
ከ 5 ሰአት በፊት
ሐንጋሪ 50 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንዳይሰጥ አገደች። ይህ እርዳታ ሊሰጥ የነበረው ከአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን ነበር።
“ድምጽን በድምጽ በመሻር መብት እርዳታውን አስቁመናል” የሚል መልእክት ለጥፈዋል የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን።
የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን የሚሰጠውን እርዳታ የተመለከተው ውይይት በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ይቀጥላል ብለዋል።
ዩክሬን ከሩስያ የተቃጣባትን ወረራ ለመቀልበስ በአውሮፓና አሜሪካ እርዳታ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ናት።
ይህ የ50 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ በሐንጋሪ እንዲቆም መደረጉ ይፋ ከሆነ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ዩክሬን በኅብረቱ አባል ስለምትሆንበት ሁኔታ ንግግር እንዲጀመር ወስነዋል። ሞልዶቫ ደግሞ የኅብረቱ እጩ አባልነት እንዲሰጣት ተወስኗል።
ሐንጋሪ ለረዥም ጊዜ የዩክሬን የአውሮፓ ኅብረት አባል የመሆንን ጥያቄ ውድቅ ስታደርግ ነው የቆየችው። ይሁንና ይህን ‘ንግግር ይጀመር’ የሚለውን ውሳኔ ድምጽን በድምጽ አልሻረችም።
የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ስብሰባውን ለቀው ከወጡ በኋላ ቀሪ የኅብረቱ አባላት ድምጽ ሰጥተዋል ተብሏል።
የአውሮፓ ካውንስል ቃል አቀባይ ቻርለስ ሚሸል ስምምነቱ በሙሉ ድምጽ ነው የተወሰነው ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ዩክሬን ለአውሮፓ ኅብረት አባልነት ንግግር እንዲጀመር በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ”ታሪካዊ ድል” ሲሉ አወድሰውታል።
- የአቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ተናገሩከ 3 ሰአት በፊት
- የኢትዮጵያ ብድር መክፈል አለመቻል እና የሚያስከተለው ዳፋከ 6 ሰአት በፊት
- ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ሰላም የሚኖራት “ዓላማችን ሲሳካ ብቻ ነው” አሉ14 ታህሳስ 2023
ሐንጋሪ የ50 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ማስቆሟን አስመልክተው አስተያየት የሰጡት የደች ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩት ‘አሁንም ጊዜ አለን፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት እንነጋገርበታለን። ዩክሬን እርዳታውን አታገኝም ማለት አይደለም።’ ብለዋል።
“26 አገራት ተስማምተናል። የሐንጋሪው ቪክተር ኦርባን ናቸው ሊስማሙ ያልቻሉት። ተስፋ አደርጋለሁ በሚቀጥለው ዓመት ምናልባትም ጥር ላይ ስምምነት እንፈርማለን” ብለዋል ማርክ ሩት።
አሜሪካ ዩክሬን የአውሮፓ አባል እንድትሆን ንግግር እንዲጀመር መወሰኑና ሞልዶቫ እጩ አባል የመሆኗን ነገር አድንቃለች።
በዚህ ዓመት መጀመርያ ሞልዶቫ ሩሲያ ታሰጋኛለች ብላ ነበር።
ትናንት ሐሙስ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የእርዳታ ጥያቄ ጉዳይ ሲያፌዙ እንደነበር ተዘግቧል። ‘የምዕራቡ ድጋፍ እየደረቀ ነው። ይቅርታ አድርጉልኝ ተገቢ ያልሆነ ቃል ከተጠቀምኩ። ግን ከዚያም ከዚሕም ተለቃቅሞ የሚመጣው ነገር የሆነ ቀን ላይ ማለቁ አይቀርም’’ ነበር ያሉት ፑቲን።
ዩክሬንን የአውሮፓ ኅብረት አባል አጋር ለማድረግ ንግግር እንዲጀመር ቢወሰንም አባልነት ረዥም ሂደት የሚጠይቅ ነው። ሂደቱ ምናልባትም ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።
አውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን እጩዎች በርካታ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሕግን በማስከበር፣ ሙስናን በማድረቅ እና በሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ ሊገለጽ ይችላል።
ዘለንስኪ ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ ለማግኘት ከሰሞኑ ዋሺንግተን እንደነበሩ አይዘነጋም።