
14 ታህሳስ 2023
ተሻሽሏል ከ 3 ሰአት በፊት
መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ ነበር በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታየ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት ከነበረበት የመንግሥት ቤት ‘ሙሉ ንብረታቸውን ሳያወጡ እንደታሸገባቸው’ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የመንግሥት ቤቶችን የሚያስተዳድረው ተቋም እስከ ሐሙስ ድረስ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ በትናንትናው ዕለትም በግዴታ እንዲወጡ መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
አቶ ታዬ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ባሉት ሶስት ቀናት ውስጥ ዕቃቸውን ይዘው እንዲወጡም ተነግሯቸው ነበር።
“የጸጥታ ኃይሎች ሐሙስ ዕለት ጥዋት ሶስት ሰዓት ላይ መጥተው አስወጡን” የሚሉት ወ/ሮ ስንታየሁ የተወሰኑ የቤት ዕቃዎችን እና አልባሳት ማውጣት ቢችሉም ሌሎች ንብረታቸው በቤቱ ውስጥ መታሸጉን ያስረዳሉ።
“አሁን የምትችሉትን ዕቃዎች ውሰዱ እና ሌሎች ንብረታችሁን አርብ ተመልሳችሁ ውሰዱ ብለው ነው ያሸጉት” ሲሉም ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በቤተሰቦቻቸው ቤት በጊዜያዊነት ተጠግተው እንደሚገኙም አስረድተዋል።
አቶ ታዬ ሰኞ ምሽት በጸጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ለቢቢሲ የተናገሩት ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ፣ ማክሰኞ ጠዋት የመንግሥት ቤቶችን ከሚያስተዳድረው ተቋም አስከ ሐሙስ ድረስ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ገልጸው ነበር።
የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት እንደራሴው አቶ ታዬ ደንደአ ባለፉት ጥቂት ወራት በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ በሚያንጸባርቁት ከመንግሥት አቋም በሚቃረን አስተያየታቸው መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ስለተካሄደው ድርድር መክሸፍ፣ ስለሙስና፣ በኦሮሚያ ክልል ስላለው ግጭት እና አዲስ አበባ ውስጥ ሊካሄድ ታቅዶ በተከለከለው ሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያ መንግሥትን የሚተች ጠንካራ አቋም ማንጸባረቃቸውን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጻፈ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው መባረራቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ዕለት ለአቶ ታዬ በጻፉት ደብዳቤ ከሚኒስትርነታቸው መሰናበታቸውን ይፋ ያደረጉትን አቶ ታዬን፣ በዚያኑ ዕለት ምሽት በርካታ የፖሊስ አባላት ወደ ቤታቸው መጥተው ፍተሻ በማካሄድ ይዘዋቸው እንደሄዱ ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“የፌደራል ፖሊስ አባላት ምሽት አምስት ሰዓት ወደ ቤታችን መጥተው እስከ ሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ድረስ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ 9፡45 ላይ ይዘውት ሄዱ” በማለት አዲስ አበባ ውስጥ ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ባለቤታቸው አቶ ታዬን ተይዘው በሚገኙበት የፌደራል ፖሊስ ማቆያ ውስጥ ረቡዕ ተቀራርበው መነጋገር ባይችሉም “ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ጊቢ ውስጥ በሩቁ በዐይኔ አይቸዋለሁ” ብለዋል።
አገሪቱን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) የሕዝብ ተወካይ የሆኑት አቶ ታዬ፣ ያለመከሰስ መብት ያላቸው ሲሆን በቁጥጥር ስር ከዋሉ ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸው እንደሆነ እና ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው ያወቁት ነገር እንደሌለ ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ለቢቢሲ ሰኞ ዕለት ተናግረው ነበር።
አቶ ታዬ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ስለመቅረብ አለመቅረባቸው ቢቢሲ ለማጣራት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግኙነት ኃላፊን ቢጠይቅም ማረጋገጫ ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
