
17 ታህሳስ 2023, 08:29 EAT
የእስራኤል ጦር በጋዛ ታግተው የነበሩ ሶስት ዜጎቹን ተኩሶ በገደለበት ወቅት ነጭ ጨርቅ እያውለበለቡ እንደነበር አስታወቀ።
እስራኤል ሶስት የታገቱ ዜጎቿን ተኩሳ የገደለችው በስህተት መሆኑንም አስታውቃለች።
የእስራኤል መከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣን “ከጦሩ አሰራር ጋር የሚቃረን ነው” እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃም ምርመራ መከፈቱንም ተናግረዋል።
በእስራኤል ጦር አርብ ዕለት የተገደሉት ታጋቾች የ28 አመቱ ዮታም ሃይም፣ የ22 ዓመቱ ሳመር ታላላካ እና የ22 አመቱ አሎን ሻምሪዝ መሆናቸውም ተገልጿል።
የታጋቾቹ መገደልንም ተከትሎ በጋዛ የቀሩት ከ120 በላይ ታጋቾችም እንዲለለቀቁ ከስምምነት ላይ እንዲደረስ በባለስልጣናቱ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና በርትቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረገችው ያለችውን የተቀናጀ ጥቃት አታቋርጥም ብለዋል።
“ታጋቾችን ለማስመለስም ሆነ ድልን ለመቀናጀት ወታደራዊ ጫና አስፈላጊ ነው። ያለ ወታደራዊ ጫና ምንም የለንም” ሲሉም ተናግረዋል።
ሐማስ በበኩሉ “በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እስካልቆመ ድረስ” ታጋቾችን ለመልቀቅ ምንም አይነት ድርድር እንደማይኖር ለአደራዳሪዎች ተናግረዋል።
- የእስራኤል ጦር ሦስት ታግተው የነበሩ የገዛ ዜጎቹን በስህተት መግደሉን አስታወቀ16 ታህሳስ 2023
- የንግሥቲቱን ከፍተኛ ሽልማት አልቀበልም ያለው እንግሊዛዊው ገጣሚ ቤንጃሚን17 ታህሳስ 2023
- ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ አጭር ፊልም ታዋቂ ሽልማትን ያገኘው ወጣት ኢትዮጵያዊ17 ታህሳስ 2023
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን እንደተናገሩት ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን የነበሩት ሶስት ታጋቾች ከህንጻ ሲወጡ መታየታቸውን ነው። ከሶስቱ አንዱ በዱላ ላይ የተጠመጠመ ነጭ ጨርቅ እያውለበለበ እንደነበርም የእስራኤል መከላከያ የመጀመሪያ ምርመራው ግኝት ያሳያል ብለዋል።
ታጋቾቹ በአስር ሜትሮች ርቀት ላይ የነበሩ ሲሆን ከእስራኤል ወታደሮች አንዱም “አሸባሪ” ሲል ተኩስ እንደከፈተባቸው እኚሁ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል። ሁለቱ ወዲያውኑ ሲገደሉ ሶስተኛው ቆስሎ ወደ ህንጻው ተመልሷል።
የድረሱልኝ እርዳታ ጩኸት በዕብራይስጥ ቋንቋ መሰማቱንም ተከትሎ የጦሩ አዛዥ ወታደሮቹ መተኮሳቸውን እንዲያቆሙ አዘዙ።
የቆሰለው ታጋች እንደገና ብቅ ባለበትም ወቅት በጥይት ተመትቶ መገደሉንም ባለስልጣኑ አስረድተዋል።
ታጋቾቹ አምልጠው ወይም አጋቾቻቸው ትተዋቸው ሄደው ሊሆን እንደሚችልም ባለስልጣኑ አክለዋል።