
12 ታህሳስ 2023
የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ከሞቱ አሥር ዓመታትን አስቆጠሩ።
የጽናት እና የነጻነት ቁንጮ በመሆን መላው ዓለም ከሚስማማባቸው አንዱ ናቸው።
ማንዴላ አይበገሬ የሚለው ስያሜያቸውም ጥያቄ አይነሳበትም።
የጨቋኙ የጥቂት ነጮች የዘር መድልዎ [አፓርታይድ] ሥርዓት መገርሰስን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካውያን ያለሙት የምጣኔ ሀብት እኩልነት አሁንም ህልም እንደሆነ ነው።
የአገሪቱን ዋነኛ ሀብት የሚቆጣጠሩት ነጮች ሲሆኑ፣ በርካታ ጥቁሮችም በድህነት እየማቀቁ ይገኛሉ።
ለዚያም ነው አዲሱ ትውልድ የፓርቲያቸውን አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እንዲሁም የነጻነት ታጋዩን ትሩፋት እየገመገሙ ያሉት።
“ከማንዴላ አሻራ ጋር የፍቅር እና የጥላቻ ግንኙነት ነው ያለኝ” ይላል የ26 ዓመቱ ሲህሌ ሎንዜ ስለ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ሲናገር።
ሲህሌ ሎንዜ ዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት በአውሮፓውያኑ 1994 ከተገረሰሰ በኋላ ያለው የትውልድ አካል ነው።
በደቡብ አፍሪካ የምጣኔ ሀብት እኩልነት ለማምጣት የሚታገለው እና የአገሪቱ ሦስተኛ ትልቁ ፓርቲ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ የተማሪዎች ክንፍ መሪ ነው።
እነ ሲህሌ አፓርታይድን ለመገርሰስ የነበረውን ትግል አያውቁትም፣ እንዲሁም የቀደሙት ትውልዶች የትግል ታሪክንም በማግዘፍ አያዩትም።
ማንዴላ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ትንንሽ ልጆች የነበሩት እነ ሲህሌ የፀረ አፓርታይድ ትግሉን እና ያስገኛቸውን ትሩፋቶች በመገምገም ላይ ናቸው።
- ሻምበል ጉታ ዲንቃ፡ የነጻነት ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላን ከሞት ያተረፉት ኢትዮጵያዊ7 ነሐሴ 2022
- ማንዴላ ታስረውበት የነበረው ክፍል ቁልፍ ለጨረታ መቅረቡን ደቡብ አፍሪካ ተቃወመች25 ታህሳስ 2021
- የኔልሰን ማንዴላ ሴት ልጅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ13 ሀምሌ 2020

ማንዴላ በዓለማችን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ተደማጭነት እንዲሁም ተጽዕኖ መፍጠር ከቻሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ናቸው።
ገና በወጣትነታቸው ጭቆናን ተጸይፈው ትግሉን ተቀላቀሉ። በትግላቸውም ጨቋኙ አገዛዝ እስር ቤት ወረወራቸው። በእስር ቤትም 27 ዓመታትን አሳለፉ።
የአናሳ ነጮች አገዛዝ እንዲያከትም ትግል እና ድርድር መደረጉንም ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ለመሆን በቁ።
ከአንድ የፕሬዝዳንትነት ዘመን በኋላም ሥልጣን ለቀቁ። በ95 ዓመታቸውም በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 5/ 2003 አረፉ። ማንዴላ ሲያርፉ ደቡብ አፍሪካ አለቀሰች። የነጻነት አባት፣ አባት አለፉ ተባለ።
ሲህሌ ሎንዜ ማንዴላ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች የፖለቲካ ነጻነትን ማጎናጸፍ ቢችሉም የምጣኔ ሀብት ነጻነት ሊያመጡ እንዳልቻሉ በማንሳት ትችቱን ያቀርባል።
