የእስራኤል ወታደሮች

ከ 5 ሰአት በፊት

የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃገራቸው “ዓለም አቀፍ ድጋፍ ብታገኝም ባታገኝም” የጋዛ ጦርነት እንደምትገፋበት ተናገሩ።

ጦርነቱ ባለበት ደረጃ የተኩስ አቁም ማለት ለሐማስ “ስጦታ” ነው ብለዋል ሚኒስትሩ ኢላይ ኮኸን።

በርካታ ሰላማዊ ፍልስጤማዊያን በጦርነቱ ምክንያት መገደላቸውን እንዲሁም በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ማሻቀቡን ተከትሎ እስራኤል ጫና እያደረባት ነው።

ማክሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግሥት ጠቅላይ ጉባዔ በፍጥነት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበው ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ አልፏል።

አልፎም ጠንከር ያለ ንግግር ያሰሙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እስራኤል “ጋዛ ላይ ባደረሰችው ጅምላ የቦምብ ጥቃት ምክንያት” በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ያላትን ድጋፍ እያጣች ነው ብለዋል።

ረቡዕ፤ በሰሜን እና ደቡብ ጋዛ ያለው ከባድ ጦርነት የቀጠለ ሲሆን ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን እየወረደ ባለው ዶፍ ዝናብ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ላይ ናቸው።

አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን የፍልስጤም ግዛት ያለው የጤና አገልግሎት በመውደሙ ምክንያት ተላላፊ በሽታዎች እየተዛመቱ ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ “የጤና ቀውስ” ሊከተል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ሳይጠበቅ ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎችን ከገደለ በኋላ 240 ሰዎችን አግቶ በመውሰዱ ነው ይህ ጦርነት የተቀሰቀሰው።

ከጦርነቱ መጀመር በኋላ 18600 ሰዎች ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል። ከተገደሉት ፍልስጤማዊያን መካከል 70 በመቶው ሴቶችና ሕፃናት ናቸው ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ይገልጣል።

ማክሰኞ በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ 153 አባል ሃገራት አስገዳጅ ያልሆነውን ረቂቅ የተኩስ አቁም ሐሳብ ደግፈውታል።

ስምንት ሃገራት ደግሞ እስራኤል እና አሜሪካን ተከትለው የተኩስ አቁም መደረግ የለበትም ሲሉ የተቃውሞ ድምፅ አሰምተዋል።

ኦስትሪያ፣ ቼክ ሪብሊክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀመርን ድምፀ ተዐቅቦን ከመረጡ 23 ሃገራት መካከል ናቸው።

ባለፈው አርብ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አስገዳጅ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረግ አለበት ሲል ያቀረበውን ሐሳብ አሜሪካ ሐማስ “ተመልሶ እንዲደራጅ” ያደርጋል ስትል ድምፅን በድምፅ የመሻር ኃይሏን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋዋለች።

ጠቅላላ ጉባዔው ካቀረበው ሐሳብ እና ባይደን ካሰሙት ማስጠንቀቂያ በኋላ ነው የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “እስራኤል ዓለም አቀፍ ድጋፍ ብታገኝም ባታገኝም ጦርነቱን ትቀጥለዋለች” ያሉት።

“አሁን ተኩስ አቁም ማድረግ ለአሸባሪው ሐማስ ስጦታ ነው። ተመልሶ መጥቶ የእስራኤል ነዋሪዎችን እንዲያሸብር መፍቀድ ነው” ማለታቸውን ቢሯቸው ያወጣው መግለጫ ያትታል።

ምንም እንኳ አሜሪካ እስካሁን የእስራልን ሐሳብ ብትደግፍም አንዳንድ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እስራኤል እያደረሰች ያለውን ጥቃት እየተቃወሙት እንደሆነ ተሰምቷል።

በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2 የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን፤ እስራኤል ሰላማዊ ጋዛዊያንን ካልጠበቀች “ታክቲካዊ ድል አምጥታ ስትራቴጂክ ሽንፈት ልታስተናግድ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሐሙስ ወደ እስራኤል አቅንተው የእስራኤሉ ፕሬዝደንት ቤኒያሚን ኔታኒያሁን ያናግራሉ።

ኔታኒያሁ ማክሰኞ ከወታደራዊ አዛዦቻቸው ጋር ባደረጉት ንግግር “ጦርነቱ እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፤ ድል እስክናገኝ ድረስ፤ ሐማስ እስኪጠፋ ድረስ” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ጫናን በተመለከት ደግሞ “ማንም ሊያስቆመን አይችልም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

እስራኤል በጋዛ የምታደርሰውን ጥቃት ብትቀጥልም ሐማስ እና አጋሮቹ ጦርነቱን ቀጥለውበታል። ማክሰኞ 10 እስራኤላዊያን ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን የምድር ጥቃት ከተጀመረ በኋላ ትልቁ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመለክተው 360 ሺህ ገደማ ፍልስጤማዊያን እንደ ሜኒንጃይተስና እና ለበርካታ ሕፃናት ሞት ምክንያት የሆነው ተቅማጥ ላሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋልጠዋል።