ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ
የምስሉ መግለጫ,ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ

ከ 58 ደቂቃዎች በፊት

ፕሮፌሰር ገቢሳ በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ይሰሩት የነበረው የተዳቀለ የማሽላ ምርምር ሥራ ግጭት በመኖሩ ምክንያት መስተጓጎላቸውን ገለጹ።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተዳቀለ የማሽላ ምርምር ላይ እንደሚሠሩ አስታውሰው፣ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ባለፉት ዓመታት ግጭቶች በመኖራቸው የተነሳ ሥራቸው መስተጓጎሉን ገልጸዋል።

ስትራይጋ የተሰኘውን አረም እና ድርቅን በሚቋቋሙ በርካታ የማሽላ ዝርያዎች ላይ የሙከራ ምርምር ማጠናቀቃቸውን የሚያስታውሱት ፕሮፌሰሩ፤ ግጭቶቹ በኢትዮጵያ ባይከሰቱ ኖሮ እነዚህን ዝርያዎች ወደ ገበሬው ማሳ በመውሰድ የሙከራ ዘር ምርት ይጀምሩ እንደነበር ተናግረዋል።

“የግል ዘርፉም ወደ ዘር ማምረት ሥራ እንዲገባ እና በስፋት የዘር ምርት ውስጥ እንዲገባ የማግባባት ሥራ እንሠራ ነበር”ይላሉ።

“ነገር ግን በምንሠራባቸው ሦስት ክልሎች ግጭት በመኖሩ የተነሳ፣ በአውሮፓውያኑ 2018 እና 2019 ትንንሽ ግጭቶች ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት መግባት እና መውጣት ባለመቻላችን ሥራችን ተስተጓጉሏል” ብለዋል።

“የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ ውጤቶች፣ ተምችን ጨምሮ የሰብል ተባዮችና በሽታዎች፣ ግጭት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሁሉም አፍሪካውያን ጤና እና በአህጉሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ነው።. . . ። በድህነት ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችንም ህይወት ለማሻሻልና የአፍሪካውያን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት በሚደረጉ ጥረቶችም ግጭት የመጀመሪያ እንቅፋት ነው።”

ግጭት በየትኛውም አካባቢ ሲኖር በግብርና ምርምር ውስጥ ትልቁ እንቅፋት ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ ዝቅተኛ ኑሮ የሚመሩ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከተሠሩ ምርምሮች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በማድረግ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ገቢሳ የአፍሪካውያንን እና ዝቅተኛ ኑሮ የሚመሩ አርሶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር በሚደረገው የግብርና ምርምር ውስጥ በግንባር ቀደምትነት “ግጭት ተግዳሮት” መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የሚያደረጉትን የምርምር ሥራ ካዘገዩ ነገሮች መካከል፣ አንዱ ግጭት መሆኑን በማንሳት ይህ በማሽላ ላይ የሚደረገውን ምርምር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የምርምር ሥራዎችም ባለው ግጭት የተነሳ መዘግየት እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

“ግጭት ለኢኮኖሚ፣ ለሕዝባችን የዕለት ተዕለት ኑሮ እንቅፋት ነው” ሲሉም አክለዋል።

በቅርቡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገቢሳ ኤጀታ (ፕሮፌሰር) በዕፀዋት ዘረመል ማዳቀል ላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአሜሪካ የሳይንቲስቶች ቡድን ዕውቅና የሰጠውን የአሜሪካ የብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ተሸለመዋል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ የዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባካናወኗቸው ሥራዎች በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ተቀብለዋል።

ፕሮፌሰሩ በቅርቡ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እጅ ብሔራዊ የክብር ሽልማት ሜዳሊያ መቀበላቸው ይታወሳል።

የማሽላ አባት – ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ማሽላ የአፍሪካ አህጉርን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ “በጣም ወሳኝ ሰብል ነው” ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በዓለም ላይ ካሉ ሰብሎች ሁሉ ማሽላ “አስተማማኝ እና የተለያዩ አየር ጠባዮችን ለመቋቋም የሚችል” ነው ይላሉ።

ማሽላ በአፍሪካውያን ዘንድ ለምግብነት የሚውል መሆኑን ያስታውሱት ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ ምግብ እና መጠጥ ለማዘጋጀት በሰፊው ጥቅም ላይ እንደሚውል ይናገራሉ።

