “ዛሬ [ሰኞ] ምሽት በተፈጠረው ክስተት እጅግ አዝነናል” ብሏል።
“በኤርያማም ስታድየም ለተከሰተው አሳዛኝ ድርጊት የቱርክ እግር ኳስ ቤተሰብን እና መላውን የስፖርት ማሕበረሰብ ይቅርታ እንጠይቃለን።”
ተቀናቃኙ ጃይኩር ሪዜስፖር ክለብ በበኩሉ በተፈጠረ ነገር ማዘኑን ገልጦ ለዳኛው ድጋፉን አሰምቷል።
“ለዳኞች ማሕበረሰብ፤ በተለይ ደግሞ የጨዋታው ዳኛ ለነበሩት ሐሊል ሜለር ድጋፋችንን እንገልጣለን፤ እንዲሻላቸውም እንመኛለን” ይላል ክለቡ የለቀቀው መግለጫ።
የቱርክ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሃገሪቱ እግር ኳስ የተሻለ እንዲሆን የተለያዩ እምርጃዎችን እንደሚወስድ አሳውቋል።
“አንካራጉጁ እና የክለቡ ኃላፊዎች ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ሲሉ ሊቀ-መንበሩ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
ከሃገሪቱ ታላላቅ ክለቦች አንዱ የሆነው ጋላታሳራይ በቱርክ እግር ኳስ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ነገር ስላለ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራ ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የቱርክ ዳኞች ማሕበር ሁሉም የእግር ኳስ ዳኞች ወደሜዳ እንዳይገቡ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ “ዳኛ ሜለር ላይ የደረሰው ጥቃት በማለው የዳኞች ማሕበር አባላት ላይ የተሰነዘረ ነው” ብሏል።