አንዳንድ ተቺዎች “አገራቸውን የሸጡ” ብለው እንደሚፈርጇቸው ግን አልከሰሳቸውም። ነገር ግን ሲህሌ እንደሚለው ማንዴላ ከአፓርታይድ መንግሥት ጋር ሲደራደሩ በጣም በርካታ ነገሮችን አሳልፈው ሰጥተዋል ይላል።
ማንዴላ በመጀመሪያ ቃል በገቡት መሠረት በመሬት እና በሀብት ክፍፍል ላይ ስምምነት እንዲደረስ “ጠንከረው መግፋት” ነበረባቸው ይላል ሲህሌ ብስጭቱን በሚያሳብቅ ድምጽ።
ማንዴላ የፓርቲያቸው ኤኤንሲ ዓላማ ማዕድን፣ ባንኮች እና በጥቂቶች የበላይነት የተያዙ ኢንዱስትሪዎችን ብሔራዊ ለማድረግ ዓላማ እንዳለው በአውሮፓውያኑ 1990 ተናገሩ።
ነገር ግን እነዚህን ኢንዱስትሪዎች ወደ ብሔራዊ ሀብትነት መቀየሩ በምጣኔ ሀብቱ ላይ መጥፎ ተጽእኖ ይኖረዋል በሚል ስጋት እንዲሁም የሥልጣን ሽግግሩን የተለሳለሰ እንዲሆን በሚል ይህ ፖሊሲ እንዲቋረጥ አድርገዋል።
ይህም ሁኔታ ደቡብ አፍሪካን በዓለም ላይ ካሉት የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከፍተኛ አለመመጣጠን ከሚታይባቸው አገራት መካከል አንዷ እንድትሆን እንዳደረጋት ሲህሌ ይናገራል።
የዓለም ባንክ በአውሮፓውያኑ 2022 ባወጣው ሪፖርት መሠረት 10 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሀብት መቆጣጠሩን ያሳያል።
ዘር የምጣኔ ሀብቱ አለመመጣጠን መሠረታዊ ቁልፍ ሆኖ እንደቀጠለም ሲህሌ ያስረዳል።
ጥቂቱ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ማኅበረሰብ በአፓርታይድ ወቅት የበዘበዙትን አብዛኛውን ሀብትም እንደያዙ ናቸው።
ይህም ጫና በጥቁሩ ማኅበረሰብ እንዲሁም አዲሱ ትውልድ እየተሰማው ይገኛል።
“ኔልሰን ማንዴላ ቃል በገባው እና በምንኖርበት እውነታ መካከል ትልቅ ክፍተት አለ” ይላል።
የአሁኑ ትውልድ ከፍተኛ መከራ እያየ ነው። የደቡብ አፍሪካ የሥራ አጥነት መጠን 60 በመቶ ደርሷል። በአገሪቱ ውስጥ የሚገደሉ ሰዎች እንዲሁም የአደንዛዥ ዕጽ በ20 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ላይ ነው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‘ኔክስት ጄነሬሽን ፋውንዴሽን’ ውስጥ እየተሳተፈች ያለችው የ24 ዓመቷ አኒታ ዳዋይባ በበኩሏ የደቡብ አፍሪካ ሁኔታ በአእምሮዋ ውስጥ አንድ ተደጋጋሚ ጥያቄ እንድታነሳ አድርጓታል “የራሴን ቤተሰብ ለመመሥረት ረዥም ዕድሜ ይኖረኝ ይሆን ወይ?” የሚለውን።

በርካታ ጓደኞቿ በአገሪቱ በተንሰራፋው ወንጀል ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ነገር ግን አኒታ ለደቡብ አፍሪካ ውድቀት ማንዴላን ተጠያቂ አታደርግም። የአፓርታይድን ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ ለማስወገድ ማድረግ የነበረባቸውን ሁሉ አድርገዋል ትላለች።
የኔልሰን ማንዴላ ትሩፋትም ሆነ አሻራ በአዲሱ ትውልድ መካከል ከፍተኛ ውዝግቦችን ቢፈጥርም ለአኒታ ግን ማንዴላ ለከፈሉት መስዋዕትነት ያላት አድናቆም መቼም ቢሆን ቀንሶ አያውቅም።
እናቷ በነጻነት ትግሉ ውስጥ የታገለች ሲሆን፣ ከእናቷ የወረሰችው የታጋይነትን መንፈስ ብቻ ሳይሆን ለማንዴላ የነበራትን አድናቆትንም ጭምር ነው። በማንዴላ ላይ የሚሰነዘሩት ትችቶችም ቢሆኑ ያላትን ስሜት አላደበዘዘውም።