ማሽላ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ለሚሊዮኖች “የዕለት ተዕለት ምግብ አካል” እንዲሁም ገ“ለሥነ ምግብ የጀርባ አጥንት” መሆኑን ይናገራሉ።

ማሽላ ላይ ሰፊ ምርምር ለአራት አስርታት ያደረጉት ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ ድርቅ፣ ተባይ፣ ጥገኛ አረም እንዲሁም ማሽላን ለይተው የሚያጠቁ በሽታዎች በአፍሪካ እንዲሁም በደቡብ ምስራቅ እስያ አገራት ማሽላን በማንኛውም ሁኔታ እና የአየር ጠባይ በሰፊው የሚያጠቁ በመሆናቸው የሚሰሯቸው የምርምር ስራዎች እጅግ በጣም ወሳኝ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር ገቢሳ በማሽላ ላይ ያደረጉት የምርምር ስራ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ተጠይቀው ሲመልሱ ከዩኒቨርስቲ እንደ ተመረቁ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ይደረገለት በነበረ የአዝዕርት ምርምር ተቋም ላይ በተመራማሪነት ለአምስት ዓመት በሚሰሩበት ወቅት የሱዳን በረሃ ድርቅን እና በሽታን የሚቋቋም የተዳቀለ ማሽላ ዝርያን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይህ የምርምር ስራቸውን በ2009 የወርልድ ፉድ ፕራይዝ ተሸላሚ እንዲሆን አድርጓቸዋል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ እኤአ በ1980ዎቹ መጨረሻ እና በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ ይህንን የተዳቀለ የማሽላ ዝርያ ዘር ተባዝቶ ለገበሬዎች የሚከፋፈልበትን መንገድ አመቻችተው ለአስር ተከታታይ ዓመታት በሚሊዮን ሄክታሮች ማሽላ በሱዳን ሲመረት መቆየቱን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ከጆ ባይደን እጅ ሜዳልያ ሲቀበሉ

ፕሮፌሰር ገቢሳ በመቀጠል ወደ አሜሪካ ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ በማሽላ ላይ የሚያካሄዱትን ምርምር ቀጥለዋል።

በአሜሪካ ቆይታ ምርምራቸው ስትራይጋ (አቀንጭራ) የተሰኘ ጥገና አረም ላይ በማተኮር እንዲሁም ድርቅን የሚቋቋም ማሽላ ዝርያ ላይ አተኩረው ሰርተዋል።

በዚያ ወቅትም በዕጽዋት ዘረመል ማዳቀል ባገኙት እውቀት የማሽላ ዘርን በማዳቀል ድርቅን እንዲሁም Striga ማቋቋም የሚችል የማሽላ ዘርን ማግኘት ችለዋል።

ፕሮፌሰር በመቶዎች የሚቆጠሩ የተዳቀሉ ዝርያዎችን በማምረት በሰፊው ምርምር ካደረጉ በኋላ በምስራቅ፣ ደቡብ እና ምዕራብ አፍሪካ 34 የተለያዩ ቦታዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ላይ ፍተሻ መደረጉን ያስታውሳሉ።

በዚህም በምረምር የተገኙት የማሽላ ዝርያዎች ከፍተኛ የሆነ አካባቢውን መላመድ ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

አሁን እነዚህ በምርምር የተገኙ የተዳቀሉ የማሽላ ዝርያዎችን በስፋት ለማምረት እና ዝርያውን ለማሰራጨት የሚያስችላቸውን ስርዓት ከአገራቱ ጋር ለመዘርጋት እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተሞከረው የተዳቀለ የማሽላ ዝርያ ከ40 በመቶ በላይ የምርት መጨመር ማሳየቱን አክለው ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ጌትስ ፋውንዴሽን፣ ዩኤስ አይዲ እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ነዋይ በግብርና ምርምር ስራ ላይ እያፈሰሱ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር የአፍሪካ አገራቱም ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ በጀት ለምርምር ስራዎች በመመደብ ላይ መሆናቸውን በማንሳት አድንቀዋል።

በአፍሪካ ባለፉት አስር ዓመታት የተሰሩ መሰረተ ልማቶችም በግብርናው ዘርፍ ለሚደረጉ ምርምሮች ያላቸውን በጎ አስተዋጽኦ በማንሳት “ተመራማሪዎች ለሕይወታቸው ስጋት ሳይገባቸው [በግጭቶች ምክንያት] ምርመራቸውን የሚያከናውኑ ከሆነ ትልቅ ጥቅም አለው” ሲሉ አክለዋል።

