
17 ታህሳስ 2023, 09:19 EAT
በእስራኤል የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት የተገደለው የአልጀዚራ የካሜራ ባለሙያ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ።
ሳመር አቡዳቃ እስራኤል በደቡባዊቷ ጋዛ ኻን ዩኒስ ትምህርት ቤት አርብ ዕለት በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ነው ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ህይወቱ አልፏል።
እስራኤል በአካባቢው እያደረሰችው በነበረው ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ምክንያት የህክምና ባለሙያዎች መድረስ ባለመቻላቸውም ሳመር ከፍተኛ ደም ፈሶት ህይወቱ አልፏል።
ከተገደለው ሳመር በተጨማሪ የአልጀዚራ አረብኛ ቋንቋ ኃላፊ ዋኤል አልዳዱህ ቆስሎ ነበር።
የጋዜጠኛውን ግድያ ለአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መምራቱንም ነው አልጀዚራ ያስታወቀው።
አልጀዚራ የሳመርን ግድያ “ሆን ብሎ የተፈጸመ ግድያ” ሲል ለአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ ጠቅሶ በፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ እየሰሩ ባሉ ጋዜጠኞቹ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ያጠቃልላል ተብሏል።
አልጀዚራ ከተመሰረተበት ከአውሮፓውያኑ 1996 ጀምሮም በስራ ላይ እያለ የተገደለ 13ኛው ጋዜጠኛው መሆኑንም ነው የገለጸው።
ኑሴይራት በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ላይ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሰባት ዓመት ታዳጊ ሴት ልጁን ጨምሮ ባለቤቱ፣ ሌላኛው ወንድ ልጁ እንዲሁም የልጅ ልጁ የተገደሉበት ዋኤል ቢጎዳም ህይወቱ ተርፏል።
ዋኤል በባልደረባው የቀብር ስነ ስርዓት ላይም ባደረገው የኃዘን መግለጫ ንግግሩ በጋዛ የሚገኙ ጋዜጠኞች “በሙያችን ኃላፊነታችንን መወጣታችን እንቀጥላለን” ብሏል።
የጋዛ ጋዜጠኞች “ሰብዓዊ እና ክቡር መልዕዕክት” ለአለም እያስተላለፉ እንደሆነ የገለጸው ዋኤል የእስራኤል ጥቃት ቢቀጥልም ከስራቸው እንደማያስተጓጉላቸው ተናግሯል።
- ቤተሰቡ በእስራኤል አየር ጥቃት የተገደሉበት የአልጀዚራው ጋዜጠኛ27 ጥቅምት 2023
- “አንዳንድ ጊዜ ከካሜራ ጀርባ ቆሜ አለቅሳለሁ” የጋዛው ጋዜጠኛ4 ህዳር 2023
- የጋዛን ሰፈር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የቀየረው ጥቃት24 ጥቅምት 2023
ዋኤል በዚህ ጥቃት ስብርባሪዎች ላይኛው ክንዱን መትተው ያቆሰሉት ሲሆን ለህክምና ወደ ናስር ሆስፒታል መሄድ መቻሉንም አልጀዚራ ዘግቧል።
የካሜራ ባለሙያው ሳመር ለአምስት ሰዓታት ደም ፈሶት መሞቱን አልጀዚራ አስታውቆ እስራኤል ጋዜጠኞቿን እና ቤተሰቦቻቸውን ኢላማ አድርጋለች ስትልም ተጠያቂ አድርጋለች።
የካሜራ ባለሙያው ሳመር አልጀዚራን የተቀላቀለው በአውሮፓውያኑ 2004 ሲሆን በካሜራ ባለሙያነት እና በአርታኢነትም ሰርቷል።
የሶስት ወንዶች እና አንዲት ሴት ልጅ አባቱ ሳመር ነዋሪነቱም በኻን ዪኒስ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አባሳን አል ከቢራ ከተማ ነበር።
እስራኤል እየፈጸመቻቸው ባሉ ጥቃቶች በርካታ ጋዜጠኞች ተቀጥፈዋል።
በባለፉት ሳምንታት 64 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በርካታዎቹ ፍልስጤማውያን መሆናቸውን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ አስታውቋል። በተለይም የጋዛ ጋዜጠኞች ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው ብሏል።