
ከ 1 ሰአት በፊት
ጋዛን ለዓመታት ሲያስተዳደር የቆው እና አሁን ከእስራኤል ጋር ከባድ ጦርነት ውስጥ የገባው ፍልስጤማዊው ታጣቂ ቡድን ሐማስ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅስ ይነገራል።
በዚህም የቡድኑ የገንዘብ የዝውውር ሥርዓት ውስብስብ ሲሆን፣ የገቢ ምንጩ ደግሞ ከጋዛ ሰርጥ እስከ መላው ዓለም የተዘረጋ ነው።
ሐማስ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በበርካታ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ ከዓለም አቀፉ የባንክ ሥርዓት እንዲታገድ ቢደረግም፣ የገንዘብ አቅሙ ግን በግልጽ በማይታይ ሁኔታ ከመጋረጃ ጀርባ እያደገ መሆኑ ይነገራል።
ሐማስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን በማስወንጨፍ፣ የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ ድኖቾችን በማብረር እና ሰፊ እና ውስብስብ ዘመቻን በማቀድ እና በመፈጸም እስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸም መቻሉ ያለውን የገንዘብ አቅም ጥንካሬን ያሳያል።
የሐማስ የገንዘብ ምንጭ
ሐማስ እንዴት ለእንቅስቃሴው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያገኛል?
ሐማስ እአአ 1987 የተቋቋመ እስላማዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ክንፎች አሉት።
ኢዘዲን አል-ቃስም ብርጌድ የተሰኘው ወታደራዊ ክንፉ ከዚህ ቀደም በርካታ ጥቃቶችን እስራኤል ላይ ፈጽሟል።
ፖለቲካዊ ክንፉ ደግሞ 50 ሺህ ሠራተኞችን እያስተዳደረ 2.3 ሚሊዮን የሚሆኑ የጋዛ ሰርጥ ነዋሪዎችን ይመራል።
ቡድኑ እንደ አንድ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ድርጅት ከነዋሪዎች ግብር ይሰበስባል፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ እርዳታ እና የገንዘብ ድጋፍ ይቀበላል።
እስላማዊ ቡድኑ ግልጽ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ይታወቃል። በምዕራባውያን የተጣሉበትን ማዕቀቦች ለመሸሽ ደግሞ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ክሪፕቶከረንሲዎችን ይጠቀማል።
ኳታር
ይህች አነስተኛ የባሕረ ሰላጤ አገር የዓለማችን ባለጸጋ ዜጎች መገኛ ናት። ኳታር ከቱርክ ጋር በመሆን ሐማስ እአአ 2007 ከፍልስጤማውያን ቡድኖች መካከል አንዱ ከሆነ ፋታህ ጋር ሲለያይ በብቸኝነት ቡድኑን የደገፉ አገራት ናቸው።
እአአ 2012 ላይ ሐማስ ጋዛን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ በጋዛ ሰርጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ጉብኝነት ያደረጉት የወቅቱ የኳታር ኢሚር ሼክ ሐማድ ቢን ካሊፋ አል-ታኒ ነበሩ። ኢሚሩ በወቅቱ ቃል የገቡት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል ገንዘብ ለሐማስ ተሰጥቷል።
የኳታር ድጋፍ በገንዘብ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። መቀመጫቸውን በሶሪያዋ መዲና ደማስቆ ያደረጉ የሐማስ መሪዎች በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በአገሪቱ መቆየት ስላልቻሉ ወደ ዶሃ እንዲዘዋወሩ የኳታር መንግሥት ይሁንታን አግኝተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሐማስ ዋና ኃላፊ ተደርጎ የሚታሰበው እስማኢል ሃኒያህ ዋና መቀመጫው ኳታር ዶሃ ነው።
ከዚህ ቀደም ሐማስ እና እስራኤልን የማደራደር ኃላፊነት በአብዛኛው ለግብፅ የተተወ ጉዳይ ነበረ። አሁን አሁን ግን ኳታር የዋነኛ አደራዳሪነት ሚናን ስትጨብጥ፣ ግብፅ ደግሞ በድርድሮች ላይ የተሳታፊ ሚናን እያዘች መጥታለች።
በቅርቡም እስራኤል እና ሐማስ ለጦርነት ፋታ ሰጥተው ጊዘያዊ የተኩስ አቁም ባደረጉበት ጊዜ ታጋቾች እና እስረኞች እንዲለቀቁ ያስቻለው ስምምነት የተደረሰው በኳታር አደራዳሪነት ነው።
አገሪቱ አሁንም ቢሆን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ኳታር ለሰብዓዊ ተግባራት የሚውል ገንዘብ ነው በማለት ባለፉት በርካታ ዓመታት በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ጋዛ ስትልክ ቆይታለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁ የአሜሪካ ጦር ሰፈር መገኛ የሆነችው ኳታር የምትልከው ገንዘብ ለፍልስጤማውያን እንጂ ለሐማስ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።
- ሐማስ ከእስራኤል አፍንጫ ስር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ እንዴት ኃይሉን መገንባት ቻለ?29 ህዳር 2023
- እስራኤል ልታጠፋው ቀን ከሌት የምትፈልገው በጋዛ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነው?23 ህዳር 2023
- በሞት ጥላ ስር ሆነው እስራኤልን እንቅልፍ የነሷት የሐማስ መሪዎች እነማን ናቸው?14 ጥቅምት 2023

ኳታር በእርዳታ መልክ ወደ ጋዛ የላከችው የገንዘብ ትክክለኛ መጠን ባይታወቅም፤ ተንታኞች ከእአአ 2014 ጀምሮ ኳታር ከ1 ቢሊዮን እስከ 2.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሳትልክ አትቀርም ብለው የሚገምቱ ሲሆን፣ ይህ ገንዘብ ከእስራኤል ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውጊያዎች የወደመችውን ጋዛ ሰርጥን መልሶ ለመገንባት ጥቅም ላይ ውሏል ይላሉ።
እአአ 2016 ላይ የኳታር ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐሚድ አል-ታኒ “በጋዛ ሰርጥ ያሉ ወንድሞች በሰፋሪው የእስራኤል ኃይል በተጣለባቸው ማዕቀብ ምክንያት ከገቡበትን የፋይናንስ ቀውስ ለማውጣት ኳታር 30 ሚሊዮን ዶለር መድባለች” ብለው ነበር።
ይህ ገንዘብ በየወሩ ተከፋይ ሲደረግ የቆየ ሲሆን፣ 50 ሺህ ለሚሆኑት የጋዛ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል እና እጅግ ደሃ ለሆኑ የቤተሰብ አባላት በየወሩ የ100 ዶላር ድጋፍ ለማድግ ጥቅም ላይ ውሏል።
ይህ ገንዘብ ታዲያ ሲተላለፍ የነበረው በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገበት እንደነበረ በኳታር የሚገኘው ሚድል ኢስተርን ስተዲስ አት ኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ካሊድ አል ሃሩብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በጋዛ ጨምሮ በፍልስጤማውያን ግዛቶች የሚደርሰው ዶላር በዓለም ከፍተኛው ቁጥጥር የሚደረግበት ገንዘብ ነው። አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ዮርዳኖስ እና ግብፅ በባንኮቻቸው በኩል ገንዘቡን እያዘዋወሩ ከፍተኛ ክትትል ያደርጉበታል” ብለዋል በሐማስ ዙሪያ በርካታ ጹሑፎችን የጻፉት መምህር።
የኳታር ገንዘብ ከዶሃ ወደ እስራኤል ይላካል። ከዚያም በኳታር ወኪሎች አማካኝነት ጥሬ ገንዘብ ወደ ጋዛ ተወስዶ ለደሞዝተኞች በፖስታ ቤት በኩል ሲላክላቸው ለተረጂዎች ደግሞ በሱፐርማርኬቶች አማካኝነት በቀጥታ እንዲደርሳቸው ይደረጋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ተንታኞች በገንዘቡ ላይ የትኛውንም ያህል ቁጥጥር ቢደረግ የተወሰነው ገንዘብ በሐማስ ወታደራዊ ክንፍ እጅ መግባቱ አይቀሬ ነው ይላሉ።
ሐማስ ግን በእርዳታ የሚገባው ገንዘብ እኔ ኪስ አይገባም ይላል። አል ሃሩብም ቢሆኑ ለእርዳታ ተብሎ የሚመጣው ጥሬ ገንዘብ ሐማስ ጋር ስለመድረሱ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም ይላሉ።
“የሐማስ ዋነኛው ኢኮኖሚያዊ ችግር የፖለቲካ ወይም የጦር ክንፉን በገንዘብ ማጠናከር አይደለም። ይህ ለሐማስ ቀላሉ ነገር ነው። የሐማስ ዋነኛው ፈተና በችግር ውስጥ ያሉትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን መደገፍ ነው። በዚህም ጫና አለበት” ይላሉ።
