አርሶ አደሮች

ከ 5 ሰአት በፊት

የኢንዶኔዥያ ጦር አርሶ አደሮችን ሩዝ በመትከል እንዲያግዝ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ታዘዘ።

በድርቅና ኤል ኒኖ ምክንያት አገሪቱ የድርቅ ስጋት ውስጥ በመግባቷ ነው ትዕዛዙን ያስተላለፉት።

ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ለአገሪቱ ጦር አዛዦች እንደገለጹት፣ ከሰሞኑ በተወሰኑ ግዛቶች ዝናብ ስለዘነበ በእርሻ አርሶ አደሮችን ማገዝ አለባቸው።

በደቡብ እስያ አብዛኞቹ አገራት በተራዘመ ድርቅ ምክንያት ሰብል ምርታማ እየሆነ አይደለም።

ከውጭ ምግብ ለማስገባት የሚጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ መሆንም የምግብ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ ጥሏል።

በድርቅ ሳቢያ ሩዝ ቀድሞ ከሚተከልበትና ከሚበቅልበት ጊዜ ዘግይቷል።

አገሪቱ የሩዝ ምርት ከ31.53 ሚሊዮን ቶን ወደ 30.9 ሚሊዮን ቶን ቀንሷል።

ከሰሞኑ ፕሬዝዳንቱ ፔካሎንጋን የተባለ ግዛት ከጎበኙ በኋላ በፕሬዝዳንታዊ ዩቲዩብ ገጽ ላይ የአገሪቱ ጦር አርሶ አደሮችን እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

ሩዝ በሚተከልበት ወቅት ተከታታይ ክትትል እንደሚፈልግ በመጥቀስና በተወሰኑ አካባቢዎች ዝናብ እንደዘነበ በመግለጽ ነው ጦሩ እርዳታ እንዲሰጥ የተጠየቀው።

በቅርብ የተተከለ የሩዝ ሰብል አጠገብ ቆመው በዩቲዮብ ቪድዮ የለቀቁት ፕሬዝዳንቱ “የሩዝ ምርት በኤል ኒኖ ምክንያት ቢዘገይም መትከል አለብን” ብለዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ ኤል ኒኖ ደረቅና ሞቃት የአየር ሁኔታ ይፈጥራል። ይህም ምርት ይቀንሳል።

የአገሪቱ መከላከያ ቃል አቀባይ ጁልየስ ሚጆኖ እንዳሉት አብዛኞቹ የሩዝ አርሶ አደሮች የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟቸዋል። ይህም ወጣቶች ወደ ከተማ ሥራ ፍለጋ ስለሚፈልሱ ነው።

መሬት እያላቸው የሰው ኃይል እጥረት የሚገጥማቸው አርሶ አደሮች ያሉት ለዚያ እንደሆነም ገልጸዋል።

ምን ያህል የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ጥናት ተደርጎ ከአንድ አካባቢ በአቅራቢያ ያለ ወታደራዊ ዕዝ ማሠማራት እንደሚቻል አክለዋል።

ከኤል ኒኖ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ከነጭ ሩዝ ውጭ ያሉት ላይ በሕንድ ከተያዘው ማዕቀብ ጋር በተያያዘ የዓለም የሩዝ ምርት ዋጋ በ45% ከፍ ብሏል።

ይህም በ15 ዓመታት ከፍተኛው ነው።

የግብርና ሚኒስትር አምራን ሱሌይማን እንዳሉት፣ የአገሪቱ ጦር ተሳታፊ ከሆነ ከዚህ ቀደም እንደሆነው ሁሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያግዛሉ።

ተሳትፏቸው ከውጭ አገር ሩዝ ማስገባት እንዲቀንስ እንደሚረዳም አክለዋል።

ከዚህ በፊት ግብርና ሚኒስቴር እና መከላከያ ሚኒስቴር የጋራ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፣ ወታደሮች በግብርና ድጋፍ ለመስጠትም ተስማምተዋል።

ጥቅም ላይ ባልዋለና በጦሩ ይዞታ ሥር ባለ ባዶ መሬት ሩዝ ለመዝራትም ተስማምተዋል።