የገንዘብ ሚኒስትሩ ስለተሰጠኝ እውቅና ክብር ይሰማኛል ብለዋል
የምስሉ መግለጫ,የገንዘብ ሚኒስትሩ ሙቱሊ ኑቤ ስለተሰጠኝ እውቅና ክብር ይሰማኛል ብለዋል

12 ታህሳስ 2023

የዚምባብዌ ዜጎች በገንዘብ ሚኒስትራቸው የሰሞኑ እውቅና ተደናግጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ሙሉሊ ኑኔ የአፍሪካ ምርጡ የፋይናንስ ሚኒስትር ተብለው መሰየማቸው ነው ድንጋጤ የፈጠረባቸው።

አንድ ዚምባብዌያዊ በኤክስ ገጹ ‘’ካፒቴኑ መርከቧን ከበረዶ ግግር ጋር በማላተሙ እንዴት ይጨበጨብለታል?’’ ሲል ትችቱን ጽፏል።

ሌላ ዜጋ ደግሞ ‘’የክፍለ ዘመኑ ቧልት መሆን አለበት’’ ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

የዚምባብዌ የሥራ አጥ ቁጥር 85 ከመቶ ደርሷል።

በአገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ ግብይት የሚካሄደው በአሜሪካን ዶላር ሲሆን የአገሬው መገበያያ ገንዘብ በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ እያጣ ስለመጣ ወደ ወረቀትነት ዝቅ እያለ ነው።

አገሪቱ በኢኮኖሚና ፋይናንስ አዘቅት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ነው ታዲያ የዚምባብዌ ገንዘብ ሚኒስትር የተሸለሙት።

እውቅናውን ለሚኒስትሩ ሙቱሊ ኑቤ የሰጠው ‘ሬፑቴሽን ፖል ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ነው።

ሚኒስትር ሙቱሊ ለአገሪቱ ሄራልድ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ‘’ይህን እውቅና በማግኘቴ ክብር ይሰማኛል’’ ብለዋል።

ጨምረውም ‘’ይህ እውቅና እሳቸውና የግምጃ ቤት ሠራተኞች በጋራ የዚምባብዌን ኢኮኖሚ ወደፊት ለማራመድ ላደረጉት ጥረት የተሰጠ እውቅና ነው’’ ብለዋል።

ማኅበራዊ ትችቶችን በመሰንዘር የሚታወቁት ሆፕዌል ቺኖኖ በኤክስ ገጻቸው ይህ ሽልማት ‘’ለዚምባብዌ ሕዝብ ስድብ ነው’’ ብለዋል።

በተለይም በቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚኒስትሩ ያቀረቡት በጀት እንደ ተቺው ቺኖኖ ከሆነ ‘’በታሪክ ጸረ ሕዝብ በጀት’ ተብሎ ሊመዘገብ የሚገባው ነው’’

የግብር ጭማሪው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለፓስፖርት ክፍያ ተመን ከ120 ዶላር ወደ 200 ዶላር ከፍ እንዲል አድርገዋል። ይህም ከአካባቢው አገራት ሁሉ ተመን የላቀ ነው።

ቺኖኖ እንደሚሉት የፋይናንስ ሚኒስትሩ እየመሩት ያሉት በዓለም ላይ በብልሹነቱ ተወዳዳሪ የሌለውን ውጥንቅጡ የወጣ ኢኮኖሚ ነው። ውጥንቅጡ የወጣውም በተሳሳተ ፖሊሲ አመራርና በሙስና የተተበተበ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የዚምባብዌ ምጣኔ ሃብት ለዓመታት ችግር ውስጥ የወደቀ ኢኮኖሚ ነው።

የዚምባብዌ ዶላር በፈረንጆቹ 2009 መሬት በመንካቱ ነው ከገበያ የወጣው። ለአንድ ሳንቲም ዶላር 231 ሚሊዮን የዚምባብዌ ዶላር ምንዛሬ ደርሶ የነበረ ሲሆን በየአንድ ሰዓቱ ዋጋው እየወረደ ቆይቷል።

ተቺዎች ኢኮኖሚው ሊንኮታኮት የቻለው በገዢው የዛኑ ፒኤፍ ያልተቀናጀ አመራር ምክንያት ነው። ይህም በሮበርት ሙጋቤ ጀምሮ በፕሬዝዳንት ምናንጓጓ የቀጠለ ነው።

ለውደቀቱ አንድ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ በምዕራብ አገራት የተጣለ ማእቀብ ነው።