የኳታር የእርዳታ ገንዘብም ቢሆን ለፍስልጤማውያን ጊዜያዊ ችግር መፍቻ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አልሰጣቸውም።
በፍልስጤም ትልቁ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋም ነው። ይህም እርዳታ ቁጥጥሮችን ካለፈ በኋላ በራሱ ሠራተኞች አማካይነት ለተረጂዎች እንደሚሰጥ ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም በየዓመቱ በፍልስጤማውያን ግዛት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በገለልተኛ አካል ወጪዎቹ ይመረመራሉ።
ኢራን
ሐማስ ከሶሪያ እና ከሌባኖሱ እስላማዊ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር በመሆን ኢራን የምትመራው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚዝታንስ’ የተባለው ጥምረት አካል ነው።
እነዚህን ኃይሎች አንድ የሚያደርጋቸው ለእስራኤል እና ለአሜሪካ ያላቸው ጥላቻ ነው።
የቻተም ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ሳናም ቫኪል፣ ኢራን የራሷን ኅልውና ለማረጋገጥ ስትል እና የእስራኤልን ተጽእኖ ፈጣሪነት ለመቆጣጠር በቀጠናው ያሉ መሰል ቡድኖችን በአንድ አደራጅት በገንዘብ፣ በሥልጣና እና በጦር መሳሪያ አቅርቦት እየደገፈች ነው ይላሉ።
ኢራን ከሐማስ በተጨማሪ ሌሎች የፍልስጤም ቡድኖች ከእአአ 1990ዎቹ ጀምሮ ስትደግፍ ቆይታለች ሲሉም ቫኪል ያክላሉ።
እንደ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከሆነ ኢራን ፍልስጤማውያን ቡድኖች ለሆኑት ሐማስ፣ ኢስላሚክ ጂሃድ እና የፍልስጤም ነጻነት ሕዝባዊ ግንባር በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር ትሰጣለች።

ምንም እንኳ በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት የሐማስ እና የኢራን ፍላጎት ቢለያየም ቴህራን ለእስላማዊ ቡድኑ የምታደርገውን ድጋፍ አላቋረጠችም።
በሶሪያ ጦርነት ወቅት ኢራን ለባሻር አል-አሳድ ያልተቋረጠ ድጋፏን ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፣ ሐማስ ግን ከቴህራን በተቃራኒ ቆሞ ነበር የሚሉት የዋሽንግተን ኢንስቲትዩት ፎር ኒር ኢስት ፖሊስ ተንታኝ የሆኑት ማቲው ሌቪት ናቸው።
እንደ አል ሃሩብ ከሆነ ምንም እንኳ የገንዘቡ መጠን ግልጽ አይሁን እንጂ በትክክል ሐማስ ከኢራን ገንዘብ ይቀበላል።
የሐማስ መሪ እስማኤል ሃኒያህ አል-ጃዚራ ላይ ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ቡድናቸው ከኢራን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚቀበል በግልጽ ተናግረው ነበር።
እአአ 2022 በተካሄደው ቃለ መጠይቅ ላይ የሐማሱ መሪ ለቡድናቸው ከፍተኛ ድጋፍ የምትሰጠው ኢራን መሆኗን እና ለሐማስ የሚሳኤል ሥርዓት ግንባታ 70 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ተናግረው ነበር።
ከመስከረም 26ቱ ጥቃት በኋላ ደግሞ አሊ ባራክ የተባሉት የሐማስ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ለሩሲያ ቴሌቪዢን ጣቢያ ሲናገሩ፣ ኢራን የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ በመስጠት ቀዳሚዋ አገር ነች ብለዋል።
ቢቢሲ ኢራን ለሐማስ ታደርጋለች ስለተባለው ድጋፍ ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።

ግብር
የፍልስጤም ግዛት የሆነችውን ጋዛን እንደሚያስተዳደር ገዢ፤ ሐማስ ከወጪ ገቢ እንዲሁም ከንግድ እንቅስቃሴዎች ግብር ይሰበስባል። ይህ ከጋዛ ሰርጥ የሚሰበሰበው ግብር መጠን ግን ምን ያክል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም።
