ባንድ

ከ 54 ደቂቃዎች በፊት

ሙዚቃ ሁሉን የሚያግባባ ቋንቋ ነው ይባላል።

የሙዚቃ መሣሪያዎች ግን አካታችነት ይጎድላቸዋል።

በክላሲካል ሙዚቃ ከዚህ ቀደም ያልነበረ የሙዚቃ መሣሪያ መነጋገሪያ ሆኗል። ለአካል ጉዳተኞች ታስቦ የተሠራ ነው።

አሌሳንድሮ ቫዛና 26 ዓመቱ ነው። ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ ሙዚቃ ይጫወታል። ፒያኖ፣ ጊታር እና ከበሮ ይችላል።

በኤሌክትሪክ በሚሠራ ዊልቸር ነው የሚንቀሳቀሰው። ፍራጃይል ኤክስ የተባለ ሕመም ስላለበት እጆቹን ማንቀሳቀስ አይችልም።

ሕመሙ ከሙዚቃ ፍቅር አላቆመውም።

የሙዚቃ መሣሪያዎች ለመጫወት እጅግ ይፈትነዋል። በኤሌክትሪክ ወደሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ (ክላሪዮን) ፊቱን ያዞረውም ለዚያ ነበር።

ክላሪዮን መተግበሪያ ነው። ማንኛውንም የሙዚቃ መሣሪያ አስመስሎ ድምጽ ያወጣል።

መተግበሪያውን ከሠሩት አንዱ ቤሪ ፋራሞንድ-ቾንግ ይባል። ኦፕን አፕ ሚውዚክ በተባለ ተቋም ይሠራል።

“አብዛኞቹን ሙዚቃ መሣሪያዎች ለመጫወት ሁለት እጅ እና አስር ጣት ያስፈልጋል። በክላሮን ለመጠቀም ግን ማዘዝ የምንችለውን የሰውነት ክፍል ብቻ መገልገል እንችላለን። ይህም ዐይን፣ እጅ፣ እግርን ይጨምራል” ይላል።

አካል ጉዳተኞች ሙዚቃ አድማጭ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም መሆን የሚችሉበት መንገድ እንደሆነ ያስረዳል።

አሌሳንድሮ የሚጠቀመው ገመድ አልባ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ነው። የሚፈልግበት ቦታ እንዲጠቁምለት የሚያደርገው በጭንቅላት እንቅስቃሴ ነው። ዐይኑን ተከትሎም መሣሪያው ድምጽ ይሰጣል።

ምርጥ ክላሪዮን ተጫዋች ከሚባሉት መካከል ይጠቀሳል።

“ቆንጆ ሙዚቃን ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር መጫወት እወዳለሁ” ይላል አሌሳንድሮ።

በሙዚቃ ስኮር ምትክ በዕይታ የሚወከሉ ኖታዎችን በመጠቀም ነው ሙዚቃ የሚሠሩት።

ሙዚቃውን ቀድመው ቢቀርጹትም መድረክ ላይ ሲያቀርቡት እንደ ማንኛውም የሙዚቃ ኮንሰርት ያለ ስሜት ይፈጥራል።

“አንዳንዴ ስህተት ሊገኝበትም ይችላል” ይላል ቤሪ።

ቤሪ የሚሠራበት ኦፕን አፕ ሚውዚክ 60 ኦርኬስትራ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም አዘጋጅቷል።

“ማንኛውም መሰናክል ተወግዶ ሙዚቀኛ መሆን ለሚችሉ ወጣቶች” ሙዚቃ ማቅረባቸውን ይናገራል።

አሌሳንድሮ የሚጫወትበት መተግበሪያ ኖዮ ይባላል። ክላሪዮኑ በተለያዩ የኦርኬስትራ ክፎሎች ያሉ የድምጽ አማራጮች እንዲሰጡት ያስችላል።

የሙዚቃ መሣሪያ

“የራሱን ድምጽ እየፈለገ ያለ የሙዚቃ መሣሪያ ነው” ሲል ቤሪ ይገልጸዋል።

የተለየ ድምጽ ያለው ሆኖ መቀጠል ከቻለ እንደ ሌሎች ሙዚቃ መሣሪያዎች ዕድሜው ረዥም እንደሚሆን ያስረዳል።

የክላሪዮን ተጫዋቾች እና አቀናባሪዎች ከቤሪ ጋር በቅርበት ይሠራሉ። ከተለመደው የኦርኬስትራ ሙዚቃ ምን እንደሚጎድል ለመረዳት ይሞክራሉ።

ክላሪዮን የራሱ ድምጽ ካለው አቀናባሪዎች ሙዚቃ አዘጋጅተው ሙዚቀኞች ሊጫወቱት እንደሚችሉ ይናገራል።

በአጠቃላይ ዩናይትድ ኪንግደም 19 በመቶ ሙዚቀኞች አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ክላሪዮንን እንደ ሙዚቃ መሣሪያ ዕውቅና ስለመስጠት ንግግሮች ተደርገዋል።

ባንድ

እንደ ቫዮሊን እና ዋሽንት ክላሪዮንን ለመጠቀም የፈቀዱ የሙዚቃ ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች አሉ።

‘አሶሽየትድ ቦርድ ፎር ዘ ሮያል ስኩል ኦፍ ሚውዚክ’ አንዱ ነው።

በተቋሙ የሚሠራው ጄምስ ሪስደን እንደሚለው ክላሪዮን ቀላል፣ ስሜትን የሚያነሳሳ ተደርጎ ነው የተሠራው። ይህም በሙዚቀኞች ላይ አወንታዊ ስሜት እንደሚፈጥር ይናገራል።

600 ገምጋሚዎች አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው በአመዛኙ በጎ ምላሽ እንደሰጡም አክሏል።

የሙዚቃ መሣሪያው እንደ ሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች መወሰድ እስከሚጀመር ድረስ ሙዚቀኞች መሣሪያውን ተጠቅመው ሙዚቃ መሥራት እንዲቀጥሉ ኦፕን አፕ ሚውዚክ ያበረታታል።

ማይክል ቤትሪጅ የተባለው ሙዚቀኛ ለአሌሳንድሮ ሙዚቃ የጻፈው በዚህ የሙዚቃ መሣሪያ ተጠቅሞ ነው።

“የሙዚቃ መሣሪያው በጣም ቆንጆ ነው። የሚፈጥራቸው ድምጾችም አስደንቀውኛል” ይላል ማይክል።

የሙዚቃ መሣሪያው እየተሻሻለ እና ዕውቅና እያገኘ እንደሚሄድ ተስፋ ተሰንቋል።

አሁን የሚገኘው በኦፕን አፕ ሚውዚክ ቢሆን፣ ከቀጣዩ የአውሮፓውያን 2024 ጀምሮ የሙዚቃ መሣሪያውን መጠቀም ለሚፈልጉ ክፍት እንደሚሆን ቤሪ ይናገራል።

“ከኦርኬስትራ ውጭም ታዋቂ ሲሆን ለማየት ጓጉቻለሁ። ዲጄዎች እና ባንዶች ሲጠቀሙት ማየትም እፈልጋለሁ” ይላል።