በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ግዛቸው ጎሹ በጂቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ እንደሚገመት ይናገራሉ።

12 ታህሳስ 2023

ጦርነት ካደቀቃት የመን የመጣ ስደተኛ፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለማቋረጥ አስበው እዚያ የተገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ የጦር ካምፓቸው በዚያ የሆነ የተለያዩ አገራት ወታደሮች፣ የከባድ መኪና ሹፌሮች፣ በግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ እስያውያን እና ሌሎችንም ጂቡቲ በጉያዋ አቅፋ ይዛለች።

በጎዳናዎቿ የኢትዮጵያ ከባድ መኪናዎች የሚመላለሱባት፣ ቀይ ባሕርን ታክካ የተመሠረተች፣ በአፍሪካ ቀንድ ብቸኛዋ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገር ጂቡቲ፣ እንግሊዝኛን በሥራ አልያም በትምህርት ቋንቋነት የሚጠቀሙ አገራት ከብበዋታል።

ምሑራኖቿ በጦርነት በሚናጡ የአፍሪካ ቀንድ አገራት የተከበበችው ጂቡቲ፣ ከሕዝቦቿ ቁጥር የማይተናነስ ፍልሰተኛ ይኖርባታል ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህ የተነሳም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖሩባታል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ግዛቸው ጎሹ በጂቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ እንደሚገመት ይናገራሉ።

በእርግጥ የእርሳቸውን ግምት በጂቡቲ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አልዬ አብደላንም ያስማማል።

አንዳንድ የጂቡቲ ምሑራን ግን ቁጥሩን ከዚህም በላይ ከፍ ያደርጉታል።

የአገሪቱ ዜጎች በብዛት የሚኖሩት በዋና ከተማዋ ጂቡቲ ነው። ከዚያ ውጪ ግን አሊ ሳቤህ፣ ዲኪል፣ ታጁራ፣ አርታ እና ኦቦክም በስሯ የሚገኙ ክፍለ አገሮቿ ናቸው።

ጂቡቲ ቀይ ባሕርን ታክካ የተመሠረተች አገር እንደ መሆኗ፣ ለኤደን ባሕረ ሰላጤ ቅርብ ናት። በባሕረ ሰላጤው በኩልም ሕንድ ውቅያኖስን ታገናኛለች።

የባሕር በር ለሌላት ኢትዮጵያ በር ሆና የምታገለግለው ይህች አገር፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊ ይኖርባታል።

አቶ አሊዬ “ለማኅበረሰባችን ለመኖር የምትመች አገር ነች። በተለይ በምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ ያሉ ሕዝቦች ጂቡቲን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ነው የሚያይዋት” ይላሉ።

አክለውም “በሕጋዊነት ገብተው የሚሠሩ ከሆነ ለሥራ ምቹ አገር ነች። ብዙ የእኛ ሠዎች እዚህ እየሠሩ አድገዋል” ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ሠነድ አልባ ዜጎች

ኢትዮጵያውያን በሦስት የጎረቤት አገራት በኩል የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ይሰደዳሉ።

በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ እና አውሮፓ፣ በኬንያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ በጂቡቲ በኩል ደግሞ ወደ መከካለኛው ምሥራቅ ይሻገራሉ።

ቢቢሲ በአገሪቱ የተለያየ ክፍል ተንቀሳቅሶ እንዳስተዋለው ሠነድ አልባ ኢትዮጵያውያን በጂቡቲ ብዙ ናቸው።

በጂቡቲ ከተማ የተለያየ የጉልበት ሥራ ሲሠራ ያገኘነው ኢብሳ ጂቡቲ ከመጣ ሁለት ዓመት ሆኖታል። “ችግሮች ቢኖሩም ከኢትዮጵያ እዚህ ይሻላል” ይላል።

“ኑሮ ከኢትዮጵያ ይሻላል። የተለያየ ሮሮም ግን አለ። ዝም ብሎ ሰው ይዞ ማሠር አለ። ፈተናው ብዙ ቢሆንም ለእኔ እዚህ ይሻለኛል። እዚህ ኑሮዬን ማሻሻል እችላለሁ” ይላል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የሆኑት አቶ ግዛቸው በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያውያን በጂቡቲ ለበርካታ ዓመታት ቢኖሩም የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።

ይህ ደግሞ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል።

ሕጋዊ የመኖርያ ፈቃድ የሌለው ግለሰብ ለልጆቹ የልደት ምስክር ወረቀት ማውጣት አይችልም።

ትምህርት ቤቶች ደግሞ ተማሪዎቻቸውን ሲቀበሉ የልደት ሰርተፍኬት ይጠይቃሉ። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያውያን ልጆቻውን ለማስተማር ፈተና ውስጥ ይወድቃሉ።

