የአራት ወር ሕጻን
የምስሉ መግለጫ,ከአውሎ ንፋሱ የተረፈው የአራት ወር ሕጻን እና የአንድ ዓመት ወንድሙ

ከ 7 ሰአት በፊት

በአሜሪካ፣ ቴኒሲ ውስጥ በአውሎ ንፋስ ተወስዶ የነበረው የአራት ወር ሕጻን በሕይወት መትረፉን ቤተሰቦቹ ተናገሩ።

“በፈጣሪ ቸርነው ነው የተረፈው” ብለዋል።

አውሎ ንፋሱ ተንቀሳቃሽ ቤታቸውን ይዞት እንደሄደና ቤቱ ውስጥ ልጃቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ልጃቸው ዛፍ ላይ በሕይወት እንደተገኘም አክለዋል።

የልጃቸው የአንድ ዓመት ወንድም እንዲሁም እናትና አባት አነስተኛ ጉዳት ብቻ ደርሶባቸው ተርፈዋል።

የ22 ዓመቷ እናት ሲድኒ ሞር እንዳለችው አውሎ ንፋሱ ሲመጣ የቤታቸውን ጣርያ ገንጥሎታል።

“ልጄ ሎርድ ቤቱ ውስጥ እያለ ነው በአውሎ ነፋሱ ቤቱ የተንሳፈፈው” ብላለች።

የልጁ አባት ሎርድን በመያዝ ለማዳን ቢሞክርም ሳይቻለው ቀርቷል።

“አውሎ ንፋሱ ሲያሽከረክረው ለመያዝ ቢሞክርም አልሆነም” ብላለች እናትየዋ።

ይሄ ሁሉ ሲሆን እናትየዋ የአንድ ዓመት ልጇ ፕሪንስተንን አቅፋው ነበር።

“እየሮጥኩ ልጄን አቀፍኩት። መተንፈስ አቅቶኝ ነበር” ትላለች።

አውሎ ንፋሱ ሲያልፍ የአራት ወር ልጃቸው ሎርድን መፈለግ ጀመሩ።

ዝናብ እየዘነበ ልጃቸው እየፈለጉት ሳለም ዛፍ ላይ መገኘቱን ትናገራለች።

“እንደሞተ ነበር ያሰብኩት። ግን ተረፈ። በፈጣሪ ቸርነት ተረፈ” ብላለች።

ቤታቸውና መኪናቸው በአውሎ ንፋሱ ስለወደመ በጎ ፈንድ ሚ ገንዘብ እያሰባሰቡ ይገኛሉ።

ገንዘብ እያሰባሰቡ ባለበት የበይነ መረብ ገጽ ላይ ከአውሎ ንፋስ የተረፈው ልጃቸው ሎርድ ሲገኝ “ዛፉ ላይ በደንብ ተቀምጦ ነው ያገኘው። መላዕክት ናቸው የጠበቁትና ወደዚያ የወሰዱት” ብለው ቤተሰቦቹ ጽፈዋል።

“ለልጆቼ ሟች ነኝ። አባታቸውም እንደዚያው” ስትል እናትየው አክላች።