
ከ 5 ሰአት በፊት
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የተወሰኑ አባላቱ እስራኤል በኃይል ይዛው በምትገኘው ዌስት ባንክ ካለ አንድ መስጅድ ገብተው ገብተው የፈጸሙትን ድርጊት አውግዣለሁ ብሏል።
የእስራኤል ወታደሮች የመስጅዱን ማይክሮፎን ጨብጠው ሲዘፍኑና ሲሳለቁ ይታያሉ።
የእስራኤል ወታደሮች በዌስት ባንክ ያሉ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በሚል ወረራ በፈጸመበት ወቅት ነው ይህ የሆነው።
በዚህ ዘመቻ 11 ፍልስጤማዊያን መሞታቸውን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች “እንደጥፋታቸው ይቀጣሉ” ብሏል።
ሠራዊቱ አክሎ በጋዛም እንዲሁ ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀሙት ወታደሮች ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ገልጧል።
ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ከተሰራጩ ቪድዮዎች መካከል በአንዱ የእስራኤል ወታደሮች የመስጅድ ማይክሮፎን የአይሁድ በዓል ስለሆነው ሃኒካህ በእብራይስጥ ቋንቋ ሲያዜሙ ይታያሉ።
ቪድዮውን ይቀርፅ የነበረው ወታደርም እየሳቀ አብሯቸው ሲያዜም ይሰማል።
በሌሎች ቪድዮዎች ደግሞ የተወሰኑ ወታደሮች መስጅድ ገብተው የአይሁድ ፀሎት ሲያሰሙ ታይተዋል።
የፍልስጤም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የተቀደሰው መስጅድ ላይ መሳለቅ ነው” ሲል ድርጊቱን ኮንኖታል።
- እስራኤል ዓለም አቀፍ ድጋፍ ብታጣ እንኳ የጋዛን ጦርነት ትገፋበታለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ14 ታህሳስ 2023
- ጋዛ፡ በእስራኤል አየር ድብደባ እና ከበባ ውስጥ የሚወልዱ እናቶችከ 6 ሰአት በፊት
- “እናቴ እና አያቴ የት ናቸው?” – 35 የቤተሰቡ አባላት የተገደሉበት ሕጻን13 ታህሳስ 2023
ሐሙስ ዕለት መግለጫ ያወጣው የእስራል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮቹ “ከሠራዊቱ ሥነ-ምግባር ውጭ ኃይማኖታዊ ተቋማትን የሚያንቋሽሽ ድርጊት አሳይተዋል” ብሏል።
መግለጫው አክሎ ለድርጊቱ ኃላፊነት የወሰዱ ወታደሮች “ወዲያውኑ ከሥራቸው ተቀንሰዋል” ይላል።
“ቪድዮዎቹ ላይ የሚታዩት ወታደሮች ያሳዩት ባሕሪ በዝምታ የማይታለፍ እና ፍፁም ከመከላከያ ሠራዊቱ እሴት ጋር የሚፃረር ነው።”
የእስራኤል ወታደሮች መሰል ድርጊት ፈፅመው የተቀረፀ ምስል ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ሲሰራጭ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ካለፈው የአውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር መገባደጃ ጀምሮ ጋዛ አቅንተው ውጊያ እያደረጉ የሚገኘው የእስራኤል ኃይል ከዚህ ቀደምም እንዲህ ሲያደርግ ታይቷል።
የእስራኤል ወታደሮች እየተሳሳቁ አንድ የአሻንጉሊት መሸጫ ሱቅ ሲያፈራርሱ እና መኪና ላይ ተጭኖ የነበረ ዕቃ ሲያቃጥሉ ታይተዋል።
አልፎም አንድ የግል መኖሪያ ቤት ገብተው የተደረደረ የሴቶች ልብስ ሲያመሳቃቅሉም ታይተዋል።
ባለፈው ሰንበት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ አዳም ዳንዔል ሃጋሪ የወታደሮቹን ድርጊት ሲኮንኑ ተሰምተዋል።
“የሠራዊቱ አባላት በሠራዊቱ እሴት መሠረት ነው ሊንቀሳቀሱ የሚገባው” ብለዋል።
“የጦር አውድማ ላይ ያሉ ወታደሮች ፕሮፌሽናል በሆነ እና ሥነ-ምግባር በተሞላበት መንገድ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ይህ የማንደራደርበት ጉዳይ ነው። ቪድዮዎቹ የሠራዊቱን እሴት የሚገልጡ አይደሉም። እርምጃ እንወስዳለን።”
እስራል ዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን ተጠርጣሪዎችን ለማሰር በሚል ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ከፍልስጤማዊያን ታጣቂዎች ጋር ጦርነት ላይ ትገኛለች።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር ከተገደሉት 11 ፍልስጤማዊያን መካከል አንዱ የ13 ዓመት ታዳጊ ነው ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ወደ ስደተኞች ጣቢያ አቅንቶ የቤት ለቤት ፍተሻ ያደረገ ሲሆን በርካታ የጦር መሣሪያዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጅዎችና ለዋሻ መሥሪያ የሚሆኑ ቁሳቁስ አግኝቻለሁ ብሏል።
ሠራዊቱ አክሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎችን ማሠሩን ገልጧል።