
17 ታህሳስ 2023, 12:59 EAT
ኤችኤምኤስ ዳይመንድ የሚል ስም ያለው የዩኬ የጦር መርከብ ቅዳሜ ዕለት አንድ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን (ድሮን) ቀይ ባሕር አካባቢ መትቶ መጣሉን አስታወቀ።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የሮያል ባሕር ኃይል አንድ ዒላማ ከአየር ተኩሶ ሲጥል ምናልባትም ከ10 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
መከላከያ ሚኒስቴር ሰው አልባ አውሮፕላኑ ከማን እንደተተኮሰ ያለው ነገር የለም። ነገር ግን የየመን ሁቲ ኃይሎች በቀይ ባሕር አካባቢ ለሚሰነዘሩ የድሮን ጥቃቶች ኃላፊነት ወስደዋል።
ሁቲዎች ለሐማስ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹ ሲሆን በቀይ ባሕር አካባቢ የሚያልፉ በተለይ ደግሞ የእስራኤል ጥቅሞች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ዝተው ነበር።
መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው የቅዳሜው ተኩስ ዒላማ ያደረገው ምናልባት አንዲትን የንግድ መርከብ ሳትሆን አትቀርም።
ቀይ ባሕር የሚገኘው በሰሜን አፍሪካና በአረቢያ ሰርጥ ሲሆን ሜዲትራኒያንን ከሕንድ ውቅያኖስ ጋር በስዊዝ ቦይ በኩል ያገናኛል።
ኤችኤምኤስ ዳይመንድ የጦር መርከብ ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ወደ አካባቢው ያቀናው።
መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ ለዓለም አቀፍ ንግድና የባሕር ጉዞ ጋሬጣ በመሆኑ ደኅንነትን ለማስጠበቅ እርምጃው ተወስዶበታል።
“ዩኬ ዓለም አቀፍ የመርከብ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥልና ንግድ እንዲሳለጥ በርትታ ትሠራለች” ይላል መግለጫው።
በዚህ ወር መጀመርያ ዩኒቲ ኤክስፖለረር የተባለች መርከብ የሁቲዎች ዒላማ ሆና እንደነበር የአሜሪካ መከላከያ አስታውቋል። መርከቧ የባሓማስን ባንዲራን ታውለብልብ እንጂ ባለቤትነቷ የብሪቲሽ ኩባንያ ነው።
- ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ አጭር ፊልም ታዋቂ ሽልማትን ያገኘው ወጣት ኢትዮጵያዊ17 ታህሳስ 2023
- የንግሥቲቱን ከፍተኛ ሽልማት አልቀበልም ያለው እንግሊዛዊው ገጣሚ ቤንጃሚን17 ታህሳስ 2023
- የእስራኤል ጦር ታጋቾችን ተኩሶ በገደለበት ወቅት ነጭ ጨርቅ እያውለበለቡ እንደነበር አስታወቀ17 ታህሳስ 2023
ባለፈው ዓርብ ደግሞ ማእረስክ የተባለ የመርከብ ድርጅት በባብ- አል- መንደብ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦቹ በሙሉ ለጊዜው ጉዞ እንዲያቆሙ ማሳሰቢያ ሰጥⶆ ነበር።
ይህ ማሳሰቢያ የመጣው የላይቤሪያን ባንዲራ እያውለበለበች ትጓዝ የነበረች መርከብ አደጋ ከገጠማት በኋላ ነው።
ባብ-አል-መንደብ በእስያ በኩል ከየመን፣ በአፍሪካ በኩል ከጂቡቲ የሚዋሰን ወሽመጥ ነው።
በየቀኑ 50 ግዙፍ መርከቦች በባል- አል-መንደብ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ ሲሆን ከዚህ እጥፍ የሚሆኑ መርከቦች ደግሞ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያልፋሉ።
ሆርሙዝ ከኢራንና ኦማን ቅርብ የሆነ የመርከብ መተላለፊያ ወሽመጥ ነው።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ እንዳመላከተው ለመጨረሻ ጊዜ አንድን በራሪ ኃይል ዒላማ በማድረግ መትቶ የጣለው በመጀመርያው የባሕረ ሰላጤው ጦርነት ጊዜ እንደ አውሮፓዊያኑ በ1991 ዓ/ም ነበር።
ከዓለም የባሕር መርከብ ጉዞዎች አንድ ስድስተኛ የሚሆነው የሚያልፈው በቀይ ባሕር ባብ-አል-ማንደብ ወሽመጥ በኩል ነው።