ሆስፒታል የደረሱ ተጎጂዎች

ከ 6 ሰአት በፊት

“ስለቤተሰቡ ሲጠይቀኝ መልስ መስጠት አልችልም። በረዥሙ እተነፍስና ርዕሰ ጉዳዩን በመቀየር ጥያቄውን ለማረሳሳት እሞክራለሁ።”

የአራት ዓመቱ ኦማር በሕይወት የተረፈው ብቸኛ ዘመዱ የሆነው አጎቱ ሞኢን አቡ ሬዝክ ነው። ኦማርም ቢሆን በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ በዲር አል-ባላ በሚገኘው አል-አቅሳ ሆስፒታል ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ላይ ነው።

ኦማር ግራ እጁን መቆረጥ ነበረበት። በቀኝ እግሩ ላይ ትልቅ ቁስል አለ። ደረቱ እና ፊቱ ላይ ትናንሽ ቁስሎች አሉት። መንጋጋውም ጉዳት ደርሶበታል። እንደ ሞኢን ገለጻ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት የኦማር እናት፣ አባት እና አያቱን ጨምሮ 35 የቤተሰቡ አባላት ተገድለዋል።

ሞኢን እስካሁንም ለኦማር ስቤተሰቦቹ አሟሟት ላለመናገር ወስኗል። ዜናው ጤናውን ሊያቃውሰው ይችላል በሚል ስጋት ነው። ይህ ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግሥት እና በቀይ ጨረቃ አማካይነት ከጋዛ በግብፅ በኩል ለሕክምና ለመውጣት ያለውን ዕድል ያሰናክለዋል።

ሞኢን ለቢቢሲ አረብኛ ሲናገርም “እንዳይደነግጥ ወይም ወደማይችለው ሁኔታ እንዳይገባ ዜናው በጥንቃቄ ሊነገረው ይገባል” ብሏል።

“ሁሉንም እንዳላያቸው ያውቃል። ‘እናቴ የት አለች? አያቴስ የት ነው ያለችው? ወደ የት ሄዱ?” ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ይሰማዋል” ብሏል።

ማዕከላዊ ጋዛ በሚባለው አካባቢ ከፍተኛ ውጊያ እና የቦምብ ጥቃት ስለሚፈጸም ኦማርን በአምቡላንስ ወደ ግብፅ ድንበር ማጓጓዝ ዋስትና ያለው አይደለም።

እስራኤል 22 ሺህ ዒላማዎችን መምታቷን ገልጻለች

የእስራኤል የምድር ጦር ከሐማስ ጋር ባደረገው ጦርነት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ በመክበብ ጋዛን ለሁለት ከፍሏታል።

የአገሪቱ ታንኮች እና ወታደሮች ወደ ደቡባዊቷ ኻን ዩኒስ ከተማ እየገፉ ነው። ከዲር አል-በላህ ጋር የሚያገናኘው ዋናው አውራ ጎዳና “የጦር አውድማ” ተብሎ ተፈርጇል። ይህም በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ለመሸሽ ያላቸው ብቸኛ ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድ የሜዲትራኒያን ባሕር እንዲሆን አድርጓል።

በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖሩ በርካታ ፍልስጤማውያን ከሁለት ወራት በፊት ቤታቸውን ለቀው ከዋዲ ጋዛ ወንዝ በስተደቡብ እንዲሄዱ የእስራኤል ጦር ካዘዛቸው በኋላ ወደ ማዕከላዊ ጋዛ አቅንተው ተጠልለዋል።

ጦሩ ትዕዛዙን የሰጠው መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው በፈጸሙት ጥቃት አንድ ሺህ 200 ሰዎችን ገድለው 240 ገደማ ሰዎችን አግተው መውሰዳቸውን ተከትሎ መሰንዘር ከጀመረው ጥቃት በኋላ ነው።

እስራኤል እያካሄደችው ባለው ጥቃት ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ ሚመራው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። እስካሁን ጉዳት ከደረሰባቸው ከ49 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል አንዱ ኦማር ነው።

የእስራኤል ጦር አሸባሪዎችን ለማጥፋት፣ መሣሪያ እና የሽብር መሠረተ ልማቶችን ለማውደም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል። ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ከ22 ሺህ በላይ ዒላማዎች ተመተዋል ሲልም አክሏል።

ሞኢን ለቢቢሲ አረብኛ እንደተናገረው ኦማር እና ቤተሰቦቹ ከዲር አል ባላህ በስተሰሜን በሚገኘው ኑሴይራት መጠለያ ጣቢያ የሚገኙትን አያቱን ሲጎበኙ ነበር የእስራኤል ጦር ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የቦምብ ጥቃት ያደረሰባቸው።

