
15 ታህሳስ 2023
ግዙፉ የዴንማርክ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት ሜርስክ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በቀይ ባሕር በኩል የሚያደርጋቸውን ጉዞዎች ማቆሙን አስታወቀ።
ባለፉት ሳምንታት በቀይ ባሕር ላይ በዕቃ ጫኝ መርኮች ላይ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።
ሜርስክ ባወጣው መግለጫ “በቅርቡ በቀጠናው በንግድ መርከብ ጭነቶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች አሳሳቢ እና በመርከበኞች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አደጋን የሚደቅኑ ናቸው” ብሏል።
ኩባንያው ትናንት ሐሙስ በሜርስክ መርከብ ላይ የተቃጣ ጥቃት መርከቡን ለጥቂት መሳቱን ገልጾ፣ ዛሬ አርብ ደግሞ በሌሎች መርከቦች ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ የኩባንያው መርከቦቹ በቀይ ባሕር እንዳያልፉ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታውቋል።
ይህ የግዙፉ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት ውሳኔ የተሰማው አሜሪካ በቀይ ባሕር በሚያልፉ ዕቃ ጫኝ መርከቦች ላይ የሚፈጸመው የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች መቀጠላቸውን ካስታወቀች በኋላ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት እንዳስታወቀው ሁለቱ መርከቦች በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ስር ከሚገኝ የየመን ክፍል በተተኮሱ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃቶች መመታታቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ አጋርነታቸውን ለሐማስ የገለጹት የሁቲ አማጺያን ወደ እስራኤል የሚያቀኑ ዕቃ ጫኝ መርከቦችን ዒላማ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
አንደኛው ጥቃት የደረሰበት ዕቃ ጫኝ መርከብ አል ጃስራህ የሚባል እና በጀርመን የትራንስፖርት ኩባንያ የሚተዳደር ነው።
የኩባንያው ቃል አቀባይ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ መርከቡ ከግሪክ ወደብ ተነስቶ ወደ ሲንጋፖር እያመረ እንደነበረ ገልጸው፣ በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን እና መርከቡ ወደ መዳረሻው ጉዞውን መቀጠሉን ተናግረዋል።
- ኢትዮጵያ የቦንድ ብድር ወለድ ያልከፈለችው በገንዘብ እጥረት አለመሆኑን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ15 ታህሳስ 2023
- የኢትዮጵያ ብድር መክፈል አለመቻል እና የሚያስከትለው ዳፋ15 ታህሳስ 2023
- የሱተን የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት፡ ዩናይትድ ከአንፊልድ ነጥብ ማግኘት ይቻለው ይሆን?15 ታህሳስ 2023

አርብ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ሌላ የላይቤሪያ ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልብ መርከብ በተወንጫፊ ሚሳኤል ተመትቶ በእሳት ከተያያዘ በኋላ የአሜሪካ ባሕር ኃይል አውሮፕላን እሳቱን ለማጥፋት ወደ ስፍራ ማቅናቱ ተመልክቷል።
አሜሪካ ከሌሎች አጋር አገራት ጋር በመሆን በቀይ ባሕር የሚተላለፉ መርከቦችን ደኅንነት ለመጠቅ እና የሚተኮሱ ሚሳኤሎች ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት በማውደም ተጠምዶ ቀይቷል።
ባለፉት ሳምንታት የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የዩናይትድ ኪንግደም ኃይሎች በቀይ ባሕር ላይ ቅኝቶችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በርካታ ሚሳኤሎችን መትተው ጥለው።
በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሰሊቫን ሁቲዎች በቀጠናው ለመርከብ እና ለንግድ ሥራዎች ስጋት ናቸው ብለዋል።
አማካሪው በሁቲ አማጺያን ለሚተኮሱት ሚሳኤሎች በሙሉ ተጠያቂዋ ኢራን ነች ሲሉ ከሰዋል።
“ቃታውን የሚስቡት ሁቲዎች ቢሆኑም መሳሪያውን እየሰጠች ያለችው ኢራን ነች። . . . እነዚህ ጥቃቶች እንዲቆሙ ኢራን ኃላፊነት መውሰድ አለባት። . . . ምክንያቱም እነዚህ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥሱ እና ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነትን የሚቃረኑ ናቸው” ብለዋል።
በሳዑዲ የሚደገፈውን የየመን መንግሥትን እየተዋጉ ያሉት የሁቲ አማጺያን ከሐማስ፣ ከሄዝቦላህ እና ከሶሪያ መንግሥት ጋር በመሆኑ በኢራን የሚመራው ‘ሬዚዝታንስ ኦፍ አክሲስ’ አካል ናቸው።
የዚህ ቡድን አባላት ለእስራኤል እና ለአሜሪካ ያላቸው ጥላቻ አንድ ያደርጋቸዋል።
በሁለቱ መርከቦች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ በአካባቢው የነበረ አንድ መርከብ በአጋቾች ተጠልፎ ወደ ሶማሊያ እየተወሰደ መሆኑን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስታውቋል።
የሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ተከትሎ በቀጠናው በተሰማሩ መርከቦች ላይ የመድን ዋስትና እጅጉን በመጨመሩ መርከቦች የቀይ ባሕር አቅጣጫን በመቀየር በደቡብ አፍሪካ በኩል አድገው ወደ መዳረሻቸው እያቀኑ ነው።
ቀይ ባሕር በዓመት 17ሺህ መርከቦች የሚተላለፉበት ሲሆን፣ ይህም ከዓለም የባሕር ግብይት 10 በመቶውን ይይዛል። በሱዩዝ ካናል አልፎ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ የሚሄድ መርከብ ግዴታ በዚህ የቀይ ባሕር ማለፍ ይኖርበታል።