
ከ 2 ሰአት በፊት
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም አይኦኤም ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያንን ከሰንዓ ወደ አዲስ አበባ ማምጣት መጀመሩን ገለጠ።
የፈቃደኛ ሰብዓዊ ተመላሾች ፕሮግራም ብሎ የጠራው ይህ በረራ ካለፈው መስከረም በኋላ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ 118 ሰዎችን ያሳፈረው በረራ ሰኞ ዕለት ወደ አዲስ አበባ ያመራ ሲሆን በሺዎች ለሚቆጠሩ የመን ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ ያጭራል ተብሏል።
ድርጅቱ በድረ-ገፁ በለለቀው ዘገባ የመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መሠረታዊ የሚባሉ እንደ ምግብ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት ተነፍጓቸው ነው የቆዩት ብሏል።
ዘገባው አክሎ ኢትዮጵያዊያኑ ለጉልበት ብዝበዛ ከመጋለጣቸውም ባለፈው የመን ባለው ግጭት እና በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ምክንያት ሕይወታቸው የከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
የድርጅቱ የየመን ጊዜያዊ ተጠሪ ማት ሁበር “ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የተጋላጭ ስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ አለበት” ብለዋል።
ኃላፊው አክለው “ምንም እንኳ በኢትዮጵያም ሆነ በየመን ፈቃደኛ ተመላሾአችን ለማጓጓዝ በቂ አቅርቦት ባይኖርም የሰኞው በረራ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻው አይሆንም።”
አይኦኤም እንደሚለው ካለፈው ጥር እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ 95 ሺህ ገደማ ስደተኞች ወደ የመን ገብተዋል።
ይህ ቁጥር ካለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2022 ጋር ሲነፃፀር እጅግ የገዘፈ ነው። ባለፈው ዓመት ወደ የመን የገቡ ስደተኞች ቁጥር 70 ሺህ ነበር።
ድርጅቱ ጨምሮ ከምስራቅ አፍሪካ እና ከአፍሪካ ቀንድ የመጡ 200 ሺህ ያክል ስደተኞች ፈጣን ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚሹ አሳውቋል።
በአካባቢው ባለው ግጭት ምክንያት በየመን ያሉ ስደተኞች የሚያስፈልጋቸውን ሰብዓዊ እርዳታ በአፋጣኝ ለመመለስ የተራድዖ ድርጅቶች እንደተቸገሩ አይኦኤም ዘግቧል።
- የአቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ተናገሩከ 6 ሰአት በፊት
- በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ12 ታህሳስ 2023
- በትግራይ የተከሰተው ድርቅ ከ77ቱ የከፋ ነው ሲሉ የክልሉ ባለሥልጣን ተናገሩ13 ታህሳስ 2023
ሃያት እና መንታ ልጆቿ
የ29 ዓመቷ ሃያት እና መንታ ልጆቿ ወደ አዲስ አበባ ከገቡ ተመላሾች መካከል ናቸው።
ሃያት፤ ከሁለት ዓመት በፊት ነው ጫካ እና በረሃ አቆራርጣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በስደት ወደ የመን ያቀናችው።
“ከስድስት ወራት በፊት እርዳታ ፈልጌ ልጆቼን ይዤ ወደ ሰንዓ አቀናሁ” የምትለው ሃያት “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦቼ ጋር የምገናኝበትን ቀን ስናፍቅ ቆይቻለሁ” ስትል ያሳለፈችውን ታስረዳለች።
ፈቃደኛ ተመላሾች የሚመለሰቡት በረራ በየመን ለሚገኙ በርካታ ስደተኞች ከብዙ መከራ የሚወጡበት ቀዳዳ ነው።
ይህ ፕሮግራም መሠረታዊ አቅርቦቶችን አሟልቶ፤ ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ነው።
ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ አስፈላጊ እርዳታ የሚደርግላቸው ሲሆን ወደሚሹት ቦታ የሚያደርስ ትራንስፖርት፣ የሕክምና አገልግሎት፣ የአእምሮ ጤና ማማከር እና ቤተሰብ ማፈላለግ ይጠቀሳሉ።
ይህ ፕሮግራም ከመቋረጡ በፊት የመን የነበሩ ከ6 ሺህ በላይ ስደተኞች ከሰንዓ እና ኤደን አየር ማረፊያዎች ተነስተው ኢትዮጵያ ገብተዋል።