አቶ አልዩ ግን ለዚህ መፍትሔ ነው ያሉትን እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

የጂቡቲ መንግሥት የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት መክፈት የሚያስችላቸውን 4 ሔክታር መሬት በነጻ እንደሰጣቸው እና በ5 ሚሊዮን ዶላር ግንባታ ለመጀመር ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑን ይገልጻሉ።

ገንዘብ ዘርዛሪዎቹ ሶማሌያውያን ሴቶች በእግረኞች እና በተሽከርካሪዎች በተጨናነቀው የጅቡቲ ጠባብ መንገድ ዳር ሰፊ ቦርሳቸውን ጭናቸውን ላይ አስቀምጠው፣ የፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጠው ይታያሉ።
የምስሉ መግለጫ,ገንዘብ ዘርዛሪዎቹ ሶማሌያውያን ሴቶች በእግረኞች እና በተሽከርካሪዎች በተጨናነቀው የጅቡቲ ጠባብ መንገድ ዳር ሰፊ ቦርሳቸውን ጭናቸውን ላይ አስቀምጠው፣ የፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጠው ይታያሉ።

ሳሪፊሌ – ገንዘብ ዘርዛሪዎቹ ሶማሌያውያን ሴቶች

በእግረኞች እና በተሽከርካሪዎች በተጨናነቀው የጂቡቲ ጠባብ መንገድ ዳር ሰፊ ቦርሳቸውን ጭናቸውን ላይ አስቀምጠው፣ የፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጠው ይታያሉ።

እግሮቻቸውን ከእንጨት በተሰራ ዱካ ላይ አሳርፈው ገንዘብ ሊዘረዝር የሚመጣ ደንበኛን ይጠባበቃሉ።

አገሬው ሳሪፊሌ ሲል ይጠራቸዋል። ገንዘብ መንዛሪዎች ወይም ዘርዛሪዎች ማለት ነው በሱማሊኛ።

በቦርሳቸው ውስጥ የበርካታ አገራት ገንዘብ ይታያል። ዶላር፣ ዩሮ፣ ፓውንድ፣ የጂቡቲ ፍራንክ፣ የኢትዯጵያ ብር፣ ወዘተርፈ. . . ትንሽ ትንሽ አማርኛ፣ ጥቂት አንግሊዝኛ ይሞክራሉ።

ነገር ግን የአገሬው መግባቢያ የሆኑትን ሶማሊኛን ወይንም ፈረንሳይኛን ይመርጣሉ።

በጂቡቲ ጎዳናዎች የሚንቀሳቀስ አገር ጎብኚ፣ ስደተኛ፣ ወታደር፣ ነጋዴ ያለ ችግር ምንዛሬውን ከእነርሱ መሸመት ይችላል።

በጂቡቲ ዋና መንገድ ዳርቻዎች ፎቅ ተደግፈው የውጪ ገንዘቦችን የሚመነዝሩት ሴቶች ብቻ የሆኑበት ምክንያት ግልጽ አይደለም።

በዕድሜም ከወጣት እስከ ጎልማሳ በንግዱ ላይ ተሰማርተዋል።

የጂቡቲ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ወደ ባሕር ማዶ ለንግድ መሄድ ቢፈልጉ ምንዛሪ ለማግኘት ከእነዚህ ሴቶች አንደሚጠቀሙም ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያውያን በተሞላው ፒካዱስም እነዚሁ ሴቶች ቦርሳቸውን ሸክፈው የፕላስቲክ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ምንዛሪውን ይሠራሉ።

በፒካዱስ ግን ገበያ መሀል አንጂ ሕንጻ ተደግፈው አይቀመጡም።

ከፀሐይ መከለያ ጥግ የላቸውም።

በፒካዱስ ካለ እነሱ የጂቡቲን ፍራንክ የሚፈልጉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ኑሯቸውን ማሳለጥ ይከብዳቸው እንደነበር ይናገራሉ።

በፒካዱስ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ የሚያማርሩት የሌብነት ተግባር እነዚህን ሴቶች ያሰጋቸው አይመስልም። ብዙ ገንዘብ በቦርሳቸው አጭቀው ያለ ችግር ደንበኞቻቸውን ይጠባበቃሉ።