በምሥራቃዊ ኬፕ ግዛት የኤኤንሲ የወጣቶች ክንፍ መሪ ምዞባንዚ ንክዌንሻ በበኩሉ አባቱ የማንዴላን ሥዕል በቤታቸው ሳሎን ላይ የሰቀሉበትም ዋነኛ ምክንያት እያንዳንዱ ጎብኚ ማየቱን ለማረጋገጥ እንደሆነ ይናገራል።

እሱም ቢሆን አንድ ቀን ቤት ሲኖረው የማንዴላን ፎቶ እንደሚሰቅል ያስባል።
“ኔልሰን ማንዴላ ሁልጊዜም ቢሆን የደቡብ አፍሪካ አብዮት መሪ እንዲሁም ታላቅ የአገር መሪ ናቸው” ሲልም ምዞባንዚ ስለ ማንዴላ ይናገራል።
የማንዴላ ስኬት ብሎ ከሚጠራቸው ለጥቁር ሕዝቦች ትምህርት እና መኖሪያ ቤት ማሻሻል እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ እና ድጎማዎችን ነው።
እነዚህ ፖሊሲዎች በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ድሆች አሁንም ቢሆን ስሜት እንደሚሰጡት ያስረዳል።
ማንዴላ ከአፓርታይድ አገዛዝ ጋር በነበራቸው ድርድር በርካታ ነገሮችን አሳልፈው ሰጥተዋል የሚለውን መከራከሪያ የሚቃወመው ምዞባንዚ፣ ሰላም ባይመጣ የእርስ በርስ ጦርነት ይነሳ ነበር ይላል።
ይህ ትውልድ ለምጣኔ ሀብት እኩልነት ለመታገል የትግል በትሩን ተቀብሏል ይላል።
የማንዴላ ወራሾች
ከአዲሱ ትውልድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ያለው ፓርቲያቸው ኤኤንሲ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ሊያሸንፉ ይችላል ወይ? ለሚለው ጥያቄ ሲህሌ “አይመስለኝም” ይላል።
“በርካቶች የማንዴላ መንፈስም ሆነ ቀልብ ይገዛቸው ነበር። ነገር ግን ሁሉ ነገር ማብቂያ አለው” የሚለው ሲህሌ፣ ሆኖም በዕድሜ የገፉ መራጮች አሁንም በዚህ ሊታለሉ እንደሚችል ይናገራል።
በደቡብ አፍሪካ የተንሰራፋው ሙስና ዘሩ የተዘራው በማንዴላ የሥልጣን ዘመን ከአውሮፓውያኑ 1994 – 1999 እንደሆነ የሚናገሩት ተችዎች፣ እሳቸውም ነገሩን እንዳላየ አልፈውታልም ብለው ይወቅሷቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 1996 ታዋቂ የኤኤንሲ መሪ እንዲሁም ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት ባንቱ ሆሎሚሳ የማንዴላ የምክር ቤት አባል የነበሩ ግለሰብን በአፓርታይድ ዘመን ከአንድ ቁማር ቤት (ካሲኖ) ጉቦ ወስደዋል በማለት ከሰዋቸው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ማንዴላ ባንቱ ሆሎሚሳን ከመንግሥት ሥልጣን ያነሷቸው ሲሆን፣ ኤኤንሲ በበኩሉ ፓርቲውን ለውርደት ዳርገውታል በሚል አባሯቸዋል።

ካረፉ 10 ዓመት የሆናቸው ፕሬዝዳንት ማንዴላ ለኤኤንሲ ጥልቅ ታማኝነት ነበራቸው። የራሳቸውን ስም የሚጎዳ እንኳ ቢሆን ለፓርቲው ነበር ቅድሚያ የሚሰጡት።
ማንዴላ የነጻነት ታጋይ፣ የአገሪቱ አባት፣ አዳኝ ሆነው ለአዲሱ ትውልድ ቢሳሉም በእሳቸው ላይ የተደበላለቀ ስሜት መስተናገዱ አልቀረም።
በደቡብ አፍሪካ ሮድስ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርቷን እየተከታተለች ያለችው የ24 ዓመቷ ማታቦ ማህሎ በበኩሏ የአዲሱን ትውልድ አባላት “ግራ የተጋቡ” ስትል የምትጠራቸው ሲሆን፣ የማንዴላንም ትሩፋት በከፋ ሁኔታ ይተቹታል ትላለች።
ለእሷ ማንዴላ አሁንም ቢሆን ደቡብ አፍሪካውያን የሚፈልጉትን ለውጥ ማምጣት አንደሚችሉ ተስፋን የሚፈነጥቁ ናቸው ትላለች።