ሩሲያ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር የምትገነባበት የባሕር ዳርቻ  የሚያሳይ ምስል
የምስሉ መግለጫ,ሩሲያ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር የምትገነባበት የባሕር ዳርቻን የሚያሳይ ምስል

ከ 1 ሰአት በፊት

በአውሮፓ እና እስያ አማካይ ስፍራ ላይ የምትገኘው ጆርጂያ፤ ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ የጀመረችውን የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ግንባታዋን እንዲያስቆሙላት ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና ለአውሮፓ ኅብረት አቤቱታ አቀረበች።

በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ 50 የጆርጂያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኔቶ እና የአውሮፓ ኅብረት ሩሲያ ከጆርጂያ በተገነጠለችው የአብኻዚያ ግዛት ውስጥ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ለመመሥረት ማቀዷን በአንድ ድምጽ እንዲያወግዙ ጠይቀው ነበር።

የሩሲያ ዕቅድ የአውሮፓ ኅብረትን ለመቀላቀል ተስፋ ያደረገችውን ጆርጂያን ወደ ሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሊጎትት ይችላል ሚል ስጋት አሳድሯል። አገሪቱ በጥቁር ባሕር ላይ የራሷን ወደብ ለማቋቋም የያዘችውን ዕቅድም ሊያኮላሽ ይችላል።

የፓርላማ አባላቱ ባወጡት መግለጫ ሩሲያ የጆርጂያ ግዛትን በወረራ ለመያዝ ያላትን ዕቅድ እንዲሁም በቀጠናው የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እና ሌሎች ድርጊቶችን በአንድ ድምጽ እና በጽኑ እናወግዛለን ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት የአብኻዚያ ግዛት ይፋዊ ያልሆኑት መሪ አስላን ብዛኒያ የጥቁር ባሕር ወደብ በሆነችው ኦቻምቺር ላይ የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር ለመገንባት ከክሬምሊን ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን አረጋግጠው ነበር።

አብኻዚያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጆርጂያ አካል እንደሆነች ነው የሚታወቀው። ይሁን እንጂ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በሩሲያ እና በተገንጣዮቹ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ትገኛለች።

ምንም እንኳን የጆርጂያ ባለሥልጣናት የባሕር ኃይል ሰፈሩ በጆርጂያ ላይ የሚደቅነውን አደጋ ዝቅ አድርገው ቢገልጹም፤ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሩሲያን ዕቅድ “የጆርጂያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጥስ ነው” ሲል አውግዞታል።

የጆርጂያ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ኃላፊ ኒኮሎዝ ሳምካራዴዝ ሩሲያ “በኦቻምቺር የባሕር ኃይል ጦር ሰፈሩን ገንብታ ለመጨረስ ቢያንስ ሦስት ዓመታት ይፈጅባታል” በማለት ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ የመንግሥታቸው ትኩረት “በቅርቡ በሚኖረው ስጋት ላይ እንጂ ወደፊት ሊመጡ በሚችሉት ላይ አይደለም” ሲሉ አክለዋል።

ከጆርጂያ ከተገነጠለችው አብኻዚያ ድንበር አቅራቢያ በጆርጂያ ዜጎች ላይ በሚፈጸሙት ግድያዎች እና እገታዎች ላይ መንግሥት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በወደቡ ላይ አዲስ የውሃ አካልን ጨምሮ ሌሎች የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ቢቢሲ ከሳተላይት ምስሎች ማረጋገጥ ችሏል።

የአብኻዚያ አስተዳደር እንደገለጸው፣ በአዲሱ ግንባታ ኦቻምቺር ወደብ ግዙፍ የጭነት መርከቦችን ማስተናገድ ይችላል።

የዩክሬን የስለላ ድርጅት በበኩሉ የግንባታው ዓላማ በጥቁር ባሕር የሚገኙ የሩሲያ የጦር መርከቦች ኦቻምቺርን እንደ ወደብ እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው ይላል።

የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ናቲያ ሴስኩሪያ፤ ሩሲያ ኦቻምቺርን ተጠቅማ ዩክሬንን ብታጠቃ ወይም ዩክሬን በወደቡ የሚገኙ የሩሲያ የባሕር ኃይል መርከቦችን ዒላማ ለማድረግ ብትወስን ጆርጂያ የጦርነቱ አካል ትሆናለች ይላሉ።

