በቅርቡ ሴት ልጅ በጋዛ የወለደችው ጁማና ኢማድ
የምስሉ መግለጫ,በቅርቡ ሴት ልጅ በጋዛ የወለደችው ጁማና ኢማድ

ከ 6 ሰአት በፊት

ከአንድ ወር በፊት የጋዛ ነዋሪዋ ጁማና ኢማድ የእርግዝናዋ የመጨረሻ ጊዜ ላይ ነበረች። ረጅሙን እና ከባዱን ጉዞ አልፋ ልጇን ለመታቀፍ ተቃርባለች። ጉጉቷም ጨምሯል።

የመውለጃ ቀኗ እየተቃረበ ሲሄድ ብዙ ፎቶዎችን በደስታ ውስጥ ሆና ለሌሎች እያጋራች የወሊድ ዝግጅቷን እያደረገች ነበር።

በሆዷ ውስጥ ሴት ልጅ እንደነበረች አውቃለች። በዚህም ባለቤቷ እጅግ ደስተኛ ነበር። የመጀመሪያዋ እና የአራት ዓመት ልጃቸው ቱሊም ከእህቷ ጋር እስክትገናኝ ቸኩላለች። ቤተሰቡም አዲሷን ልጅ ለማየት ቀን እየቆጠረ ነው።

ብዙም ሳይቆይ ይህ ተስፋ እና ደስታ ወደ ስጋት ተቀየረ።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባ ከፈተ።

በዚህ ግጭት ሐማስ 1400 ሰዎችን እንገደለ እና ከ200 በላይ ሰዎችን እንዳገተ ሲነገር፣ እስራኤል ደግሞ ከ16 ሺህ በላይ ሰዎችን ገድላለች።

በዚህ ጊዜ ለመውለድ የተቃረበችው ጁማና ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ ገባች።

“በጣም ፈርቼ ነበር። ተከታታይ የአየር ጥቃት ሲፈጸም ምጥ ውስጥ ነበርኩ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የ25 ዓመቷ ጋዜጠኛ የእስራኤልን ‘ከደቡብ ጋዛ ውጡ’ የሚል ትዕዛዝ ተከትሎ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ሸሽታለች። የእስራኤል ጥቃት ተጠናክሮ እስኪቀጥል እና ጦሩ ወደ ደቡባዊ ጋዛ ሊገባ ሁለት ቀን እስኪቀረው እዚያው ነበረች።

በከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ የነበረችው የዘጠኝ ወሯ ነፍሰ ጡር ጁማና የመጀመሪያ ልጇን ወደ ዘመዶቿ መላክ ግድ ሆነባት።

አስቀድሞ የነበራትን ዝግጅት ትታ፣ አንድ ልብስ፣ አንስተኛ መጠን ያለው ወተት እና ለመጀመሪያ ልጇ አነስተኛ ቦርሳ ይዛ ነበር የወጣችው።

“ሁኔታው ከባድ ነበር” ስትል ለቢቢሲ የምትገልጸው ጁማና “በምሽት አንተኛም ነበር። በርካታ የጦር ጄት ድበድባዎች ይፈጸሙ ነበር። በዚህም ምክንያት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር ይጠበቅብን ነበር። እንደእኔ ያለች እርጉዝ ሴት የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባት ነበር። ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት ምግብ ለመግዛት እንኳን መውጣት አንችልም ነበር” ትላለች።

የእራኤልና ሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተወለደችው ታልያ
የምስሉ መግለጫ,የእራኤል እና ሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የተወለደችው ታልያ

ጁማና በጦርነት ውስጥ እንዴት እወልዳለሁ ከሚለው ስጋት እና ጭንቀቷ በተጨማሪ በከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ ውስጥ የመብራት እና የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዲሁም የውሃ እጥረት ፍርሃቷን አክብዶት ነበር።

ጁማና የእስራኤል እና ሐማስ ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ 6 ቀናት በኋላ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም. ምጥ መጣባት።

ይህ ሁሉ ከመሆኑ አስቀድሞ ለመውለድ ያቀደችው ጋዛ በሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋ ነበር። ሆኖም ሆስፒታሉ በጦርነቱ ሳቢያ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሆነ ሰማች።

በዚህም ሳቢያ በጋዛ ሰርጥ መካከል ላይ ወደሚገኘው አል አዋድ የተሰኘ አነስተኛ ሆስፒታል ተጓዘች።

ሆኖም እዚያ መሄድም ቀላል አልነበረም።

ጁማና በህመም እና ምጥ ውስጥ ሆና ወደ ሆስፒታል የሚወስዳት ሰው መፈለግ ነበረባት።

“የታክሲ አሽከርካሪዎች ፈርተዋል፣ አምቡላንሶች ደግሞ ለመውለድ ለታቃረበች ሴት ጊዜ የላቸውም” ስትል ታስረዳለች።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ሆስፒታል ደረሰች። የማማጫ ክፍሉ ግን ከባድ እና አስጨናቂ ሆና አገኘችው።

