መኪና እየነዳች ያለች ግለሰብ

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ተቆጣጣሪው ባለስልጣን የቴስላ መኪናዎች የአሽከርካሪ ደጋፊ ስርዓቱ በከፊል ጉድለት እንዳለበት ማረጋገጡን ተከትሎ ኩባንያው ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለተሸጡ መኪኖች ጥሪ አድርጓል።

ከዚህ ውሳኔ የተደረሰው ቴክኖሎጂው ሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት የተከሰቱ አደጋዎች ላይ ለሁለት አመት ምርመራን መደረጉን ተከትሎ ነው።

ጥሪው እአአ በ2015 ‘የአውቶፓይሎት’ ቴክኖሎጂ ከተጀመረበት ወዲህ ተመርተው ለአሜሪካ ገበያ የቀረቡ ቴስላ መኪናዎችን ይመለከታል።

የቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ንብረት የሆነው ቴስላ ችግሩን ለማስተካከል የመተግበሪያ (ሶፍትዌር) ማሻሻያም እንደሚያደርግላቸውም አስታውቋል። ሶፍትዌሩም ለመኪኖቹ ባለቤት እንደሚላክላቸውም ተነግሯል።

የመኪኖቹ ባለቤቶች የመኪናዎቹን መተግበሪያ (ሶፍትዌር) ማሻሻያም እንዲኖራቸው ወደ መሸጫ ሱቆች ወይም ጋራዥ መሄድ አያስፈልጋቸውም። ሶፍትዌሩ እንደተላከላቸው መኪኖቹ ወዲያውኑ ራሳቸውን በአዲሱ ያሻሽሉታል።

የዩናይትድ ኪንግደም የአሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ደረጃዎች ኤጀንሲ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቴስላን በተመለከተ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት ማጋጠሙን እንደማያውቅ ገልጿል።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚሸጡ መኪኖች አሜሪካ ገበያ ላይ ከቀረቡት ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ አይደሉም ሲል አክሏል።

“በዩኬ ገበያ የሚሸጠው ቴስላ በራሱ የሚሸከረከር አይደለም። ይህ ቴክኖሎጂም አልተፈቀደለትም” ሲሉ የኤጀንሲው ቃል አቀባይ መስሪያ ቤታቸው ሁኔታውን እንደሚከታተል ተናግረዋል።

‘አውቶፓይለት’ በማሽከርከር፣ ፍጥነት በመቆጣጠር እና ፍሬን ለመያዝ ታስቦ የተሠራ ቴክኖሎጂ ነው። መኪናው በራሱ የሚንቀሳቀስ ቢባልም አሽከርካሪዎችን ግን ይፈልጋል።

የቴስላ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) አሽከርካሪዎች ትኩረታቸውን እንዳይነቅሉ የሚጠይቅ ሲሆን ቴክኖሎጂውም ውጤታማ የሚሆነው ተገቢው ሁኔታ ሲመቻችላቸው መሆኑ ታውቋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የትራፊክ ደህንነት አስተዳደር በ956 የቴስላ አደጋዎች ላይ ለሁለት ዓመታት ባደረገው ምርመራ “ሶፍትዌሩ የአሽከርካሪዎችን አላግባብ አጠቃቀምን ለመከላከል በቂ ላይሆን ይችላል” ብሏል።

“አሽከርካሪ አልባ ቴክኖሎጂ ደህንነትን ለማሻሻል ትልቅ ተስፋ ቢሰጥም ይህ የሚሆነው በኃላፊነት ሲሠራ ብቻ ነው” ሲል አክሏል።

ቴስላ በጉዳዩ ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

በጥሪው መሠረት ኩባንያው ከኤጀንሲው ትንታኔ ጋር ባይስማማም ስጋቶቹን ለመቅረፍ አዳዲስ አሰራሮችን ለመጨመር ተስማምቷል።

ጥሪ የተላለፈው የቴስላ የቀድሞ ሠራተኛ ቴክኖሎጂው ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም ብሎ ለቢቢሲ ከተናገረ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

ሉካስ ክሩፕስኪ የብሉፕሪንት ሽልማትን ካሸነፈ በኋላ ለቢቢሲ “ሃርድዌሩ እና ሶፍትዌሩ ዝግጁ ነው ብዬ አላምንም” ብሏል።

“ሁላችንንም ይነካል ምክንያቱም በሕዝብ መንገዶች ላይ ሙከራዎች እየተከናወኑ ነው” ብሏል ።

ኩባንያው መኪናዎቹን መጥራቱን በተመለከተ ክሩፕስኪ ለቢቢሲ እንደተናገረው “ትክክለኛ እርምጃ ነው” ነገር ግን ይህ አሜሪካ ውስጥ ብቻ ያለ ችግር አይደለም ብሏል።

“ዋናው አካሉ አሜሪካም ሆነ ቻይና ሁሉም ጋር ተመሳሳይ ነው።”

የደህንነት መለኪያዎች

ቴስላ ማክሰኞ ዕለት ለዋሽንግተን ፖስት ጽሁፍ ምላሽ በኤክስ ላይ በሰጠው ምላሸስ “የአውቶ ፓይለትን” ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ሲል ተከላክሏል።

“የደህንነት መጠበቂያዎች አውቶ ፓይለት ሲሠማራ የበለጠ ጠንካራ ይሆናል” ሲል ጽፏል።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጃክ ስቲልጎ ቴስላ ስርዓቱን በማዳበር ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ነበረበት ብለዋል።

“የተለመደው ደህንነትን የማረጋገጫ መንገድ መኪናው ከፋብሪካ ከመውጣቱ በፊት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።