በጂቡቲ ከተማ ላይ የሚገኝ ጽሑፍ

ስድስት ቋንቋ የሚናገሩ ኢትዮጵያውን

ጂቡቲ ዛሬም ድረስ የቅኝ ገዢዋን ፈረንሳይኛ ቋንቋ አልጣለችም። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእስልምና እምነት ተከታይ በመኖሩ ደግሞ አረብኛን የሚናገሩ ዜጎች አሏት።

የአገሬው ቀደምት ሕዝቦች ሶማሊ እና አፋሮችም የራሳቸውን የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች፤ ሶማሊኛ እና አፋርኛን ይናገራሉ።

በአገሩ በተለያየ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ፣ በወታደርነት የመጡ ደግሞ እንግሊዝኛን በመናገር አገሪቱን የሉላዊነቱ አካል እንድትሆን ያደርጋሉ።

ለዚህም ነው በጂቡቲ ጎዳናዎች ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ እና ሶማሊኛ የሚያቀላጥፉ አዛውንቶች፣ እንግሊዝኛ ለመናገር የሚጥሩ ወጣቶች እና ስደተኞችን ማየት የተለመደ የሆነው።

ፈረንሳይኛ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች የሥራ ቋንቋ፣ አረብኛ የሃይማኖት ቋንቋ እንግሊዝኛ ደግሞ የኢንቨስትመንት ቋንቋ ይመስላል።

ፋሪስ እናት እና አባቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። እናቴ የባቲ ሰው አባቴ ደግሞ የጎጃም ነው ይላል።

ይህንን ከእናት እና ከአባቱ ይስማ እንጂ ኢትዮጵያን ረግጦ አያውቅም።

በርቀት ጎጃም ዘመድ አለኝ፣ ባቲ ደግሞ ቤተሰብ ከማለት በዘለለ ኢትዮጵያ ለእርሱ የቅርብ ሩቅ ናት።

ከኢትዮጵያ ሌላ የቀረው አማርኛ ቋንቋ ነው።

ከዚያ ውጪ ሶማሊኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አፋርኛ፣ እና እንግሊዝኛ ይናገራል።

ይህን ሁሉ እንዴት ስንለው የተወሰነውን ከሚኖርበት ማኅበረሰብ የተወሰነውን ደግሞ ከትምህርት ቤት መማሩን ይናገራል።

በጂቡቲ ዋና ከተማ የሚገኘው የምንሊክ ፓላስ ሆቴል
የምስሉ መግለጫ,በጂቡቲ ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ትልልቅ ምግብ ቤቶች፣ ሚኒሊክ፣ ላፎንቴን ላ ሂስቶሪያ የተሰኙ ሆቴሎች በከተማዋ እንብርት ላይ ይገኛሉ።

አቶ አልዬ “አንዳንዴ ያስቀናሀል። እኛ አገራችን ብዙ ቋንቋ አለ። ሰዉ ግን የተወለደበትን ብቻ ነው የሚናገረው። እዚህ አንድ ሰው አምስት ስድስትም ቋንቋ ይናገራል” ሲሉ የፋሪስን እውነት ያጠናክራሉ።

ኢብሳ ከኢትዮጵያ ሲወጣ ኦሮምኛ ብቻ እንደሚናገር አስታውሶ አሁን ግን ሶማሊኛ እና አረብኛ እንደሚችል በመግለጽ “ኦሮምኛ ብቻ እየተናገሩ እዚህ መኖር አይቻልም” ይላል።

በጂቡቲ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ፈረንሳይኛ ይሰጣል። የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው ሌላው አረብኛ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ውስጥ እንደ አንድ ቋንቋ ይሰጣል።

ኢትዮጵያውያን፣ ሱማሊያውያን እና አፋሮች በጋራ በሚኖሩበት አካባቢ ያደገው ፋሪስ ከቤተሰቡ አማርኛን ከጎረቤቶቹ ሶማሊኛ እና አፋርኛን ቀስሟል።

በሚሠራበት ተቋም ፈረንሳይኛን ወደ ተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ ለመጻፍ ሌሎቹን ቋንቋዎች ደግሞ ደንበኞቹን ለማስተናገድ እንደሚጠቀም ይናገራል።

በጂቡቲ የሚገኙ መሥርያ ቤቶች በአጠቃላይ የደብዳቤ ልውውጥ ሲያደርጉ ፈረንሳይኛን መጠቀም ይመርጣሉ ይላል።

በሆቴል ውስጥ በእንግዳ ተቀባይነት የምትሠራው ፋጡማ ደግሞ እንግሊዝኛን አቀላጥፋ ትናገራለች። በአሁኑ ሰዓት ምዕራባውያን ወይንም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ካልሆኑ አገራት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል እና ለማስተናገድ እንግሊዝኛ መቻል ወሳኝ እየሆነ ነው ትላለች።

