
15 ታህሳስ 2023
ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ሰኞ ዕለት መክፈል የነበረባትን ወለድ እስካሁን ያልከፈለችው ሁሉንም አበዳሪዎች “በእኩል ለማስተናገድ” በሚል እንጂ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኖሮባት አለመሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን የገለጸው ትላንት ሐሙስ ታህሳስ 4/2016 ዓ.ም. ከቦንዱ ገዢዎች ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ ነው። ከአንድ መቶ በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል በተባለው በዚህ የአንድ ሰዓት ስብሰባ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ቦንዱን በተመለከተ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለገዢዎች እንደገለጹ መግለጫው አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታውን እና ገዢዎችን ለስብሰባ ያስቀመጠው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ለሽያጭ የቀረበው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም ነበር። ኢትዮጵያ ይህንን ቦንድ ሸጣ ከገዢዎች አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ያገኘች ሲሆን፣ ብድሩ የሚመለሰው በአስር ዓመት ውስጥ ነው።
እስከዚያው ድረስም መንግሥት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚፈጸም የ6.625 በመቶ ዓመታዊ ወለድ ለቦንዱ ገዢዎች ይከፍላል። ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ዕለት 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ መክፈል የነበረባት ቢሆንም ክፍያውን ሳትፈጽም ቀናት አልፈዋል።
ይህንን የብድር ቦንድ አስመልክቶ ትናንት ከገዢዎች ጋር ውይይት ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር ኢዮብ፤ ኢትዮጵያ የታኅሣሥ ወርን ወለድ ያላስተላለፈችው “ክፍያውን ለማዘግየት ወስና” እንደሆነ ለገዢዎች እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ዶ/ር ኢዮብ፤ ኢትዮጵያ ወለዱን ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ እንዳላት በውይይቱ ላይ የተናገሩ ሲሆን ክፍያውን የማዘግየት ውሳኔ ላይ የተደረሰው ግን “ሁሉንም የውጪ አበዳሪዎቿን “በፍትሐዊነት ለማስተናገድ” ካላት ፍላጎት በመነጨ መሆኑን አብራርተዋል ተብሏል።
ገንዘብ ሚኒስቴር በመግለጫው፤ “[ሁሉንም አበዳሪዎች] በፍትሐዊነት ለመመልከት አለመቻል በዕዳ ሽግሽግ ላይ ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት አደጋ ላይ ይጥለዋል” ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር ወለዱን ቢከፍል ሊያጋጥም የሚችልን መስተገጓጎልን ጠቅሷል።
- የኢትዮጵያ ብድር መክፈል አለመቻል እና የሚያስከተለው ዳፋ15 ታህሳስ 2023
- የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ችግር አዙሪት እና ስጋቶቹ4 ታህሳስ 2023
- ጥያቄ ያስነሳው ሰኔ ላይ የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት ወደ 20% የማውረድ ዕቅድ30 ህዳር 2023
ኢትዮጵያ በቅርቡ ከአበዳሪዎቿ ጋር የብድር ክፍያ ሽግሽግን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሷን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፤ “የቦንድ ገዢዎችን ጨምሮ ሌሎች አበዳሪዎችም ተመሳሳይ አይነት የብድር ክፍያ ማስተካከያ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ [ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ] ወጥነት እና እኩልነትን ለማረጋገጥ” እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የብድር እፎይታ ለማግኘት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ውይይት ማካሄድ ከጀመረች ሰነባብታለች። ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በቻይና እና በፈረንሳይ በሚመራው የፓሪስ ክለብ አማካኝነት የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ደርሳለች።
በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለአበዳሪዎቿ መክፈል የሚጠበቅባትን ብድር እና ወለድ ሁለት ዓመት ገደማ አትከፍልም። ይህ የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ አገሪቱ በየዓመቱ መክፈል የሚጠበቅባትን 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዕዳ በጊዜያዊነት የሚያስቀር መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ከሁለት ሳምንት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡ ጊዜ ተናግረው ነበር።
የዚህን አይነቱን ስምምነት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንዱን ከገዙ የግል ባለሀብቶች ጋርም ለመፈጸም የምትፈልገው ኢትዮጵያ፤ የዋናው ብድር የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም እና በየዓመቱ የሚከፈለውን የወለድ ምጣኔ ከ6.625 በመቶ ወደ 5.5 በመቶ ዝቅ ማድረግ ሀሳብ እንዳላት አስታውቃለች።
የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት የብድር አከፋፈሉ ላይ ማስተካከያ ማድረግ የፈለገው ከሌሎች አገራት ጋር በሚያደርገው የብድር ሽግሽግ ላይ አበዳሪዎችን በተመሳሳይ መልኩ ማስተናገድን በተመለከተ ስጋት እንዳይነሳ በማሰብ መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በስጋትነት ያነሳችው ወጥ ያልሆነ የብድር አከፋፈልን በተመለከተ ከሌሎች አበዳሪ አገራት የሚነሳ ቅሬታ ጉዳይ በቅርቡ በዛምቢያ ላይ እንደተፈጠረ ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።
ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የሦስት ቢሊዮን ዶላር የብድር ቦንድ ለገዢዎች የሸጠችው ዛምቢያ፤ የቦንድ ዕዳ ክፍያን በተመለከተ የብድር ሽግሽግ ከሚያደርጉላት ሌሎች አገራት “ተመሳሳይ አካሄድ አትከተልም” የሚል ቅሬታ ተነስቶባት ነበር። በዚህም ምክንያት አገሪቱ የብድር ሽግሽግ ለማግኘት ስትል የዚህን የቦንድ ብድር አከፋፈልን ለማሻሻል ተገድዳለች።
የገንዘብ ሚኒስቴር በመግለጫው የብድር አከፋፈል ማስተካከያው ላይ ከቦንዱ ገዢዎች ጋር በተቻለ ፍጥነት ስምምነት ላይ መድረስ “ጠንካራ ፍላጎት” እንዳለው ገልጿል። ይሁንና ኢትዮጵያ የቦንድ ብድር ወለዱን በቀኑ እንደማትከፍል ማስታወቋ በቦንዱ ገዢዎች ዘንድ በመልካም አልተወሰደም።
የቦንዱ ገዢዎች ኮሚቴ ይህን የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ “አላስፈላጊ እና አሳዛኝ” አድርጎ እንደሚመለከተው መግለጹን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ውሳኔውን የማያጥፍ ከሆነ ግን ከፍ ያለ ዳፋ ይኖረዋል ማለታቸውም ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ ሰኞ ዕለት መክፈል የነበረባትን ወለድ ለቦንድ ገዢዎች ለማስተላለፍ የ14 ቀናት የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷታል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ወለዱን የማትከፍል ከሆነ ውልን አለማክበር (technical default) እንደሚያጋጥማት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፊች የተሰኘው የአገራትን ብድር የመክፈል አቅም ደረጃ የሚያወጣ አሜሪካ ተቋም ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ዕዳ የመክፈል ደረጃ ከነበረበት “ሲሲ” (CC) ደረጃ ወደ “ሲ” (C) ዝቅ ማድረጉን አስታውቋል። ተቋሙ ለዚህ የደረጃ ምደባ የጠቀሰው አንዱ ምክንያት አገሪቱ የቦንዱን ወለድ በቀኑ አለመክፈሏል ሲሆን፣ በ14 ቀናት ውስጥ ክፍያው ካልተፈጸመ ይህንን ደረጃ በድጋሚ ዝቅ እንደሚያደርገው ገልጿል።