
17 ታህሳስ 2023, 08:47 EAT
ጃኮብ ዙማ አዲስ ፓርቲ መመሥረታቸውንም ይፋ አደረጉ። ፓርቲው በመጪው ምርጫ ገዢውን ኤኤንሲን ይፎካከራል ብለዋል።
ዙማ ትናንት በሰጡት መግለጫ ከእንግዲህ ለገዢው ፓርቲ ማለትም የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ፣ በእንግሊዝኛው ምሕጻር ኤኤንሲ (ANC ) ድምጽ አልሰጥም ብለዋል።
ዙማ ይህን ፓርቲ ወክለው ተወዳድረው እንደ አውሮፓዊያኑ ከ2009 እስከ 2018 ዓ/ም ደቡብ አፍሪካን በፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው አይዘነጋም።
አዲስ የመሠረቱት ፓርቲ በምሕጻሩ ‘ኤምኬ’ (MK) የሚል ስም ተሰጥቶታል። ይህ ስም በቀድሞው የኤኤንሲ ፓርቲ የትጥቅ ትግል ክንፍ ስም ነበር።
ዙማ በመግለጫቸው በዚህ ወቅት ለኤኤንሲ እና ለአሁኑ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ድምጽ መስጠት ‘እንደ ክህደት እቆጥረዋለሁ’ ብለዋል።
ኤምኬ በአፓርታይድ ዘመን ትጥቅ ትግሉን ይመራ የነበረ ታጣቂ ክንፍ ሲሆን ያኔ ዙማ የክንፉ አባል ነበሩ።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1993 ማንዴላ የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው ቀደም ብሎ ይህ የትጥቅ ትግል ይመራ የነበረው ክንፍ እንዲበተን ሆኖ ነበር።
‘ፓርቲው ከያኔው ተመሳሳይ ነው፤ ልዩነቱ አሁን በጦር ሳይሆን በድምጽ ሥልጣን እናገኛለን’ ብለዋል ዙማ።
ዙማ በሶዌቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ረዥም ንግግር ለማድረግ ጤንነት እየተሰማቸው ስላልሆነ መግለጫውን ከሴት ልጆቻቸው አንዷ እንድታነበው አድርገዋል።
- በግጭቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ወሳኝ የምርምር ሥራቸው መስተጓጎሉን ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ገለጹ16 ታህሳስ 2023
- ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ አጭር ፊልም ታዋቂ ሽልማትን ያገኘው ወጣት ኢትዮጵያዊ17 ታህሳስ 2023
- የንግሥቲቱን ከፍተኛ ሽልማት አልቀበልም ያለው እንግሊዛዊው ገጣሚ ቤንጃሚን17 ታህሳስ 2023
ዙማ በመግለጫቸው “ኤኤንሲ ታላቅ ፓርቲ የነበረና አገሪቱን ከአፓርታይድ ሥርዓት ያወጣና ልንሞትለት የተዘጋጀንለት ቢሆንም አሁን ያለው ኤኤንሲ ግን በተቃራኒው መሆኑ ሐዘን ላይ ጥሎኛል” ብለዋል።
ዙማ “ለኤኤንሲ እሞታለሁ” ካሉ በኋላ ነገር ግን ፓርቲው አሁን ‘የማውቀው ፓርቲ አልሆንልህ አለኝ’ ሲሉ ተናግረዋል።
ኤኤንሲ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚሸነፍ እጠብቃለሁ ያሉት ዙማ ለታላቁ ፓርቲ ውድቀት የአሁኑን መንግሥት ተጠያቂ አድርገዋል።
በተለይም ፕሬዝዳንት ራማፎሳን ፓርቲውን ለማጥፋት ከነጮች ጋር እያሴሩ እንደሆነ ከጠቆሙ በኋላ ፓርቲው በጥቁር ምሁራን ላይ ፊቱን አዙሯል ሲሉ ከሰዋል።
“በምንም መልኩ ራማፎሳ ለሚመሩት ኤኤንሲ ልንቀሳቀስ አልችልም” ብለዋል ዙማ።
ያን ማድረግ እንደ ክህደት እንደሚቆጥሩት ደጋግመው የተናገሩት ዙማ ፓርቲው በባንዳዎችና ለአፓርታይድ ያጎበደዱ ሰዎች ተጠልፏል ሲሉ ተችተዋል።
በዚህም የተነሳ ድምጼን የምሰጠው አዲስ ለመሠረትኩት ኤምኬ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ዙማ፣ በደቡብ አፍሪካ እውነተኛ እርቅ ሊመጣ የሚችለው በዚያች አገር የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕና እኩልነት ሲሰፍን ብቻ ነው ብለዋል።
በአፓርታይድ ሥርዓት ዘመን ዙማ ቀዳሚ ከሚባሉ ታጋዮች አንዱ የነበሩ ሲሆን 10 ዓመት በእስር ቤት አሳልፈዋል።
በፕሬዝዳንትነት ከተመረጡ በኋላ ደግሞ በርካታ የሙስና ክሶች ቀርበውባቸዋል።
ዙማ በፓርቲው ከፍተኛ ጫና ተደርጎባቸው በፈረንጆቹ 2018 ከሥልጣን የለቀቁ ሲሆን ያን ጊዜ ነበር ራማፎሳ ዙማን ተክተዋቸው ወደ ሥልጣን የመጡት።
ዙማ በ2021 ዓ/ም ደግሞ ፍርድ ቤትን በመዳፈር ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ነውጥ የተቀሰቀሰ ሲሆን 350 ሰዎች ሞተዋል።
ዙማ ለሁለት ወራት ከታሰሩ በኋላ ከጤና ጋር በተያያዘ ከእስር ተለቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ምርጫ ታደርጋለች። ከነጻነት ወዲህ በብቸኝነት እየመራ ያለው ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ ከፍተኛ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ይገመታል።