“ከሆስፒታሉ አጠገብ ባለ አንድ ቤት ላይ ከባድ ደብደባ ይፈጸም ነበር። ቅርብ ስለሆነ ድምጹ በጣም ይጮኻል፣ በጣም ይረብሻል። ጥቃቱ ሆስፒታሉ ላይ የደረሰ ሁሉ መስሎኝ ነበር። የተጎዱ ሰዎች መምጣታቸውን ቀጥለው ነበር። ከሁሉም አቅጣጫ በስቃይ የሚጮህ ሰው ይሰማኝል። በዚህ መካከል ስለመጀመሪያዋ ልጄ አስብ ነበር። ከአጠገቤ ስለራቀች ስለእሷ እጨነቅ ነበር። ሀሳቤ በሙሉ ምንም ነገር ይፈጠር ልጄን መውለድ እፈልጋለሁ የሚል ነበር” ትላለች።

ከብዙ አስጨናቂ ሰዓታት በኋላ ምሽት ላይ ታልያ የሚል ስም የወጣላት ሴት ልጅ ተወልዳ ለቅሶዋ ተሰማ።

“ለቅሶዋ ሁላችንም እስካሁን በሕይወት አለን የሚል ትርጉም ሰጠኝ” ስትል ትገልጻለች።

ጁማና ልጇን እንደወለደች ማረፊያ አልጋ አልተገኘላትም ነበር። በከፍተኛ ህመም እና ደም መፍሰስ ውስጥ ሆና በታካሚዎች የተሞላ ክፍል እስኪገኝ ድረስ መቆየት ነበረባት።

“ያንን በማግኘቴ ዕድለኛ ነኝ። ሌሎች ሴቶች ልክ እንደወለዱ በሆስፒታሉ ጥጋጥጎች ሶፋ ላይ ወይም ደግሞ ወለል ላይ ይተኙ ነበር” ትላለች።

የጁማና ልጆች፣ በቅርቡ የተወለደችው ታሊያና የአራት ዓመት እህቷ ቱሊን
የምስሉ መግለጫ,የጁማና ልጆች፣ በቅርቡ የተወለደችው ታሊያና የአራት ዓመት እህቷ ቱሊን

የመንግሥታቱ ድርጅት የሥነ ሕዝብ ተቋም በጋዛ 50 ሺህ ነፍሰጡሮች እንደሚገኙ እና ከእነዚህ ውስጥ 5500 የሚሆኑት በቀጣዮቹ 30 ቀናት ውስጥ እንደሚወለዱ ገምቷል።

ጨምሮም ሆስፒታሎች በከፍተኛ መጨናነቅ ውስጥ እንደሚገኙ እና የመድኃኒት እና መሠረታዊ አቅርቦቶች እያለቁባቸው እንደሆነ ገልጿል።

ጁማና ከወለደች አንድ ቀን በኋላ ሆስፒታሉን ለቃ ወደ ቤተሰቧቿ መሄድ ነበረባት። ሆኖም ያ ራሱ ከባድ ጭንቅ እና መከራ እንደነበር ታስታውሳለች።

የሆስፒታሉን ደረጃዎች ከመውረድ ቤተሰቦቿ ጋር እስክትደርስ ያለው መንገድ ሁሉ ፈተና ነበር።

“ሊፍቱ በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት አይሰራም ነበር” ስትል ታስታውሳለች። በዚህም ምክንያት ከወለደች ገና አንድ ቀን የሆናት ጁማና በህመም ውስጥ ልጇን ታቅፋ ከአራተኛ ፎቅ እስከ መውጫው ድረስ በርካታ ደረጃዎችን በእግሯ መውረድ ነበረባት።

ይህንን ሁሉ አልፋ ወደምትታረስበት ስፍራ ለመሄድ መጓጓዣ መጠበቅ ደግሞ ሌላ ፈተና ሆነ።

“ታክሲ ለማግኘት አንድ ሰዓት ጠብቄያለሁ። የትኛውም የታክሲ አሽከርካሪ እኛን ለመውሰድ ፍቃደኛ አልነበረም። አካባቢው ላይ ጠዋት ላይ በነበረው ወታደራዊ ጥቃት ምክንያት ፈርተው ነበር። መጨረሻ ላይ በከፍተኛ ዋጋ የሚያደርሰን መኪና ብናገኝም የምቆይበት ቤት አቅራቢያ አላወረደንም” ትላለች።

ጁማና በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውለድ እጅግ አስቸጋሪ መዘዝ ይዞ እንደመጣ ትናገራለች። “አእምሮዬ በጣም ዝሏል። ማንኛውንም ነገር የማድረግ ፍላጎቴ ጠፍቷል” ስትል ትገልጻለች።

ሆኖም ልጇ ታሊያ በጥሩ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሳለች። “አዲሷ ልጃችን የእኔ፣ የእህቷ እና የአባቷን ባህሪ ይዛለች” ስትል ትናገራለች።

ቀጥላ “ጦርነት ውስጥ ባንሆን ኖሮ ከተወለደች አንድ ሳምንት በኋላ በጣም አስደሳች የሆነውን ባህላዊ ሥነ ሥርዓት እናካሂድ ነበር። ሁሉንም ቤተሰቦቼን ጋብዤ አቂቃ [የሙስሊሞች ባህላዊ ሥነ ሥርዓት] አደርግ ነበር” ብላለች።

ቀጣዩ ጊዜ ለቤተሰቦቼ ምን ይዞ እንደሚመጣ አላውቅም የምትለው ጁማና፣ በአዲሷ ልጅ ፈጣሪዋን እንደምታመሰግን ተናግራለች። ጨምራም “በጦርነት እና ሞት መካከል ባለው በዚህ ሕይወት ውስጥ ተስፋ የማገኝባት ነች” ብላለች።