በእስራኤል የተገደሉት እስራኤላውያን
የምስሉ መግለጫ,”በስህተት ተገደሉ” የተባሉት፣ አሎን ሻመሪዝ፣ ዮታም ሃይም እና ሳሚር ታላልካ

ከ 45 ደቂቃዎች በፊት

የእስራኤል ጦር ሦስት ታግተው የነበሩ የገዛ ዜጎቹን ጋዛ ውስጥ በስህተት መግደሉን አስታወቀ።

የእስራኤል ጦር በሐማስ እገታ ስር የነበሩትን ሦስቱን ታጋቾችን የገደለው በጦር ቀጠና ውስጥ ለሠራዊት አባላቱ “አደጋ” ተደርገው በስህተት በመታየታቸው ነው ብሏል።

ግድያውን በተመለከተ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ባወጡት መግለጫ “በከፍተኛ ሐዘን ልባችን ተሰብሯል። . . . ታግተው ቆይተው በተገደሉት ዜጎቻችን ሞት ሐዘን ላይ ላሉት በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሐማስ እጅ የሚገኙ ታጋቾችን በሙሉ ነጻ ለማውጣት እስራኤል ቁርጠኛ ናት ያሉ ሲሆን፤ ሦስቱ እስራኤላውያን ታጋቾች ሕይወታቸውን ባጡበት ዘመቻ የተሳተፉ ወታደሮችን አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወታደሮቹ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ወደ አደገኛ የጦር ቀጠና ዘልቀው ገብተዋል ብለዋል።

የአገሪቱ ጦርም የታጋቾቹ ግድያ በተመለከተ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋ “በዚህ አሳዛዥ ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ሠራዊቱ እየገለጸ ለቤተሰብ አባላት ከልብ የመነጨ መጽናናትን ይመኛል” ይላል የእስራኤል ጦር ያወጣው መግለጫ።

ጦሩ ጨምሮ የሟቾቹ አስክሬን ወደ እስራኤል መመለሱን አስታውቋል።

ሐማስ ከዚህ ቀደም በማይቋረጠው የእስራኤል የቦምብ ድብደባ 50 ታጋቾች ተገድለዋል ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

በእስራኤል ጦር በስህተት የተገደሉት የ28 ዓመቱ ዮታም ሃይም፣ የ22 ዓመቱ ሳሚር ታላልካ እና የ26 ዓመቱ አሎን ሻመሪዝ ናቸው።

ሦስቱም ወንዶች ሐማስ መስከረም 26 ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ወደ ጋዛ ከተወሰዱት ወደ 240 ከሚጠጉት ታጋቾች መካከል ይገኙበታል።

በኳታር አደራዳሪነት እስራኤል እና ሐማስ ለጦርነቱ ፋታ በመስጠት የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህ ልውውጥ እስራኤል ዜጎቿን ጨምሮ ከ100 ያላሱ ታጋቾችን ብታስለቀቅም አሁንም ከ100 በላይ ታጋቾች በሐማስ እና በሌሎች እስላማዊ ቡድኖች በጋዛ ተይዘው ይገኛሉ።

ሦስቱ እስራኤላውያን በስህተት በአገራቸው ጦር የመገደላቸው ዜና ከተሰማ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በአገሪቱ መዲና ወጥተው መንግሥት ታጋቾችን እንዲያስመልስ ተጽእኖ ፈጥረዋል።

በከተማዋ ወዳለው የእስራኤል መከላከያ የጦር ሰፈር ያቀኑት ሰልፈኞቹ መንግሥት እንደዚህ ቀደሙ አይነት ስምምነት ፈጽሞ ታጋቾችን እንዲያስለቀቅ ጠይቀዋል።

“ወደ ቤታቸው መልሷቸው” እንዲሁም “የታጋቾች ልውውጥ አሁኑን” የሚሉ ጽሑፎችን ይዘው ወጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሰልፈኞቹ ሕይወታቸው ያጡትን ታጋቾችን ለማስታወስም ሻማ የማብራት ስነ-ስርዓት አካሂደዋል።