
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ከሐማስ ጋር እያደረገች ባለችው ጦርነት ዓለም አቀፍ ድጋፍ እያጣች ነው ሲሉ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህ እየሆነ ያለው እስራኤል ‘የጅምላ ቦምብ ጥቃት’ እየፈጸመች ስለሆነ ነው ብለዋል።
ባይደን ይህን ያሉት ማክሰኞ ዕለት በዋሺንግተን በተደረገ አንድ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ነው።
ይህ የጆ ባይደን አስተያየት ወዳጅ አገር በሚሏት እስራኤል ላይ የሰነዘሩት ብርቱው ትችት ተደርጎ ተወስዷል።
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ለእስራኤል ያላሰለሰ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች።
ባይደን አሁንም ቢሆን አገራቸውአሜሪካ እስራኤልን በማንኛውም ሁኔታና በማንኛውም ወቅት ከጎኗ እንደምትቆም ካረጋገጡ በኋላ ነው በቀጥታ ኂስ የሰነዘሩት።
“የእስራኤል ደኅንነት በአሜሪካ የሚደገፍ ነው። አሁን ግን ከአሜሪካም በላይ ነው። የአውሮፓ ኅብረት አለ። አብዛኛው ዓለምም እንዲሁ የእስራኤል ደጋፊ ነው” ሲሉ ከተናገሩ በኋላ “ነገር ግን ይህን ሰፊ ድጋፍ እስራኤል የጀምላ የቦምብ ጥቃት በማድረስ እያጣችው እየመጣች ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ጆ ባይደን በሐማስ ላይ የሚወሰደው እርምጃ በሙሉ ልብ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
እስራኤል ይህን ለማድረግ ሙሉ መብት እንዳላትም የሚያጠያይቅ እንዳልሆነ ገልጠዋል።
- በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ12 ታህሳስ 2023
- በአማራ ክልል መሀል ሳይንት ወረዳ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገደሉ12 ታህሳስ 2023
- ‘በኦንላይን’ ሥራ እንዴት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል? “በ9 ወር ሚሊየነር ሆኛለሁ” የሚለው ኢትዮጵያዊከ 6 ሰአት በፊት
የአሜሪካ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ጭምር ጫና በርትቶበታል። ጫናው የመጣው እስራኤል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በጀምላ እየወሰደች ያለውን እርምጃ አሜሪካ ለመግራት እንድትሞክር ነው።
የእስራኤል መከላከያ በሚወስዳቸው የጅምላ እርምጃዎች በርካታ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቅሬታ እንዳላቸው ተመላክቷል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር በዚህ ጦርነት ከ18ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻል። ይህ የሆነው ሐማስ ድንበር ጥሶ ባደረሰው መብረቃዊ ጥቃት 1ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ናታኒያሁ ትናንት ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ እስራኤል የአሜሪካንን ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዳገኘች ገልጸዋል። አሜሪካ ከዚህም አልፋ እስራኤል ላይ የነበረውን ዓለም አቀፍ ጫና እንደተከላከለች እውቅና ሰጥተዋል።
ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ እስራኤልና ፍልስጤም በምን መንገድ መቀጠል ይችላሉ የሚለው አሁን መወያያ እየሆነ መጥቷል።
ባይደን ‘’አሁን ያለው መንግሥት በእስራኤል ታሪክ ወግ አጥባቂ የሚባላው ነው። በሁለት ነጻ አገር ጽንሰ ሐሳብ የሚያምን አይደለም። ይህ ሁኔታዎችን ከባድ ያደርግብናል’’ ብለዋል።
ይህ የባይደን አስተያየት በእስራኤል ወግ አጥባቂ መንግሥትና በአሜሪካ መካከል እየሰፋ ያለውን ልዩነት ያጋለጠ ነው ተብሏል።
ናታኒያሁ በሰጡት መግለጫ ከጦርነቱ በኋላ ጋዛን የፍልስጤም አስተዳደር ተረክቦ እንዲያስተዳድር በባይደን የቀረበውን ሐሳብ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።