እንግሊዝኛ የዲፕሎማሲው፣ የንግዱ፣ የመከላከያ፣ የስደተኞች፣ የሚዲያ እንዲሁም የፊልሞች እና የኢንተርኔት ቋንቋ መሆኑን ትጠቅሳለች።

በዚህም የተነሳ እንግሊዝኛ መቻል የሚፈልጉ ወጣቶች ቁጥር በትምህርት ቤት እንደሌሎች ቋንቋዎች በስፋት ባይሰጥም የቋንቋ ትምህርት ቤቶች እየሄዱ መማር እንደ አንድ መንገድ መያዙን ታስረዳለች።

በጂቡቲ ጎዳና ላይ እንጀራ የሚሸጡ እናቶችን መመልከት የተለመደ ነው

የኢትዮጵያ እንጀራ በጂቡቲ ጎዳና

በጂቡቲ ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ትልልቅ ምግብ ቤቶች በርካታ ናቸው።

ሚኒሊክ እና ላፎንቴን ሆቴሎች በከተማዋ እንብርት ላይ ይገኛሉ።

ፋሪስ “ጂቡቲ ይህችው ናት” ይላል ሆቴሎቹ የሚገኙበትን አካባቢ በማሳየት።

በጂቡቲ ዋና ከተማ ብቻ ከ600 ሺህ በላይ ሰው ይኖራል። ይህ ደግሞ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ከግማሽ በላይ እንደማለት ነው።

በጂቡቲ የቡና ሱስ ያለበት ኢትዮጵያዊ፣ አንድ ስኒ አቦል ቡና በ100 ፍራንክ በየስፍራው ያገኛል። ማኪያቶ ያለ ችግር የሚገኝባቸው ካፍቴሪያዎችም አሉ።

የኢትዮጵያውያን ምግብ የሚያቀርቡ ብዙ ናቸው።

ሽሮ ከ1000 እስከ 1500 ፍራንክ፣ ጥብስ በ2000 ፍራንክ የሚበላባቸው የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶች በርካታ ናቸው።

እንጀራ በጂቡቲ አውራ ጎዳናዎች ላይ በ100 ፍራንክ ይሸጣል።

ኢትዮጵያውያን ከየመናውያን ስደተኞች ጋር እየተጋፉ በሚሄድበት አውራ ጎዳና እጣን፣ ጥሬ እና የተቆላ ቡና፣ ቅመማ ቅመም የጎዳና ላይ ንግድ ላይ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያውያንም ሆኑ የጂቡቲያውያን ምግብ ቤቶች በረንዳቸው ላይ ሺሻ ማስጨስ የተለመደ ነው።

ጂቡቲያውያን እና ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የሚያስማማው በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት ነው።

“የራሷ ወደብ ያላት አገር ጅቡቲ አንድ ሊትር ናፍጣን የምትሸጠው፣ ወደብ ከእኛ ከተከራየችው ከጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ውድ በሆነ ዋጋ ነው” ይላል የሆቴል ማናጀር የሆነው እስማኤል።

“የራሳችን ወደብ ኖሮን አንድ ናፍጣ በሊትር በ2 ዶላር ነው የምንገዛው። ከኢትዮጵያ ውድ በሆነ ማለት ነው” ይላል በቁጭት።

ጂቡቲ የኤሌትሪክ አቅርቦት የምታገኘው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ አሁንም ነዋሪዎቿ በውድነቱ ያማርራሉ።

አንድ ብቻውን የሚኖር የአገሪቱ ዜጋ በወር ከ60 ሺህ እስከ 70 ሺህ የጂቡቲ ፍራንክ ለኤሌክትሪክ እንደሚከፍል በመናገር ያማርራል።

ውሃም ቢሆን እንዲሁ በጂቡቲ ርካሽ የሚባል አይደለም። በቀላሉ በወር 5000 ፍራንክ ለቧንቧ ውሃ ማውጣት ይጠበቃል።

ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጫት፣ ፍራፍሬ እና አትክልት እንዲሁም ጥራጥሬ ታስመጣለች።
የምስሉ መግለጫ,ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጫት፣ ፍራፍሬ እና አትክልት እንዲሁም ጥራጥሬ ታስመጣለች።

