
ከ 5 ሰአት በፊት
ሁለት አሜሪካውያን 3,600 የሚደርሱ አእዋፍ በመግደል ተጠርጥረው ተከሰሱ።
ከአእዋፉ መካከል ንስሮች ይገኙበታል።
ሳይመን ፖል እና ትራቪስ ጆን ብራንሰን የተባሉት ተከሳሾች በዓመታት ውስጥ አእዋፉን በሽጉጥ በመግደል የሰውነት ክፍላቸውን በጥቁር ገበያ በመሸጥ ነው ክስ የተመሠረተባቸው።
በመመሳጠር፣ የንስር ጥበቃ ሕግ በመተላለፍና በሕገ ወጥ ዝውውር ተከሰዋል።
በጥር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡም ተወስኗል።
አእዋፉን የገደሉት ፍላትላንድ ኢንዲያን ሪዘርቬሸን በተባለ ጥብቅ የተፈጥሮ ስፍራና በሌሎች አካባቢዎችም ነው።
ከተከሳሾቹ አንዱ “ወንጀል ስለመሥራት” እና “ግድያ ስለመፈጸም” እንዲሁም “ከፍተኛ ገንዘብ ስለማግኘት” ለሚያውቃቸው ሰዎች መልዕክት መላኩም ተገልጿል።
በ13 የተለያዩ አጋጣሚዎች የንስሮች መብት ጥበቃ መርህ በጣሱ ተገልጿል።
የተቀሩት አእዋፍ ዝርያቸው እንዲሁም ለመጥፋት የተቃረቡ ስለመሆናቸው የተባለ ነገር የለም።
የ48 ዓመቱ ተከሳሽ ትራቪስ በዋሽንግትን ሲኖር፣ የ42 ዓመቱ ሳይመን በሞንታና ነው የሚኖረው።
- የአቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ተናገሩከ 6 ሰአት በፊት
- “በአፍሪካ የራሱ የጣት ምልክት ያለው የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ”ከ 6 ሰአት በፊት
- በትግራይ የተከሰተው ድርቅ ከ77ቱ የከፋ ነው ሲሉ የክልሉ ባለሥልጣን ተናገሩ13 ታህሳስ 2023
ተከሳቹ አስተያየታቸውን አልሰጡም። የሚወክሏቸው ጠበቆችም በዐቃቤ ሕግ ይፋ አልተደረጉም።
ንስር የአሜሪካ ብሔራዊ ወፍ ሲሆን፣ በአሜሪካ ሳንቲም ላይም ይገኛል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው አንዱ ነው።
ዋነኛ ምክንያቱም አደንና መኖሪያ ቦታ ማጣት ነው።
ንስሮች እንቁላል እንዳይጥሉ የሚያደርገው ተባይ ማጥፊያ ዲዲቲ ለህልውናቸው አደጋ ስለሆነ እአአ በ1972 ጥቅም ላይ እንዳይውል ታግዷል።
የአሜሪካ የዓሣና ዱር እንስሳት ጥበቃ እንደሚለው 1963 ላይ ንስሮች እንቁላል የሚጥሉባቸው 417 ስፍራዎች ብቻ ነበሩ።
ጥበቃ ከተደረገላቸው ወዲህ ቁጥሩን ከፍ ማድረግ ተችሏል። ለአደጋ ከተጋለጡ ዝርዝርም ወጥተዋል።
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የቀረበባቸው ክስ እስከ አምስት ዓመት እስር ያስከትላል።