
14 ታህሳስ 2023, 18:07 EAT
ተሻሽሏል 14 ታህሳስ 2023, 18:07 EAT
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኧርቪን ማሲንጋ ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ ኮሚሽኑ በድረ-ገጹ ላይ ያወጣው መረጃ “ስህተት” በመሆኑ ከገጾቹ ላይ ማንሳቱን ለቢቢሲ ገለጸ።
ኮሚሽኑ በድረ ገጹ እና የማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ የወጣውን መረጃ በተመለከተ “ኃላፊነት በጎደለው መልኩ” መረጃውን አሰራጭተዋል ያላቸውን የኮሚሽኑን የሥራ ኃላፊ ከሥራ አግዶ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ማስተባበያ የሰጠበት ይህንን መረጃ በድረ-ገጽ እና ማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ ያወጣው ሰኞ ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ነበር። ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ እና የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያደረጉትን ውይይት የተመለከተው ይህ መረጃ፤ በውይይቱ “ተነስተዋል” የተባሉ ጥያቄዎች እና ምላሾችን የያዘ ነበር።
በትግራይ እና በአማራ ክልል ጉብኝት አድርገው የነበሩት አሜሪካው አምባሳደር፤ በትግራይ ክልል ውስጥ ይገኛል የተባለውን የኤርትራ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ የተነሱ ስጋቶችን እንዳነሱ በኮሚሽኑ መረጃ ላይ ተጠቅሶ ነበር።
ኮሚሽነሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፤ ከአሜሪካው አምባሳደር ለተነሱ ጥያቄዎች “ሰጥተዋቸዋል” የተባሉ ምላሾችም በስፋት በኮሚሽኑ ድረ-ገጽ ላይ ወጥቶ ነበር።
ቢቢሲ በኮሚሽኑ ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ የወጣውን መረጃ መሠረት በማድረግ በዕለቱ ዘገባ አቅርቦ ነበር። በዕለቱ ዘገባው ከመውጣቱ በፊት በጉዳዩ ላይ የአምባሳደር ተሾመን አስተያየት ለማካተት ጥረት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ኮሚሽነሩ “ቲዊተር ላይ” ከወጣው ውጪ ተጨማሪ መረጃ አለመኖሩን ለቢቢሲ በስልክ በመናገራቸው አስተያየታቸው በዘገባው ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል።
- የፋኖ ኃይል በአንድ ዕዝ ሥር አለመሆን ከመንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር እንቅፋት መሆኑን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ11 ታህሳስ 2023
- “በአፍሪካ የራሱ የጣት ምልክት ያለው የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ”14 ታህሳስ 2023
- ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያንን ከየመን ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ጀመረ14 ታህሳስ 2023
ይሁንና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 4/2016 ዓ.ም. ለቢቢሲ በላከወ ደብዳቤ አምባሳደር ተሾመ እና አምባሳደር ኧርቪን ውይይት ያደረጉት የአሜሪካ መንግሥት የኮሚሽኑን ሥራዎች ለመደገፍ ሊያደርግ የሚችለውን ድጋፍ እና ትብብር የተመለከተ መሆኑን አስታውቋል።
ስለዚህም ይህንን መረጃ አስመልክቶ ከቀናት በፊት በኮሚሽኑ የተለያዩ ገጾች ላይ የወጣው መረጃ ትክክለኛ አለመሆኑን እና እንዲነሳ መደረጉን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ በደብዳቤው፤ “በተቋማችን ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ዌብ ሳይት ላይ በኮሚዩኒኬሽን ክፍላችን በኩል የተሰራጨው መረጃ የተቋሙን አሠራር የጣሰ፣ ከውይይቱ አውድ የወጣ፣ ከተቋማችን ተልዕኮ ጋር የማይገናኝ እና በውይይቱ ያልተነሱ መረጃዎች ጭምር የተካተቱበት ነው” ብሏል።
በዕለቱ በወጣው መረጃ የተሰራጨው “ከተቋሙ አመራር እውቅና ውጪ” መሆኑን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ መረጃው ከሁሉም የመሥሪያ ቤቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች እና ድረ-ገጽ እንዲወርድ ማድረጉንም ገልጿል።
ቢቢሲ ውይይቱን አስመልክቶ ለአምባሳደር ተሾመ ጥያቄ ባቀረበበት ወቅት ኮሚሽኑ በተቋሙ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ስለወጣው መረጃ እንደማያውቁ የኮሚሽነሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻንቆ ደለለኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በድረ-ገጹ ላይ የወጣው መረጃ የተቋሙን “የኮሚዩኒኬሽን አሰራር እና መርሆዎች” የሚጥስ መሆኑን በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። ኮሚሽኑ አክሎም፤ “ይህን የተሳሳተ መረጃ ኃፊነት በጎደለው መልኩ ያሰራጩት እና በዚህ የተሳሳተ መረጃ በተቋሙ ገጽታ፣ አመኔታ እና ቀጣይ ግንኙነቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕእኖ እንዲያድር ያደረጉ የሥራ ኃላፊም ከሥራ ታግደው ጉዳዩ እየተጣራ ይገኛል” በማለት ጉዳዩን አስመልክቶ የወሰደውን እርምጃ ገልጿል።
ስለዚህም ስህተቱ የተከሰተው የኮሚሽኑን ይፋዊ ገጾች ጠቅሶ እና ከኮሚሽነሩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሞክሮ ቢቢሲ ባቀረበው ዘገባ ላይ እንዳልሆነ የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሃድሶ መልሶ በማቋቋም በአገሪቱ ሰላም እና ልማት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሁም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ዓላማን ይዞ ባለፈው ዓመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።
ይህንንም ዓለማውን ለማሳካት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው እና ከተለያዩ አገራት እና ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል።