
17 ታህሳስ 2023
የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ተቃርቧል። ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን የምታስተናግደው አይቮሪ ኮስት ዝግጅቷን አጠናቃለች።
ውድድሩ ከአንድ ወር በኋላ ቅዳሜ ጥር 4/2016 ዓ.ም. አቢጃን በሚገኘው አላሳኔ ኦዋታራ ስታድየም አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ከጊኒ ቢሳው በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል።
ሰባት ጊዜው ዋንጫውን በማንሳት ክብረ-ወሰን የጨበጠችው ግብፅም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በመክፈቻው ሰሞን ከሚያደርጉ ቡድኖች መካከል ናት።
የቀደመውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችው ሴኔጋል ደግሞ ሰኞ ጥር 6 በምድብ ሐ ከጋምቢያ ጋር ጨዋታዋን በማድረግ ውድድሩን ትጀምራለች።
የዘንድሮው ውድድር ምን ይመስላል? ተጠባቂ ጨዋታዎች የትኛቹ ናቸው?
እነሆ የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሠረታዊ መረጃዎችን እንዲህ አቅርበናል።
የምድብ ድልድል
24 አገራት በስድስት ምድቦች ተደልድለው ይፋለማሉ።
አዘጋጇ አገር በምድብ ‘ኤ’ ከሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳው ጋር ትፋለማለች።
ምድብ ‘ቢ’ የሞሐመድ ሳለህ ግብፅ እና ጋና የሚገኙበት ሲሆን፣ የቀድሞው የኒውካስል እና ብራይተን አሠልጣኝ ክሪስ ሁቶን ጋና ይዘው ወደ አይቮሪ ኮስት ይጓዛሉ።
ኬብ ቨርድ እና ሞዛምቢክ ምድብ ‘ቢ’ ውስጥ ይገኛሉ።
የአምናው ዋንጫ አሸናፊ ሴኔጋል በምድብ ‘ሲ’ ስትደለደል፤ በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር የሆነችው ሞሮኮ በመጨረሻው ምድብ ትገኛለች።
እነሆ ምድቦቹ፡
- ምድብ ኤ፡ አይቮሪ ኮስት፣ ናይጄሪያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳው
- ምድብ ቢ፡ ግብፅ፣ ጋና፣ ኬፕ ቨርድ እና ሞዛምቢክ
- ምድብ ሲ፡ ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ ጊኒ እና ጋምቢያ
- ምድብ ዲ፡ አልጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሞሪታኒያ እና አንጎላ
- ምድብ ኢ፡ ቱኒዚያ፣ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አንጎላ
- ምድብ ኤፍ፡ ሞሮኮ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ዛምቢያ እና ታንዛኒያ
- በቱርክ ሱፐር ሊግ አንድ ዳኛ ክፉኛ መደብደባቸውን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ሊጉ እንዲቋረጥ አዘዘ12 ታህሳስ 2023
- ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የባይናንስ ማስታወቂያ በመሥራቱ የ1 ቢሊዮን ዶላር ክስ ተመሠረተበት30 ህዳር 2023
- የካፍ ሽልማት: ቪክተር ኦሲምሄን የዘንድሮው ሽልማት ያመልጠው ይሆን?9 ታህሳስ 2023
የጨዋታዎች ሰዓት
ከመክፈቻው ጨዋታ በኋላ በቀን ቢያንስ ሁለት ጨዋታዎች እስከ ምድብ ፍልሚያዎች መጨረሻ ድረስ ይካሄዳሉ።
የምድብ ጨዋታዎች የሚካሄዱት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ቀን 8፡00፣ 11፡00 እና ምሽት 4፡00 ሲሆን በጥሎ ማለፍ ጊዜ ቀን 8፡00 የሚደረገው መርሐ ግብር ይቀራል።
ከየምድቡ ሁለት ከፍተኛ ነጥብ ያላቸው አገራት ቀጥታ ሲያልፉ፣ አራት ምርጥ ሦስተኛ ቡድኖችም ወደ ዙር 16 ይሸጋገራሉ።
ስታድየሞች
አገሪቱን ለሁለት ከከፈለው የእርስ በርስ ጦርነት 12 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን የምታስተናግደው አይቮሪ ኮስት በአውሮፓውያኑ 1984 ይህን ውድድር ማዘጋጀቷ ይታወሳል።
ለ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ስድስት ስታድየሞች ተዘጅተዋል። ሁለቱ በዋና ከተማዋ አቢጃን የሚገኙ ናቸው።
- አላሳኔ ኦታራ ስታድየም – አቢጃን [60 ሺህ ታዳሚ]
- ፌሊክስ ሆፌት-ቦይኚ ስታድየም – አቢጃን [33 ሺህ ታዳሚ]
- ቻርልስ ኮናን ባኒ ስታድየም – ያሞሶውክሮ [20 ሺህ ታዳሚ]
- ስታዴ ዴ ላ ፔይ ስታድየም – ቦዋኬ [40 ሺህ ታዳሚ]
- አማዱ ጎን ኩሊባሊ ስታድየም – ኮርሆጎ [20 ሺህ ታዳሚ]
- ሎሬንት ፖኩ ስታድየም – ሳን ፔድሮ [20 ሺህ ታዳሚ]
አንዳንዶቹ ስታድየሞች አዲስ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲሆኑ የታደሱ ናቸው። መንግሥት ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል።
ለወትሮው ሰኔ እና ሐምሌ የሚደረገው የአህጉሪቱ ትልቁ የስፖርት ውድድር ዝናባማውን ወቅት ለመሸሽ ሲባል በወርሃ ጥር እንዲደረግ ተወስኗል።
ለዋንጫ የሚጠበቁ አገራት
በርካቶች ባለፈው ካሜሩን ባዘጋጀችው ውድድር ዋንጫ ያነሳችው ሴኔጋል ድጋሚ ታነሳለች የሚል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ከሴኔጋል ከዋክብ መካከል ሳዲዮ ማኔ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ እና ግብ ጠባቂው ኤድዋርዶ ሜንዲ ወደ ሳዑዲ በማቅናት ለሱፐር ሊግ ቡድኖች በመጫወት ላይ ይገኛሉ።
ነገር ግን የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አዳዲስ ተጫዋቾችንም አፍርቷል። የቶተንሃሙ ፓፔ ማታር ሳር እና የማርሴው ኢሊማን ንዲያዬ የሚጠቀሱ ናቸው። በቅርቡ የአፍሪካ ምርጥ ታዳጊ ተጫዋች የተባለው ላሚን ካማራም ይገኝበታል።
አልጄሪያ፤ ምንም እንኳ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ደካማ አቋማ ብታሳይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ ቡድን የገነባች ትመስላለች።
የሪያድ ማሕሬዝ አገር በወዳጅነት ጨዋታ ሴኔጋልን የረታች ሲሆን፣ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ መጠናከሯን አሳይታለች።
በኳታር የዓለም ዋንጫ አስደናቂ አቋም ያሳየችው እና የውድድሩ ክስተት የነበረችው ሞሮኮ የዘንድሮውን ዋንጫ ሊያነሱ ይችላሉ ከተባሉ አገራት መካከል ናት።
አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት እንደ ዲዲዬ ድሮግባ እና ያያ ቱሬ ያሉ ግዙፍ ስሞችን ባትይዝም ለዋንጫው ግምት ከተሰጣቸው ተርታ ትመደባለች።
ሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው ግብፅ እንዲሁም ካሜሩን፣ ናይጄሪያ እና ጋናም ይጠበቃሉ።