“እድሎች አሉ። ነገሮች ተስፋ ሰጪ ናቸው። ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነ ለአፍሪካ በግብርና ላይ የተመሰረተ ልማት ላይ ስኬታማ. . . “ መሆን እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ልውጥ ዘረመል ሰብሎች እና አፍሪካ

ልውጥ ዘረመል (ጂኤም ኦ) ሰብሎች የአፍሪካን ምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ያላቸው ሚና ይኖራቸው እንደሆን የተጠየቁት ፕሮፌሰር ገቢሳ “አዎ አምናለሁ ነገር ግን የአፍሪካን ችግር መሰረት አድርገው መሰራት አለባቸው። እንደዚያ ሲሆን የሚመጡት ቴክኖሎጂዎች ችግሩን ይቀርፋሉ ማለት ነው” ብለዋል።

ሳይንሱ እምቅ አቅም እንዳለው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ ባዮ ቴክኖሎጂ በበርካታ አገራት በግብርና እድገት ላይ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን በማቅለል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይናገራሉ።

ነገር ግን ፈሰስ የሚደረገው መዋዕለ ነዋይ በቀጥታ የአፍሪካውያንን ችግር የሚቀርፍ እና “በአፍሪካ ሁኔታ ውስጥ የሚሰራ ምርት ማምረት አለበት” በማለት ድርቅ እና ስትራይጋ የተሰኘ አረም የሚቋቋም ምርምራቸውን በምሳሌነት ያነሳሉ።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ የቴክኖሎጂ ምርምሮች የአደጉ አገራትን ታሳቢ አድርገው የተሰሩ በመሆናቸው እነርሱን መጥቀማቸውን ያነሱት ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ አሁን የሚደረጉ ምርምሮች እና የሚወጡ መዋዕለ ነዋዮች በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በአፍሪካ ለእርሻ ምቹ የሆነ 60 በመቶ መሬት መኖሩን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ገቢሳ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ትውልድ በእርሻ ስራ ላይ እንዲሳተፍ ቢደረግ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣ ያለቸውን እምነት ይገልጻሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ወደ አህጉሪቱ በስፋት ማስተዋወቅ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዚህ ላይ እንዲሰሩ ቢደረግ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለመፈለግ በተለያየ መንገድ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ።

በአፍሪካ ያለው ሊታረስ የሚችል መሬት ለመስራት ተነሳሽ ለሆነው ወጣት በዘመናዊ ግብርና ላይ እንዲሰማራ ቢመቻችለት አፍሪካ ራሷን ለመመገብ ያላት እድል ከፍተኛ መሆኑን ጨምረው ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እጅ ሜዳሊያ ሲቀበሉ

ፕሮፌሰር ገቢሳ ማን ናቸው?

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ በሆለታ እና ጊንጪ ከተሞች መካከል በምትገኘው ኦሎንኮሚ በምትባል መንደር በ1942 ዓ.ም. ተወለዱ።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ የግብርና ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ የተከታተሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእፅዋት ሳይንስ ከሀሮማያ ኮሌጅ በ1965 ዓ.ም አግኝተዋል።

በ1968 በእፅዋት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ1970 ዓ.ም. በእፅዋት ማዳቀል እና ዘረ መል ምኅንድስና አሜሪካ ከሚገኘው ፑርዱ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ፕሮፌሰር ኤጄታ በእፀዋት ዘረመል ማዳቀልና ዓለም አቀፍ ግብርና ተመራማሪ፣ የፑርዱ ግሎባል የምግብ ዋስትና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ በማሽላ እህል ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2009 የከፋ ድርቅን እና አጥፊ አረምን የሚቋቋም የማሽላ ዝርያ ላይ ባደረጉት ምርምር የዓለም ምግብ ሽልማትን አግኝተዋል።

ምርምራቸው ከፍተኛ የማሽላ ምርትን በመጨመር ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ ረድቷል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ በ2011 በፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የዓለም አቀፍ የምግብ እና ግብርና ልማት ቦርድ ውስጥ እንዲሁም ከ2014 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ጆ ባይደን ብሔራዊ የክብር ሽልማት ከተሸለሙ 21 አሜሪካውያን ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።