- አቶ ታዬ ደንደአ “መንግሥትን ለመጣል” በማሴር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ12 ታህሳስ 2023
- “ስለእርቅ ስለተናገርኩ፣ ጦርነት ይቁም ስላልኩ እንጂ ሌላ ምክንያት የለም” – አቶ ታዬ ደንደአ11 ታህሳስ 2023
- “የዳሬሰላሙ ድርድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” – አቶ ታዬ ደንደአ7 ታህሳስ 2023
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአቶ ታዬን በቁጥጥር ስር መዋልን በተመለከተ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ በሽብር ቡድንነት ከተፈረጀው ሸኔ እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር “መንግሥትን በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ለመጣል” ሲያሴሩ እንደተደረሰባቸው ጠቅሷል።
ጨምሮም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጸሙ የሽብር ተግባራት “በተለይም ከእገታ ጋር” በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት መግለጫው ከሶ፣ በቤታቸው ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የጦር መሳሪያዎች፣ የኤሌክተሮኒክ መገልገያዎች እና ሌሎች ሰነዶች መገኘታቸውን በፎቶግራፍ አስደግፎ አቅርቧል።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ግን በአቶ ታዬ ላይ የቀረቡት ክሶችን እንደማይቀበሉ “አሁን የሚጻፈው እና የሚባለው እርሱን ይገልጸዋል ብዬ በፍጹም አላምንም! በፍጹም!” ሲሉ በአጥብቀው ተቃውመዋል።
“በእርግጥ ሥራውን የሚደግፉም፣ የሚተቹም አሉ። እሱ በፓርቲው ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ መካድ ካልሆነ በስተቀር የሚያውቀው ያውቀዋል። ይሄ ጫና የጀመረው ከክልል ነው። እኔ እርሱ ታማኝ እንደሆነ ነው የማውቀው” ብለዋል።
የባለቤታቸው መታሰር በቤተሰባቸው ላይ ከባድ ችግርን እንዳስከተለ የሚናገሩት ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ፣ አቶ ታዬ ሰኞ ታኅሣሥ 01/2016 ዓ.ም. ምሽት መያዛቸውን ተከትሎ በቀጣዩ ቀን የሚኖሩበትን የመንግሥት ቤት ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው ጎዳና ላይ የመውደቅ ስጋት እንደደቀነባቸው ገልጸው ነበር
“የኪራይ ቤቶች ሰዎች ማክሰኞ ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ መጥተው ቤቱን በሦስት ቀናት ውስጥ ለቀን እንድንወጣ መልዕክት አስቀምጠው ሄደዋል። ረቡዕ ጠዋት መልሰው በመምጣት ሐሙስ 3፡00 ላይ ቤቱን እንድትለቁ ብለውናል።” ሲሉም ለቢቢሲ አስረድተው ነበር።
ወ/ሮ ስንታየሁ ልጆቻቸው ተማሪዎች መሆናቸውን እንዲሁም ሌላ ቤተሰብም አብረዋቸው እንደሚኖሩ በመጥቀስ በዚህ አጭር ጊዜ ቤት መፈለግም አስቸጋሪ እንደሆነባቸው እና ሁኔታው የበለጠ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
ግራ የተጋቡት ወ/ሮ ስንታየሁ ውሳኔው ገፍቶ የሚመጣ ከሆነ “እንግዲህ ጎዳና ላይ ለመውጣት እንገደድ ይሆናል። ነገ [ሐሙስ] ሦስት ሰዓት ላይ ምን እንደሚሆን እናያለን” ሲሉም ሰኞ ምሽት ተናግረዋል።
አቶ ታዬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ባሉበት ሁኔታ ቤተሰባቸው ይኖርበት ከነበረው የመንግሥት ቤት በሦስት ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን በተመለከተ ባለቤታቸው ላቀረቡትን ቅሬታ ከሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያ ለመጠየቅ ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ታዬ ደንደአ በአገሪቱ የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ከእስር የወጡ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመሪነት መንበሩን ከያዙ በኋላ ከቅርብ ደጋፊዎቻቸው መካከል በመሆን ወደ መንግሥት ሥልጣን መምጣታቸው ይታወቃል።
አቶ ታዬ ኢህአዴግን የተካው ብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል ከመሆናቸው በተጨማሪ በፓርቲው፣ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ላይ ሠርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሦስት መስመር የምስጋና ደብዳቤ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ከኃላፊነታቸው አስከተነሱበት ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ድረስም ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።