ካትሊን ፎልቢግ

ከ 5 ሰአት በፊት

አራት ልጆቿን ገድለሻል ተብላ ለ20 ዓመታት የታሰረችው አውስትራሊያዊት እናት ከወንጀሉ ነጻ ናት ተባለ።

ከጨቅላዎቹ ሞት ጋር ተያይዞ ‘የአውስትራሊያ ክፉ እናት’ የሚል ስያሜ የተሰጣትን ግለሰብ ፍርድ ቤት ከወንጀሉ ነጻ አድርጎ አሰናብቷታል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ካትሊን ፎልቢግን የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስበየነባት ማስረጃዎች “ የሚታመኑ አይደሉም” ሲልም ነው ሐሙስ እለት የወሰነው።

የ56 አመቷ እናት 20 ዓመታትን በእስር ካሳለፈችም በኋላ እንድትፈታም ተወስኗል።

ካትሊን ከወንጀሉ ነጻ የመደረጓን ዜና በደስታ ብትቀበለውም ነገር ግን ንጽህናዋን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ለሁለት አስርት ዓመታት ቸል እንደተባሉ እና እንደተተው አስረድታለች።

“ስርዓቱ አንዳንድ ጊዜ ህጻናት በድንገት፣ ባልተጠበቀ እና ልብ በሚሰብር ሁኔታ ሊሞቱ እንደሚችሉ ከመቀበል ይልቅ እኔን መወንጀል መርጧል” ስትልም ሐሙስ እለት ከፍርድ ቤቱ ውጪ ተናግራለች።

የካትሊን የእስር ጉዳይ በአውስትራሊያ ከባዱ የፍትህ ስርዓት መዛባት የታየበትም ነው ተብሏል።

የካትሊን አራት ጨቅላዎች ካሌብ፣ ፓትሪክ፣ ሳውራ እና ላውራ በአውሮፓውያኑ 1989 እስከ 1999 ባለው ጊዜ ህይወታቸው በድንገት ነው ያለፈው ። ህጻናቱ ከ19 ቀን እስከ 18 ወራት የሚቆጠር ዕድሜ ነበራቸው ተብሏል። በወቅቱ የከሰሷት አቃብያነ ህግ አፍና ገድላቸዋል የሚል ክስም ነው ያቀረቡት።

እንደ አንድ ማስረጃ ከቀረቡት መካከል የካትሊን ዲያሪ (ማስታወሻ) ላይ ያሰፈረቻቸው ጉዳዮች ሲሆን ግለሰቧ፣ ያልተረጋጋች እና ከፍተኛ ቁጣ ያለባት እንደሆነም ለማሳየት መቅረቡም ተገልጿል። ማስታወሻው በስነ ልቦና ባለሙያዎች ወይም በሳይካትሪስቶችም አልተፈተሸም።

ህጻናቱንም ገድለሻል ተብላም የ40 ዓመታት እስር የተፈረደባት በአውሮፓውያኑ 2003 ነበር።

ካትሊን ይግባኝ በማለቷ የእስር ቅጣቷ ወደ 30 ዓመት ዝቅ ቢደረግም ክሱ ውድቅ እንዲደረግላት ያቀረበችው ተቀባይነት አላገኘም ነበር።

ነገር ግን በቅርቡ በጉዳዩ ላይ በተደረገ አንድ አስደናቂ ጥናት ልጆቿ በተፈጥሮ ምክንያቶች ሊሞቱ እንደሚችሉ ይፋ ሆኗል። ሳይንሳዊ ግኝቱም ልጆቹም ብዙም ባልተለመደ የዘረ መል ለውጥ (ጂን ሚውቴሽን) ጋር በተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ምክንያቶች አግኝቻለሁ ብሏል። በዚህ ግኝት ምክንያት ግለሰቧ ከተከሰሰችባቸው ወንጀሎች ሙሉ በሙሉ ነጻ እንድትሆን ተደርጋለች።

የካትሊን ጠበቆች በበኩላቸው ግለሰቧ ለታሰረችባቸው አመታት ካሳ እንጠይቃለን ብለዋል።

ጉዳዩ የዓለምን ትኩረት የሳበ እና የአውስትራሊያ የፍትህ ስርዓት በሳይንስ ላይ ያለውን ክፍተት ያሳየ ነው የሚም ውንጀላ ቀርቦበታል።