
12 ታህሳስ 2023, 08:56 EAT
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ክላውዲን ጌይ በተቋሙ ስላለው ጸረ ሴማዊነት በአሜሪካ ህግ መምሪያ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ቀርበው በሰጡት ምስክርነት ምክንያት ከስልጣናቸው እንዲለቁ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው ነው።
ዶ/ር ጌይ በአይሁዶች ላይ የዘር ማጥፋትን የቀሰቀሱ ተማሪዎች በተቋሙ ስለሚጠብቃቸው ቅጣት ምንም ባለማለታቸው ይቅርታ ለመጠየቅ ተገደዋል።
በሳምንቱ መጨረሻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃርቫርድ ባልደረቦቻቸው ዩኒቨርስቲው እንዳያባርራቸው በመወትወት ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል።
ዕጣ ፈንታቸው ሰኞ በሚከናወነው በሃርቫርድ ኮርፖሬሽን ስብሰባ ላይ ሊወሰን ይችላል ተብሏል።
ዶ/ር ጌይ ከፍተኛ ትችት ያስከተለውን አስተያየት የሰጡት ባለፈው ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት ነው።
ኤሊዛቤት ማጊል ከፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ እና ሳሊ ኮርንብሉዝ ከኤምአይቲም በዚሁ ወቅት ተገኝተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“የአይሁዶች የዘር ይጥፋ ዘመቻ ማለት የሃርቫርድን የስነምግባር ደንብ መጣስ ነው ወይ?” ተብለው በሪፐብሊካን የተወካዮች የምክር ቤት አባል ኤሊስ ስቴፋኒክ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ጌይ ጉዳዩ “እንደ አውዱ ይታያል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ጌይ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጣ ከሆነው ክሪምሰን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አዝናለሁ። ቃላቶች ጭንቀትን እና ህመምን ሲያበዙ ከጸጸት በስተቀር ምን ሊፈጥር እንደሚችል አላውቅም” ብለዋል።
13 አባላት ያሉት የሃርቫርድ ኮርፖሬሽን ሰኞ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዟል። በዶ/ር ጌይ ዕጣ ፈንታ እና በተቋሙ ሊኖሩ ስለሚችሉ የድርጊት መርሃ ግብሮች እንደሚመክሩ ተዘግቧል።
ቅዳሜና እሑድ ከ500 የሚበልጡ የሃርቫርድ ሠራተኞች “ፕሬዝዳንት ክላውዲን ጌይ ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቁትን ጥሪዎች ጨምሮ ከሃርቫርድ የአካዳሚክ ነፃነት መርሆዎች ጋር የሚጋጩ የፖለቲካ ጫናዎችን ለመቋቋም የድጋፍ ፊርማ አሰባስበዋል።
ሰኞ ረፋድ ላይ ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን ያሰፈሩ ሠራተኞች ቁጥር ወደ 700 ደርሷል።
ፊርማውን በማሰባሰብ ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ አንዷ አሊሰን ፍራንክ ጆንሰን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ሠራተኞቹ “በፖለቲካዊ ድራማ ምክንያት ሊያጡዋት አይፈልጉም” ብለዋል።
“ከእሷ ጋር የማይስማሙ ሰዎችን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ካሉ ምሁራን፣ የሥራ ባልደረቦቿ እና አመራሮች ምን ያህል ድጋፍ እንዳላት ብዙ ሰዎች የተረዱ አይመስለኝም ” ሲሉ አክለዋል።
- ጋዛ፡ “የት እንድንሄድ ነው የሚፈልጉት? እንዲህ ሆነን የት እንሂድላቸው?”7 ታህሳስ 2023
- ቀይ መስቀል ታጋቾችን በማስለቀቁ ሂደት ምን ሚና ነበረው?6 ታህሳስ 2023
- ልብሳቸው ተገፎ ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች የተያዙ ፍልስጤማውያን ወንዶችን የሚያሳይ ቪድዮ ይፋ ሆነ8 ታህሳስ 2023
በሐምሌ ወር ወደ ስልጣን መጡት ዶ/ር ጌይ በ368 ዓመታት የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ጥቁር ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል።
ከ70 የሚበልጡ የኮንግረስ አባላት ማጊል እና ዶ/ር ኮርንብሉዝን ጨምሮ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶቹ ከሥራቸው እንዲለቁ ጥያቄ አቅርበዋል።
አብዛኛዎቹ የሪፐብሊካን አባለት የሆኑት ህግ አውጪዎች በጻፉት ደብዳቤ የፕሬዝዳንቶቹን መልሶች “አስጸያፊ” እና “ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሪዎቻችን ከምንጠብቀው መርህ ጋር በእጅጉ የተቃረነ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
ቅዳሜ ዕለት ፕሬዝዳንት ማጊል “በፍቃደኝነት የሥራ መልቀቂያቸውን ማስገባታቸውን” አስታውቀዋል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ለዩኒቨርሲቲው ድጋፍ የሚያደርግ አንድ ለጋሽ ፕሬዝዳንቷ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም የ100 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ካቋረጠ በኋላ ነው።
ማጊል ከስልጣን መልቀቃቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ፣ ስቴፋኒክ በዶ/ር ጌይ እና በዶ/ር ኮርንብሉዝ ላይ ማነጣጠራቸውን ቀጥለዋል።
በኤክስ ላይ “አንዷ ሄዳለች፣ ሁለት ይቀሩናል” ሲሉ ጽፈዋል።
በመላው አሜሪካ የሚገኙ ኮሌጆች የፍልስጤም ወይም የእስራኤል ደጋፊ የሆኑ ሰልፎች እየተካሄዱባቸው ሲሆን ይህም ሁኔታ የእስልምና እንዲሁም የጸረ ሴማዊነት ጥላቻዎችን እንዳያነሳሱ ስጋትን ፈጥሯል።