አፍጋኒስታን

ከ 12 ደቂቃዎች በፊት

ታሊባን አፍጋኒስታን ውስጥ ከጥቃት የተረፉ ሴቶችን ወደ እስር ቤት እየወሰደ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።

ሴቶቹ የሚታሰሩት ለደኅንነታቸው ነው በሚል ሽፋን መሆኑን አክሏል።

ከጥቃት የተረፉ ሴቶችን ለአእምሯዊና አካላዊ ጉዳት የሚያጋልጥ መሆኑን ተመድ ገልጿል።

ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ማገገሚያና ማቆያ ማዕከሎችንም ታሊባን መዝጋቱን የተመድ ሪፖርት ይጠቁማል።

በአፍጋኒስታን ወደ አመራር በተመለሰው ታሊባን ሥር የሴቶች አያያዝ ከዓለም የከፋው ነው።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ከመመለሱም በፊት ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚደርስ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከፍተኛ እንደነበር በአፍጋኒስታን የሚሠራው የተመድ የተልዕኮ ቡድን አስታውቋል።

ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከምጣኔ ሀብትና ሰብአዊ ቀውሱ ጋር በተያያዘ ጥቃቶች ተባብሰዋል።

ሴቶች ከትምህርትና ሥራ ታግደው ቤት እንዲቆዩ አስገዳጅ ሕጎች መውጣታቸው ሴቶችን በቅርብ አጋር ለሚደርስ የቤት ውስጥ ጥቃት የበለጠ ተጋላጭ እንደሚያደርገቸው ተገልጿል።

እአአ በ2021 ታሊባን ሥልጣን ሳይዝ በፊት በአፍጋኒስታን በመንግሥት የሚደገፉ 23 ለሴቶች ጥበቃና ከለላ የሚሰጡ ማዕከሎች ነበሩ።

አሁን ግን ተዘግተዋል።

ታሊባን ለተመድ የልዑካን ቡድን እነዚህ ማቆያዎች እንደማያስፈልጉና ሴቶች ከባሎቻቸው ወይም ወንድ የቤተሰብ አባላት ጋር እንደሚሆኑ ገልጿል።

እነዚህ ማዕከሎች ‘ምዕራባዊ ዕሳቤ’ ናቸው ሲል ታሊባን ይቃወማል።

ከጥቃት የተረፉ ሴቶች ላይ ጥቃት እንዳያደርሱ ወንድ የቤተሰብ አባላትን ‘ቃል እንደሚያስገባ’ ታሊባን ገልጿል።

አንድ ሴት ወንድ ዘመድ ከሌላት ወይም የደኅንነት ስጋት ካለባት ወደ እስር ቤት እንደምትላክና ይህም ‘ደኅንነቷን ለመጠበቅ’ መሆኑን ነው የገለጹት።

በካቡል የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች መቆያ እንደሚገቡ የተመድ ሪፖርት ያሳያል።

“ይህም ነጻነት ላይ የተጣለ ገደብ ነው። አደጋ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ገድቦ ማስቀመጥ ቅጣት ነው። የአእምሮና አካላዊ ጤና ጉዳት ያስከትላል” ብሏል ተመድ።

ከእስር ሲወጡ በማኅበረሰቡ እንዲገለሉና የተጎጂነት ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርገም ገልጿል።

ታሊባን ጾታዊ ጥቃትን የያዘበት መንገድ “ግልጽ ያልሆነና ዘላቂነት የሚጎድለው” መሆኑን ተመድ ገልጿል።

ሲቪልና የወንጀል ጉዳዮች ተለይተው አለመቀመጣቸው የሕግ ሥርዓትን ያደናቅፋል።

ቅሬታ ተቀባዮች ወንድ መሆናቸውና ቃል የሚቀበሉ ሴቶች አለመኖራቸው ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ሪፖርት ከማድረግ እንደሚያስቀርም ተመድ አክሏል።

ከጥቃት የተረፉ ሴቶች የሚካሱበት መንገድ አለመኖሩ ሌላው ችግር ነው።

የታሊባን ፍራቻ ስለሚይዛቸው በመደበኛ መንገድ ፍትሕ ለማግኘት ለመሞከር እንደማይፈልጉ ተገልጿል።

ታሊባን ወደ ሥልጣን ሲመጣ የሴቶች ጭቆና እንደማይኖር ቢናገርም ባለፉት ዓመታት ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ ሕጎች እየወጡ ነው።

ሴቶች ከመጀመሪያ ደረጃ ውጭ እንዲማሩ አይፈቀድላቸውም። ከሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርስቲ ትምህርት ታግደዋል።

ከፓርክ፣ ስፓርት ማዘውተሪያና መዋኛ ተከልክለዋል። የውበት ሳሎኖች ተዘግተዋል። ሴቶች እንዲለብሱ የሚፈቀደውም ዐይን ብቻ የሚያሳይ ልብስ ነው።

ከ72 ኪሎሜትር በላይ ከተጓዙ ከወንድ ጋር መሆን አለበት።