እአአ 2016 ላይ የጋዛ የፋይናንስ ሚኒስቴር ከግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ 15 ሚሊዮን ነው ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አሃዝ አሁን ላይ ከ300 አስከ 450 ሚሊዮን ዶላር ሊሆን እንደሚችል ተንታኙ ማቲው ሌቪት ይገምታሉ።
ሐማስ ከግብር ምን ያህል እንደሚያገኝ በትክክል ባይታወቅም፤ አንድ እውነታ ግን ሐማስ የጣለው ግብር ከፍ ያለ ነው ይላሉ ተንታኙ።
ከጦርነቱ በፊት 80 በመቶ ሕዝብ እርዳታ ጠባቂ እና 45 በመቶ ነዋሪ ሥራ አጥ በሆነባት ጋዛ ሰርጥ ሐማስ በነዋሪው ላይ የጣለው ግብር እጅግ ከፍተኛ ነው።
አል ሃሩብ እንደሚሉት ከሆነ ሐማስ በሲጋራ፣ በጂንስ ልብሶች፣ በተሸከርካሪዎች እና መሠረታዊ አይደሉም ተብለው በሚፈረጁ የምግብ ምርቶች ላይ በየዓመቱ የግብር መጠን ሲጨምር ቆይቷል።
ኢንቨስትመንት
እንደ የአሜሪካ ግምጃ ቤት የውጭ ንብረቶች ተቆጣጣሪ ቢሮ ከሆነ ሐማስ በሱዳን፣ በቱርክ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በአልጄሪያ እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በተለያዩ መስኮች ፈሰስ ያደረገው 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት አለው።
ዋሽንግተን ሐማስን አሸባሪ ድርጅት ብላ በመፈረጇ ከሐማስ ጋር ግብይት በሚፈጽሙት ላይ ቅጣት ትጥላለች።
አሜሪካ ከሐማስ ጋር ግብይት ፈጽመዋል በማለት ከለየቻቸው ኩባንያዎች መካከል የሱዳኑ ማዕድን አውጪ ኩባንያ፣ የቱርክ ቤት አልሚ ኩባንያ እና የሳዑዲ የግንባታ ድርጅት ተጠቃሽ ናቸው።

ክሪፕቶከረንሲ እና ልገሳዎች
ሌላኛው የሐማስ የገንዘብ ምንጭ በፍልስጤም ግዛቶች፣ በአረብ አገራት እና በተቀረው ዓለም ከሚገኙ ደጋፊዎቹ በልገሳ መልክ የሚያገኘው ገንዘብ ነው ይላሉ አል ሃሩብ።
እስላማዊ አስተምርሆን መሠረት በማድረግ ሐማስ ለትምህርት ቤቶች እና ለሆስፒታሎች ግንባታ ሰዎች ገንዘብ እንዲለገሱ ይጠይቃል ይላሉ ፍልስጤማዊው አል ሃሩብ።
አል ሃሩብ ከሁለተኛው የፍልስጤማውያን አመጽ (ኢንቲፋዳ) በኋላ አሜሪካ “በሽብር ላይ ጦርነት” ባወጀጅ ማግስት ሐማስ በጋዛ ብቻ ከአርብ ጸሎት በኋላ በአንድ ቀን ከ1.5 አስከ 2 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ ችሎ እንደነበረ ይገልጻሉ።
ሐማስ ለሰብዓዊ ድርጅቶች ብሎ ገንዘብ ሲሰበስብ “ገንዘቡን ለሐማስ ብሎ ሳይሆን በደም የተጨማለቀ የሕጻን ልጅ ፎቶ በማሳየት ነው” የሚሉት ማቲው ሊቪት፤ አብዛኛው ለሰብዓዊ ተግባራት ተብሎ የሚሰበሰበው ገንዘብ መጨረሻው ለሐማስ ወታደራዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ ነው የሚውለው ይላሉ።
እአአ 2019 ላይ ሐማስ ልገሳዎችን በክሪፕቶክረንሲ ሲቀበል ነበር።
“ልገሳዎች በክሪፕቶከረንሲ እንዲሆን በመጠየቅ ሐማስ የመጀሪያው ነው” የሚሉት የብሎክቼይን ቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው ቲአርኤም ላብስ ባልደረባ የሆኑት አሪ ሬድቦርድ ናቸው።
በተለመደው መልክ ጥሬ ገንዘብ ማዘዋወር የሚያስከትለውን ተጠያቂነት በሚያስቀር መልኩ ሰዎች ማንነቻቸውን ይፋ ሳያደርጉ እና በፍጥነት ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ በክርሪፕቶከረንሲ አማካይነት ማዘዋወር ይቻላቸዋል።
ይሁን እንጂ እስራኤል እና አሜሪካ ውስብስብ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም በክሪፕቶከረንሲ አማካይነት ለሐማስ ገንዘብ የሚለገሱ ግለሰቦችን እና ተቋማትን መለየት ችለዋል።
እንደ ቲአርኤም ላብስ ከሆነ እአአ 2020 ላይ የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ ከሐማስ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 150 የክሪፕቶካረንሲ አድራሻዎችን ወርሷል።
በቅርብ ዓመታት ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አድራሻዎችም በእስራኤል ተወርሰዋል። ይህም ሐማስ በክሪፕቶ አማካይነት ልገሳዎችን መቀበል አቁሚያለሁ እንዲል አስገድዶታል።