December 16, 2023

” ጥናቱ ባካለላቸው ወረዳዎች 36 ሰዎች በድርቅ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል ” – ረዳት ፕሮፌሰር አምሳሉ ደረጀ

የደባርቅ ዩኒቨርስቲ 8 አባላት ባሉት የጥናት ቡድን በመመደብ በሰሜን ጎንደር ዞን የተከሰተውን ድርቅ መጠንና ስፋት ያጠና ሲሆን ውጤቱንም ይፋ ማድረጉን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሰምቷል።

ይህንን በተመለከተ የጥናት ብድኑ ስብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር አምሳሉ ደረጀ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጻ ሰጥተው ነበር።

ምን አሉ ?

– ጥናቱ ከመስከረም 28 እስከ ህዳር 20 2016 ዓ.ም የተካሄደ ነው። ጥናቱ ድርቅ በጃናሞራ፣ በበየዳና በጠለምት ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎችን ላይ የተካሄደ ነው።

– ጥናቱ ድርቁ በእነዚህ አከባቢዎች (በሦስቱ ወረዳዎች) በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል። 73 ሺህ 387 የቤት እንስሳትም በዚሁ ምክንያት #መሞታቸውን አረጋግጧል።

– በበየዳና ጃናሞራ ወረዳ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚኖሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዋል። 16ሺ 650 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተቸግረዋል። 292 ተማሪዎች አካባቢውን ለቀው ጠፍተዋል።

– ጥንቱ ባካለላቸው ወረዳዎች 36 ሰዎች በድርቅ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። የድርቁ ተጎጅዎች ድርቅን እንዲቋቋሙት ለማስቻል አስቸኳይ የምግብ የውኃ አቅርቦት ማቅረብ ይገባል።

ጥናቱ እንደመፍትሄ ምን አቀረበ ?

* የትክልትና ፍራፍሬ ዘር ማቅረብ፤
* የእንሰሳት መኖ ማቅረብ፤
* የእንሰሳት ክትባት  ማካሄድ፤
* የመድሂኒት ግዥና አቅርቦት፤
* የትምህርት ቤት ምግብ ፕሮግራም መጀመር፤
* የቤት ለቤት ልየታና ህክምና ማካሄድ
* የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በአንድ አካባቢ እንዲማሩ መርዳት ይገኙበታል።

የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል  ፦

° በዞኑ በ6 ወረዳዎች በሚገኙ 83 ቀበሌዎች በተከሰተ የድርቅ አደጋ ከ 452 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለድርቅ አደጋ ተጋልጠዋል።

° በሰብል የተሸፈነ 34 ሺህ ሄክታር መሬት በድርቅ ተጎድቷል።

° ለህብረተሰቡና ለእንሰሳት አግልግሎት የሚሰጡ የውኃ ተቋማት ደርቀዋል።

° ድርቁ በ100 የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ላሉ 54 ሺ 406 ተማሪዎች እንቅፋት ሆኗል።

° የፌደራል መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 239 ሺህ 400 የድርቁ ተጎጅዎች የምግብ እህል ለማዳረስ እየሰራ ነው። እስካሁን ለ177ሺ 100 ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እህል ማድረስ ተችሏል።

° በክልል መንግስት 5 ሺህ 100 ኩንታል፤ በሌሎች ረጅ ድርጅቶች ደግሞ 7 ሺህ 73 ኩንታል እህል ድጋፍ ተደርጎል።

° ከተረጅው ብዛት አኳያና የድርቁ ተጎጅዎች መጠን እያደገ በመምጣቱ አሁንም ሰፊ ድጋፍ ያስፈልጋል።

° በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ ርብርብ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። አሁንም መቀጠል ይገባል።

መረጃውን አዘጋጅቶ የላከው የጎንደር የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተስብ አባል ነው።