
17 ታህሳስ 2023, 10:01 EAT
በሊቢያ የባህር ዳርቻ በደረሰ የጀልባ አደጋ ከ60 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸውን የተባበበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።
ጀልባዋ 86 የሚጠጉ ስደተኞችን አሳፍራ ከዙዋራ ከተማ ቅዳሜ ዕለት መውጣቷንም ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ዋቢ አድርጎ ድርጅቱ ጠቅሷል።
ከፍተኛ ማዕበል ጀልባዋን ማናወጡን ተከትሎ በደረሰው አደጋ ህጻናትን ጨምሮ 61 ስደተኞች በውሃ ውስጥ የጠፉ ሲሆን ህይወታቸው አልፏልም ተብሏል።
ሊቢያ በአደገኛ ሁኔታ ሜድትራንያን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ መግባት ለሚሹ ስደተኞችም መነሻ ሆና እያገለገለች ትገኛለች።
በዚህ የበርካታ ስደተኞችን ህይወት በሚቀጥፈው ጉዞም በዚህ ዓመት ብቻ ከ2 ሺህ 200 የሚበልጡ ስደተኞች ህይወታቸው አልፏል። በአለም ላይ ካሉት እጅግ አደገኛው የስደተኞች መሸጋገሪያ መንገዶችም አንዱ ነው።
በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ያጡት አብዛኛዎቹ ከናይጄሪያ፣ ጋምቢያ እና ሌሎች አፍሪካ አገራት የመጡ መሆናቸውምንም ኤጀንሲውን ዋቢ አድርጎ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከአደጋው የተረፉ 25 ግለሰቦች ወደ ሊቢያ ማቆያ ጣቢያ እንዲገቡ ተደርገው የህክምና ድጋፍም እየተሰጣቸው መሆኑም ተገልጿል።
በዚህ አመት የሞቱ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡንም በመጥቀስ “በባህር ላይ የሚቀጠፉ ሰዎችን ህይወት ለማዳን በቂ ስራ እንዳልተሰራ ያሳያል” ሲሉም የአይኦኤም ቃለ አቀባይ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
በሰኔ ወር የአሳ ማጥመጃ ጀልባ በደቡባዊ ግሪክ በመስጠሟ ቢያንስ 78 ሰዎች ሲሞቱ 100 ያህሉን ደግሞ ማትረፍ ተችሏል።
- የአልጀዚራ የካሜራ ባለሙያ በእስራኤል የድሮን ጥቃት ተገደለ17 ታህሳስ 2023
- ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ አጭር ፊልም ታዋቂ ሽልማትን ያገኘው ወጣት ኢትዮጵያዊ17 ታህሳስ 2023
- የንግሥቲቱን ከፍተኛ ሽልማት አልቀበልም ያለው እንግሊዛዊው ገጣሚ ቤንጃሚን17 ታህሳስ 2023
ሜዲትራንያን ተሻግረው ወደ አውሮፓ ለማቅናት የሚሞክሩ ስደተኞች የሚጫኑባቸው ጀልባዎች በጣም አነስተኛ እንዲሁም መጫን ከሚችሉት በላይ በማጨቅም ይታወቃሉ።
በርካታ ስደተኞች ግጭትን፣ መሳደድንም ወይም ለተሻለ ህይወት ፍለጋ በሚልም ባህሩን ተሻግረው ወደ ጣሊያን ከዚያም ወደ ሌሎች አውሮፓ አገራት ለማቅናት ይሞክራሉ።
በዚህ በአውሮፓውያኑ ዓመት ከ153 ሺህ በላይ ስደተኞች ከቱኒዝያ እና ሊቢያ ወደ ጣሊያን መግባታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።
ቅዳሜ እለት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከጣሊያን አቻቸው ጆርጂያ ሜሎኒ እና ከአልባኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢዲ ራማ ጋር ወደ አውሮፓ የሚደረገውን ህገወጥ ስደት እንዴት መቀነስ እንደሚቻል በሮም ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ትናንሸ ጀልባዎችን በመጠቀም ወደ እንግሊዝ የሚገቡ ስደተኞችን ማስቆም ከመንግሥታቸው አምስት ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።