
ከ 5 ሰአት በፊት
የሆንግ ኮንግ ፖሊስ አምስት የዲሞክራሲ ተሟጋቾችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚረዳ መረጃ ለጠቆመ የሆንግ ኮንግ አንድ ሚሊዮን ዶላር ወይም 128 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንደሚሸልም አስታወቀ።
ከነዚህም ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው የቀድሞ የእንግሊዝ ቆንስላ ሰራተኛ ሲሞን ቼንግ ተካቶበታል።
ሌሎቹ ደግሞ ፍራንሲስ ሁይ፣ ጆይ ሲዪ፣ ጆኒ ፎክ እና ቶኒ ቾይ ናቸው።
ሁሉም የተከሰሱት የአገሪቷን የብሔራዊ ደህንነት ህግ በመጣስ ነው።
አገሪቱ እየወሰደችው ያለችው እርምጃ ተሟጋቾቹ መኖሪያቸውን ባደረጉባቸው አሜሪካ እና እንግሊዝ ተወግዟል።
አምስቱ ግለሰቦች “መገንጠልን በማነሳሳት” እንዲሁም “ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነትን ለአደጋ አጋልጠዋል” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
“አገራቸውን ሆንግ ኮንግን ሸጠዋል እንዲሁም የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አስተላልፈው ሰጥተዋል” ሲሉም የአገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ዋና ተቆጣጣሪ ሊ ክዋይ ዋህ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤታቸው እስከ መጨረሻው እንደሚያሳድዳቸውም አስጠንቅቀዋል።
- ‘በኦንላይን’ ሥራ እንዴት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል? “በ9 ወር ሚሊየነር ሆኛለሁ” የሚለው ኢትዮጵያዊ13 ታህሳስ 2023
- አራት ልጆቿን ገድለሻል ተብላ ለ20 ዓመታት የታሰረችው እናት ከወንጀሉ ነጻ ናት ተባለ14 ታህሳስ 2023
- የአቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ተናገሩከ 3 ሰአት በፊት
ዋና ተቆጣጣሪው ሊ ክዋይ ዋህ አክለውም ተሟጋቾቹ አገራቸውን ለቀው ወደ ባህር ማዶ አገራት ካቀኑም በኋላም “የአገራቸውን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ተግባራት በመሰማራት ቀጥለውበታል” ሲሉም ወቅሰዋቸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት የተሰጠው ሲሞን ቼንግ በአውሮፓውያኑ 2019 ለስራ ወደ ቻይና ባቀናበት ወቅት ለሁለት ሳምንት ያህል ታስሮ ነበር።
በሆንግ ኮንግ የእንግሊዝ ቆንስላ ሰራተኛ የነበረው ቼንግ የፖለቲካ ሁከትን በማነሳሳትም ክስ ቀርቦበት ነበር።
ቼንግ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በካቴና ታስሮ እንደነበረ፣ ዓይኑም በጨርቅ እንዲሸፈን እንደተደረገ በወቅቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ አስረድቷል።
የታሰረበት ምክንያት ግልጽ ያልሆነለት ቼንግ ለቢቢሲ እንደተናገረው በሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ተሳትፏል ተብሎ ለእስር የተዳረገውን ጓደኛውን ዘመዶች ማግኘቱን ለቢሲ ተናግሯል።
የ33 ዓመቱ ቼንግ ከሆንግ ሆንግ ወደ ብሪታንያ የሚያቀኑ ዜጎችን የሚደግፍ ለትርፍ ያልቆመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትም ይመራል።