የጂቡቲ አትክልት ተራ – ሪያዲ

የጂቡቲ አትክልት ተራ ለጋስ ነው። አትክልት እና ፍራፍሬ በገፍ ይገኝበታል።

ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጫት፣ ፍራፍሬ እና አትክልት እንዲሁም ጥራጥሬ ታስመጣለች።

ታድያ በሱማሌያውያን ባለቤትነት በተያዘው በዚህ ንግድ የሐረርጌ ወጣቶች በሽያጭ ሥራ ተሳትፈዋል።

ከሐረርጌዋ ፈዲስ እና ከአሰቦት፣ ከአማራ ክልል ወሎ የመጡ ወጣቶች የፍራፍሬ ንግዱ ላይ በሻጭነት ተሰማርተዋል።

አሊያስ በፍራፍሬ ገበያው ተቀጥሮ የሚሠራ ወጣት ነው። “እዚህ የሚሠሩት አብኞቹ የሐረርጌ ልጆች ናቸው፤ ወለዬዎችም አሉ” ይላል።

ከኢትዮጵያ ቃርያ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ብርቱካን እና ሙዝን ጨምሮ ሌሎች ፍራፍሬዎች እንደሚመጡ አሊያስ ይናገራል።

“የገበያ ነገር በአንድ ቦታ አይረጋም አንጂ አሁን ቲማቲም በ150 ፍራንክ፣ ድንች በኪሎ 100፣ ሽንኩርት 250 እንሸጣለን” ይላል።

ኢብሳ በበኩሉ “ከኢትዮጵያ መጥቶ እዚህ የማይሸጥ ነገር የለም” በማለት ጂቡቲ ውስጥ አብዛኛው ሰው የሚጠቀመው ከኢትዮጵያ የሚመጣውን ሲሆን፤ ጤፍ፣ ማሽላ፣ በቆሎ እና ሌሎች ጥራጥሬዎችም ከኢትዮጵያ እንደሚመጡ ይናገራል።

ኢብሳ “እኛ የምንመገበው ከኢትዮጵያ የሚመጣውን ነው። እኔ እዚህ እንዳየሁት ከሆነ ፍራፍሬዎችን ከኢትዮጵያ ተመርጦ ስለሚመጣ የበለጠ እዚህ ይገኛል።”

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን
የምስሉ መግለጫ,በጂቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን

ስለ ጂቡቲ ጥቂት እውነታዎች

ጂቡቲ የቆዳ ስፋቷ አነስተኛ ይሁን እንጂ በቀጠናው ወሳኝ አገር ናት።

በአፍሪካ ቀንድ እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ቅርብ በመሆኗ የአረቡን፣ የአውሮፓን እና የአፍሪካን ባሕል ታንጸባርቃለች።

በአገሪቱ የሰሜን ክፍል አፋሮች፣ በደቡብ ደግሞ ሶማሌዎች ይገኛሉ።

እነዚህ ሁለቱ ብሔሮች ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የጎረቤት አገራትም ይኖራሉ።

ኢትዮጵያ የተወለዱት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመሩ 24 ዓመት ሆኗቸዋል።

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንቱን ምርጫን በማጭበርበር ይከስሷቸዋል።

በጂቡቲ በአገሪቱ መንግሥት ከሚተዳደረው የመገናኛ ብዙኃን ውጪ የግል ሚዲያ የለም።

በአፋር እና በሶማሌያውያን መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎም የማኅበራዊ ሚዲያ ገደብ ተጥሏል።

አገሪቱ በረሃ በመሆኗ እና ለእርሻ የሚሆነው ጥቂት መሬት ብቻ ነው። ዋነኛ የገቢ ምንጯ የወደብ አገልግሎት ነው።

በአንጻራዊነት በአፍሪካ ቀንድ ካሉ አገራት ሰላማዊ የሆነችው ጂቡቲ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በቅርብ ርቀት ላይ ስለምትገኝ የበርካታ ኃያላን አገራት ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች ይገኙባታል።

አሜሪካ በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የጦር ሠፈሯ የሚገኘው በትንሿ ጂቡቲ ውስጥ ነው።

ጃፓንም ቢሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገሯ ውጪ የጦር ሠፈር ያቋቋመችው በጂቡቲ ነው።

ቻይናም እንዲሁ ከአገሯ ውጪ የጦር ሠፈር የከፈተቸው በጂቡቲ ነው። ጣልያን፣ ስፔን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይም የጦር ሠፈር አላቸው።

ጂቡቲ አጠቃላይ የአገሪቷን 70 በመቶ ገቢ የምታገኘው ወደብ በማከራየት ነው።

ተያያዥ ርዕሶች