“እንዲህ አይነት ሚሳኤሎች ከዚያ በፊት አይተን አናውቅም። ሚሳኤሉ ሲወድቅ በዙሪያው ያለውን የመኖሪያ አካባቢ በሙሉ አወደመ” ሲል አስታውሷል።

“እንደ ዕድል ሆኖ ቤቱ በነበረው ቀዳዳ ኦማር ወደቀ። የግራ እጁ በጣም በመጎዳቱ ወዲያውኑ መቆረጥ ነበረበት።”

“[ቅዳሜ ዕለት] ወደ 1 ነጥበ 5 ሊትር የሚጠጋ ደም ፈሰሰው። የሂሞግሎቢን መጠኑም ከ 9.5 ወደ 7.4 ዝቅ አለ። ስለዚህ የደም ዝውውር እንዲደረግለት ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል መዘዋወር ነበረበት።”

ሆስፒታሉ በጣም በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ጉዳቱ ከባድ ቢሆንም ሐኪሞች አልጋ ማግኘት ባለመቻላቸው፤ ዶክተሮች እና ነርሶች በቻሉት መጠን ኮሪደር ላይ ሕክምናውን እንዲያከናውኑለት አስገድዷቸዋል ሲል ሞኢን ገልጿል።

“የሁሉም የሕክምና መሳሪያዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆናቸው የተነሳ ከተለመደው መንገድ ውጪ ማስተናገድ ነበረብን።”

“የሕመም ማስታገሻዎች ስለሌሉ እሱን ለማረጋጋት እየቀለድን ልናስቀረው ሞክረናል።”

ይህ ዘዴ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሚሠራ የገለጸው ሞኢን ነገር ግን “ሌላ አማራጭ የለንም” ብሏል።

ኦማር ሐሙስ ዕለት በግብፅ ድንበር ወደሚገኘው የራፋህ ድንበር ማሻገሪያ ተወስዶ በመቀጠልም ለተሻለ ሕክምና ወደ ትልቅ ሆስፒታል እንደሚወሰድ ተስፋ አለው።

የጋዛ ተፈናቃዮች

ሊና ሻኮራ፣ ባለቤቷ እና ሦስት ልጆቿ ከእስራኤል የቦምብ ጥቃት እስካሁን በሕይወት ተርፈዋል። አሁንም ግን “በቅዠት ውስጥ” እየኖሩ መሆናቸውን ተናግራለች።

በጋዛ ከተማ ሼክ ራድዋን አውራጃ ከሚገኘው ቤታቸውን ሸሽተው በመውጣት ከዲር አል ባላህ ወጣ ብሎ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ከዘመዶቻቸው ጋር ተጠልለዋል።

“በየቀኑ ከእንቅልፌ የምነቃው ሰዎች እየተራቡ እና በጦርነት ላይ መሆናችንን እያስታወስኩ ነው። ከቤት መፈናቀል እና ምግብ ሳያገኙ መኖር ከባድ ነው” ስትል ሊና ለቢቢሲ አረብኛ ተናግራለች።

“እኔ እና ቤተሰቤ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ40 ግለሰቦች ጋር ተጠልለናል። በቦምብ ፍንዳታ ምክንያት ሁሉም መስኮቶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በመሠረቱ ከቤት ውጪ ተጠልለናል ማለት ይቀላል … በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑም ባለፈ ውርደትም ነው።”

ወንድ ልጆቿ ውሃ በማመላለስ ምክንያት የወገብ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በነዳጅ እጥረት ምክንያት ውሃ ማጣሪያው እና ፓምፑ ስለማይሠራ ውሃውም ንጹህ አይደለም።

ሱቆቹ ባዶ ስለሆኑ እና ምንም ዓይነት እርዳታ ባለማግኘታቸው የተበላሸ ምግብ ለመብላት መገደዳቸውን ተናግራለች።

“ትልቁ ተስፋችን ለመጋገር እንድንችል ዱቄት ማግኘት ነው። ዱቄቱ ቢገኝም መጋገር የምንችለው በማገዶ እንጨት ነው።”

“ሰዎች ያገኙትን እንጨት እየዞሩ ይሰበስባሉ። እንጨቱ የሚሰበሰበው በቦምብ ጥቃት ከደረሰበት አካባቢ በመሆኑ ዳቦው ሲጋገር ይበክለዋል” ትላለች።

የተባበሩት መንግሥታት እሑድ ዕለት እንዳስታወቀው በግብፅ ድንበር ላይ ከምትገኘው ራፋህ ከተማ ውጪ እርዳታ ማሰራጨት ያልቻለው በሚካሄደው ጦርነት እና የእንቅስቃሴ ገደቦች በመጣሉ ነው።