“ፑቲን ጆርጂያ በጦርነቱ እንድትሳተፍ ወይም ይህ ጦርነት እንዲጓተት ከፈለገ ያደርገዋል። በዚህም በሚያሳዝን ሁኔታ በጆርጂያ ላይ ጫና ለመፍጠርም አቅም ይኖረዋል” ብለዋል።

ይህ የሩሲያ እርምጃ ጆርጂያን ጦርነት ውስጥ ይከታል ከሚለው ስጋት በተጨማሪ፤ አገሪቱ በጥቁር ባሕር ላይ ለመገንባት ያቀደችውን ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሊያደናቀፍ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

አናክሊያ በሩሲያ ቁጥጥር ስር በምትገኘው አብኻዚያ አቅራቢያ ያለች የጆርጂያ ከተማ ናት።

በእስያ እና በአውሮፓ መካከል በፍጥነት ጭነት ለማመላለስ የሚያስችለው አካባቢ የታቀደው የአናክሊያ ፕሮጀክት ንግድን ለማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ ይነገርለታል።

አናክሊያ ፕሮጀክት
የምስሉ መግለጫ,አናክሊያ ፕሮጀክት

ፕሮጀክቱ እውን ቢሆን በሩሲያ በኩል ሳያልፍ በቀጠናው የሚደረግ የንግድ ልውውጥን በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል የዓለም ባንክ ይገምታል።

ክሬምሊን የአሜሪካ ፕሮጀክት ነው በማለት ለረዥም ጊዜ ስትቃወም የቆች ሲሆን፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭም የአሜሪካ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ወደቡን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ጆርጂያ ወደ አውሮፓ ኅብረት የሚያዘነብል ሕዝብ ቢኖራትም፣ የአገሪቱ መንግሥት ግን ከሞስኮ ጋር ያለው ግንኙነት ውስብስብ የሚባል ነው።

የጆርጂያ መንግሥት እአአ በ2020 በምዕራባውያን ባንኮች እና ባለሀብቶች ለሚደገፈው ጥምረት የተሰጠውን የባሕር ወደብ ግንባታ ውል ሰረዟል።

የአናክሊያ ዲቨሎፕመንት ኮንሰርቲየምን የመሩት ማሙካ ካዛራዴዝ እንደተናገሩት በጆርጂያ የሚገኘው መንግሥት ሞስኮን ለማስደሰት በሚል የወደብ ልማቱን ውድቅ አድርጎታል።

“ከዚህ መንግሥት ጋር ያለን ትልቁ ችግር የሩሲያን ጥቅም እያስከበሩ ነው። ምክንያቱም በአናክሊያ በሚገነባው ፕሮጀክት ላይ ሩሲያ ፍላጎት የላትም።”

የጆርጂያ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኒኮሎዝ ሳምሃራዴዝ በበኩላቸው መንግሥታቸው የሩሲያ ደጋፊ ነው የሚባለውን ውንጀላ “ውሃ የማያነሳ” ብለውታል።

“እንዴት ሆኖ ነው የሩሲያ ደጋፊ የሆነ መንግሥት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ለመሥራት ስምምነት የሚፈራረመው? . . . ለአውሮፓ ኅብረት ዕጩ ሆኖ መቅረብ የሚችለው?” ሲሉ ሳምሃራዴዝ ጠይቀዋል።

ጆርጂያ በሰሜን አቅጣጫ ከምትገኘው ጎረቤቷ ጋር ያላትን ግንኙነት በጥንቃቄ ለማስኬድ ትገደዳለች ብለዋል።

“ባለፉት 30 ዓመታት ከሩሲያ ጋር ሦስት ጦርነቶችን አድርገናል። የኔቶ የደኅንነት ጥበቃ የለንም። የአውሮፓ ኅብረት የኢኮኖሚ ትብብር የለንም።”

ጆርጂያን ወደ አውሮፓ ኅብረት ለመግባት ያላትን ፍላጎት ለማኮላሸት ሩሲያ ኦቻምቺርን እየተጠቀመች እንደሆነም ጠቁመዋል።

ጆርጂያ የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን ባቀረበችው ጥያቄ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የአውሮፓ መሪዎች በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል።