
17 ታህሳስ 2023
ቃላቶች ይታዘዙለታል የሚባለው እንግሊዛዊው ገጣሚ እና ፀሐፊ ቤንጃሚን ዘፋኒያህ በቅርቡ ሕይወቱ አልፏል።
በ65 ዓመቱ ያረፈው ቤንጃሚን ከፀሐፊነቱ በተጨማሪ ሙዚቀኛ፣ ተዋናይ እንዲሁም በግጥም እና በጽሁፍም የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ነበር።
ቤንጃሚን ዘረኝነትን አጥብቆ የሚጠየፍ ታጋይ ነበር።
ለሚታገልለት ዓላማ ያለው ቁርጠኝነትም ሽልማትን አልቀበልም እስከሚል ጽናት ድረስ ዘልቋል።
ወቅቱ በአውሮፓውያኑ 2003 ነበር።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሁለተኛነት ለተቀመጠው ‘ኦርደር ኦፍ ዘ ብሪቲሽ ኢምፓየር’ ሽልማት እንደተመረጠ ተነገረው።
ለሽልማት መታጨቱ የተነገረው በወቅቱ በሥልጣን ላይ በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቶኒ ብሌየር ጽህፈት ቤት በኩል ነበር።
ሽልማቱን ውድቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሽልማቱን እንዴት እንደሚጸየፈውም ጋርዲያን ላይ ባወጣው ጽሑፉ አስፍሮ ነበር።
“እኔን!? ለኦርደር ኦፍ ዘ ብሪቲሽ ኢምፓየር? ጥርግ በሉ” ጋርዲያን ላይ የወጣው ጽሁፉ ርዕስ ነበር።
“ኢምፓየር (ግዛት) የሚለውን ቃል ሳይ ተናደድኩ። ባርነትን ነው የሚያስታውሰኝ። ለሺዎች ዓመታት የቀጠለ የጭካኔ እና የግዞት ሥርዓትን እና ቀጣይነቱን እንዲሁም የጣለውን ጠባሳ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። ሴቶች ቅድመ አያቶቼ እንዴት እንደተደፈሩ፣ አባቶቼ በጭካኔ እንዴት እንደተገላቱ ማስታወሻ ነው።”
“ኢምፓየር (ግዛት) በሚለው ምክንያት ነው እንደኔ ያሉ ጥቁር ሰዎች ትክክለኛ ስማችንን የማናውቀው ወይም ታሪካችን እንዲሰረዝ እና እንዲፋቅ የተደረገው” ሲልም ጽፏል።
ቤንጃሚን በቃላቶቹ ፍሰት፣ በሐሳቡ ጥልቀት በርካቶችን መድረስ የቻለ ገጣሚ ነው።
የሚያምንበትን ነገር ከመጻፍ፣ ከመናገር እና ከመታገል ፈቅ የሚያደርገው አልነበረም።
“በመጀመሪያ ቃል ነበር፣ ቃልም ግጥም ሆነ እናም እሱን አገኘሁት፤ ትልቅም ነገር ነው” ሲል የወንጌላዊውን ዮሐንስን “በመጀመሪያ ቃል ነበር” የሚለውን የሚያስተጋባ ጽሁፍም በሕይወት ታሪኩ አስፍሯል።
በ65 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ቤንጃሚን በሕይወቱ በርካታ ተልዕኮዎች ነበሩት፤ አንዳንዶቹ ግላዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ።
እንዲህ ታላቅ ፀሐፊ ሊሆን የበቃው ቤንጃሚን የልጅነት ሕይወቱ በውጣ ውረድ የተሞላ ነበር።
ትምህርቱን ያቋረጠው በ13 ዓመቱ ነበር። ማንበብ እና መጻፍ ሳይችል ነበር ከትምህርት ቤት የወጣው።
በሁለት ዓመታት ውስጥ ‘ደብ ፖየትሪ’ በሚባለው ግጥም አይነትም ታዋቂነትን አተረፈ።
ደብ ፖየትሪ መነሻው ጃማይካ ነው።

ነገር ግን ብዙ አልቆየም የታዳጊነት ሕይወቱ ‘መስመሩን ስቶ’ በዘረፋ ወንጀል ታስሮ ነበር።
ሕይወቱን በተሻለ መንገድ ለመምራት እና እንደ አዲስ ለመጀመር በ22 ዓመቱ ከበርሚንግሐም ወደ ለንደን ከተማ አቀና።
ወቅቱም 1979 ነበር። በለንደንም ሌሎች ፀሐፊዎችን አገኘ።
በዓመቱም ‘ፔን ሪትም’ የተሰኘ የግጥም መጽሐፉን አሳተመ። በስኬት የተሞላውን ሕይወቱንም ‘ሀ’ ብሎ ጀመረ።
“ግጥም የሚታይበትን ዕይታ መቀየር እፈልግ ነበር። በእኛ ላይ እየሆነ ያለውን ነገርም በግጥም ሕይወት ዘርቼ ማምጣት ጀመርኩ” በማለት በአንድ ወቅት ለጋርዲያን ተናግሯል።
“ቃለ መጠይቅ በማደርግበት ወቅት ቃላትን ለማውጣት እቸገራለሁ። ግጥም በምጽፍበት ወቅት ግን ፈቃድ የተሰጠኝ ይመስል ቃላቶቹ ይፈሳሉ።”
አክሎም “ቃላቶቹን እንደፈለጉ እቀያይራቸዋለሁ፣ የተወሰነውን ለምናብ እተወዋለሁ። የፈለግኩትን መልዕክት ማስተላለፍ የምችልበት ነው።”
“እናቴ ሁልጊዜም መድረክ ላይ ስታየኝ፣ ልጄን የማየው እዚህ ላይ ነው ትላለች” ሲልም አጋርቶ ነበር።
- “የአንዳንድ ቋንቋዎች የበላይነት ባህልን እያጠፋ ነው” ኬንያዊው ደራሲ ጉጊ18 ጥቅምት 2020
- ታላቋ ፀሐፊ ቶኒ ሞሪሰን ስትታወስ7 ነሐሴ 2019
- በአገራቸው ባዳ የሆኑት የኖቤል ተሸላሚው ታንዛኒያዊ ደራሲ14 ህዳር 2021
ልጅነት እና ቤተሰብ
ቤንጃሚን ያደገው እንግሊዝ በርሚንግሃም ውስጥ ነው።
ከካሪቢያን ደሴቶች፣ ባርቤዶስ እና ጃማይካ ከመጡት ቤተሰቦች ነው የተወለደው።
ከትልቅ ቤተሰብ የተወለደው ፀሐፊው ሰባት ወንድሞች እና እህቶች ነበሩት።
ስለ አባቱም ሲናገር “ይመታኝ ነበር። አሁንም የተመታሁት ትዝ ይለኛል” ሲል ከቢቢሲ ሬድዮ ጋር በአውሮፓውያኑ 1997 ባደረገው ቆይታ ተናግሮ ነበር።
“ከሁሉም በላይ ግን እናቴን ሲመታት ትዝ ይለኛል። እናም ብዙም ሳይቆይ አረፈ።
“ለቤተሰባችንም ትንሽ የሚያቋስል ጉዳይንም ትቶ ነው ያለፈው። እናቴ እኔን ብቻ ይዛ ነበር አባቴን ጥላ የወጣችው። ሌሎቹን ልጆች እሱ ጋር ትታቸው ነበር የሄደችው።”
“እናም ሲሞት። ሌሎቹ ብቻውን በጽናት ያሳደጋቸው ልጆች ወላጅ አድርገው እንደ ጀግና ነበር የሚያዩት” ብሏል።
ለእሱ ግን ይህ ሊዋጥለት አልቻለም።
ቤተሰቡ እንዲቀራረብ እና አንድ ላይ እንዲመጣ በአውሮፓውያኑ 2002 በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ ያለፈው የአጎቱ ልጅ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ቤንጃሚን ተናግሮ ነበር።
“እያንዳንዷ የምትሆነውን ነገር አወራለት ነበር” ሲልም በአውሮፓውያኑ 2009 ከጋርዲያን ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
ለቤንጃሚን የእናቱ ነገር ልዩ ነው። ግንኙነታቸውም በጣም የጠበቀ ነበር።
“ከእናቴ ጋር በጣም የጠበቀ ግንኙነት አለን። በየቀኑ አዋራታለሁ።”
“ብዙ አይታለች። እንደ ነርስነቷ ዘረኛ ለሆኑ ሰዎች እንኳን ሳይቀር ሕክምና መስጠት ነበረባት። ሁልጊዜም ቢሆን የሰዎችን መልካም ጎን የምታይ ናት። እኔም እንደዚያ ነኝ። ሰዎች የሚያምኑባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ያስደንቁኛል” ሲልም ተናግሯል።
በሕይወቱ ውስጥ ካሳዘኑት ነገሮች አንዱ ግን ልጆች ለማፍራት አለመቻሉ ነው።
“ክፉኛ ይፈትነኝ ነበር። ለዓመታትም በርካታ ምርመራዎችን አድርጌያለሁ። አሁን ነገሩን ቀለል አድርጌ ነው የማየው። ሕይወት እንደዚህ ነው።”
“በሳምንት ቢያንስ አርባ ደብዳቤዎች ከልጆች ይደርሱኛል። ‘ግጥምህን እወደዋለሁ ቤንጃሚን’ ወይም ‘መጽሐፍን እያነበብኩ ነው’ የሚሉ።”

ዘረኝነት
“ጥቁሮች ባርያዎች አይደሉም። ጥቁሮች ወደ ባሪያነት የተቀየሩ ሰዎች ናቸው” ሲልም በአንድ ወቅት ለላኩና መጽሔት ተናግሯል።
ዘረኝነትን በቅርበት ያውቀዋል ቤንጃሚን። የመጀመሪያ የዘረኝነት ጥቃት የደረሰበትም ገና ልጅ እያለ ነው። በዚህም አንድ ልጅ ጭንቅላቱን በድንጋይ መትቶ አስፓልት ላይ ደሙን እያዘራ ወደቀ። የመታውም ልጅ ብስክሌቱን እየነዳ ‘ወደ አገርህ ሂድ’ አለው።
ቤንጃሚን ሙሉ ሕይወቱን ስለ ዘረኝነት ተናግሯል፣ ጽፏል፣ ዘፍኗል እንዲሁም አስተምሯል።
በአውሮፓውያኑ 1999 የጻፈው ‘ዋት ስቴፈን ላውረንስ ሃዝ ቶውት አስ’ (ስቴፈን ላውረንስ ያስተማረን ጉዳይ) ማስታወሻነቱ በዘረኝነት ጥቃት ለተገደለው የ18 ዓመት ታዳጊ ነበር።
ታዳጊው በምሥራቅ ለንደን በነጭ ወጣት ወንዶች ቡድን ነው የተገደለው። ሁለት ነጭ ወንዶች በአውሮፓውያኑ 2012 ክስ ቢመሠረትባቸውም ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች በነጻነታቸው ቀጠሉ።
ስፖርተኛው ቤንጃሚን
ቤንጃሚን የአስቶን ቪላ የእግር ኳስ ክለብ አድናቂ ነበር። ከመሞቱ ከሦስት ዓመታት በፊትም እግር ኳስ ይጫወት ነበር።
ከሁሉም ዕድሜ የተውጣጡ እግር ኳስ በሚጫወቱበት (11-a-side) በተባለውም አገሪቷን ወክለው በተለያዩ ውድድሮችም ተሳትፏል። በቡድኑ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሕጻናት ሲሆኑ፣ እሱም አምበልም ሆኖ ነበር።
“እንደዚህ መሮጥ መቻሌን ሊያምኑት አልቻሉም። ተስፍንጥሬ ስሮጥ ጎበዝ ነኝ። እንዲሁም ኳስ ማንጠባጠብም ላይ እንዲሁ” ሲልም ከጋርዲያን ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሮ ነበር።
እግር ኳስ መጫወት ለምን እንዳቆመ ከጋዜጣው ጋር በነበረው ቆይታ ሲናገር።
“ደቡባዊ አውሮፓ አገራት ለውድድሮች ሄደን መቼም ቢሆን እንግሊዛዊ መሆን አትችልም አሉኝ። አምበል ነበርኩኝ እና አሸነፍኩ። ራሴን እንድጠቀልልበት ሰንደቅ ዓላማ ሰጡኝ ላደርገው አልቻልኩ” ሲልም ለጋዜጣው ተናግሯል።
የመማር ችግር (ዲስሌክሲያ)
ቤንጃሚን የመማር ችግር እንዳለበት የተረዳው በ21 ዓመቱ ነበር። ለንደን በሚገኝ የጎልማሶች ትምህርት ቤት ገብቶ ማንበብ እንዲሁም መጻፍ ተማረ።
“ሁልጊዜም ለበርካታ ሰዎች በተለይም ለሕጻናት የምነግራቸው የመማር ችግር (ዲስሌክሲያ) ጉብዝናችሁን አይለካም። ታሪኮቻችሁን መንገሪያ መንገድ መፈለግ ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂውም ልቋል። መምህራንም ይሁን በዩኒቨርስቲዎች ያሉ ፕሮፌሰሮች ስለ ዲስሌክሲያ ያውቃሉ።
“ይህ ሁኔታ ወደ ኋላ ሊጎትታችሁ አይገባም። አይንስታይንን ጨምሮ በጣም ምጡቅ አዕምሮ የነበራቸው ግለሰቦች የዲስሌክሲያ ችግር እንደነበራቸው አሁን አውቀናል” ሲልም ለቡክ ትረስት በአውሮፓውያኑ 2020 ተናግሮ ነበር።

የሰው ልጅ ሰውን ይፈልጋል
ለቤንጃሚን ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ የአንድ ማኅበረሰብ አካል መሆንን ከሁሉም ነገር በላይ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
ሆኖም በሕይወት ውስጥ ለአንተ የሚስማሙህን ሰዎች ማግኘት ቀላል አይደለም።
“ሁላችንም ሰዎች ያስፈልጉናል። እኛ ማኅበራዊ እንስሶች ነን። ዋናው ነገር ጥሩ ተግባር እያከናወኑ ያሉ ሰዎችን ማግኘቱ ላይ ነው” ብሏል።
በዝግጅቶቹም ላይ ይታደሙ ከነበሩ ሰዎች ጋር የነበረውንም ጥልቅ ግንኙነት ይወደው ነበር።
“ከሁሉም በላይ ይነካኝ የነበረው ነገር ሰዎች ያካፈሉኝ ታሪኮች ናቸው” ሲልም በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።
መልካምነት
ሰዎች የያዙዋቸውን የተሳሳቱ አመለካከቶች ለመቀየር እንደሚፈልጉ ለላኩና መጽሔት በአንድ ወቅት ተናግሮ የነበረው ቤንጃሚን “በእንግሊዝ እንደ ጥቁር ሰው ምን ማድረግ እችላለሁ? ብዬ ራሴን እጠይቅና የተሳሳቱ አመለካከቶችን እና እምነቶችን ለመቀየር የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ እጥራለሁ” ሲል ያስረዳል።
“ጥቁር ወንዶችን ለሚፈሩ ሰዎች እስካሁን ካጋጠሟቸው ሁሉ በጣም ጥሩ ሰው እና መልካም መሆኔን አሳያቸዋለሁ” ብሎም ለመጽሔቱ ተናግሮ ነበር።
ተስፋ
ቤንጃሚን ሙሉ ሕይወቱን ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ሰው ነበር።
“ማስረጃ ማቅረብ ባልችልም መልካም ነገር ክፉውን ያሸንፋል። ተስፋ ማድረግ አለብን” ይላል።
“ጨቋኞቻችን ከሚጠሏቸው ነገሮች አንዱ እኛን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ እና ገጣሚዋ እና ፀሐፊዋ ማያ አንጀሎ እንደምትለው ልትጥለኝ ትሞክራለህ እኔ ግን እነሳለሁ” ብሎም ያለውን ተስፋ አጋርቶ ነበር።

እምነት
ቤንጃሚን ጥልቅ እምነት ነበረው። ሆኖም በእምነት እና በሐይማኖት መካከል ያለውንም ልዩነት የተረዳ ሰው ነው።
“ሳስበው ሃይማኖች ለአምላክ መጥፎ ስም እንዲኖረው አድርጓል” ይላል።
“እኔ እምነት ስል ስለ ማመን ነው የምናገረው። አምላክን የማወቅ፣ በተመስጦ (ሜዲቴሽን) ውስጥ ስሆን የማገኘው ነው። ማንንም ሰው አይፈልግም። ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ቄስ አያስፈልገውም። ሼክም ሆነ ኢማም አያስፈልገውም። ምንም አያስፈልገውም። በተመስጦ ውስጥ መሆን ብቻ” በማለት ሐይ ፐሮፋይል ለተሰኘው መጽሔት አስረድቷል።
ሥጋ አለመመገብ
ቤንጃሚን ለእንስሳ መብቶች አጥብቆ ይሟገት ነበር። ሥጋም ሆነ የእንስሳት ተዋጽኦ ለማይመገቡት ‘የቪጋን’ ማኅበረሰብ አምባሳደር ነበር።
ሥጋ መብላት ያቆመው ገና በልጅነቱ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው።
በግጥሞቹም ላይ እነዚህን ሐሳቦች ያንጸባርቅ ነበር። የራሱን ምግቦችም በአትክልት ስፍራው ያበቅላል። ራሱ ያመረተውን ነበር የሚመገበው።
“ትልልቅ መደብሮች (ሱፐር ማርኬቶች) የምሄድበት ጊዜ ውስን ነው” ብሎ ነበር።
ለውጥ ማምጣት
“ግራ አትጋቡ፣ አትዘኑ። የመሸነፍ ስሜት አይሰማችሁ። የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ” ሲልም ከሦስት ዓመታት በፊት ተናግሮ ነበር።
“ትንሿን፣ (ወይም ትልቁን)፣ ማድረግ የምትችሉትን ለውጥ የሚያመጣውን ሁሉ ነገር አድርጉ። የሚታይ እና የሚጨበጥ ነገር። ወይም ለወደፊቱ የሚሆኑ ነገሮችን ለማድረግ ወደ አደባባዮች ውጡ። ማንኛውንም ነገር አድርጉ። ተስፋ አትቁረጡ” ብሏል።
“ድቅቅ እንዲያደርጉላችሁ አትፍቀዱላቸው። የበለጠ የምታውቁ ወንድሞች እና እህቶች ተነሱ። በመንገዳገድም ውስጥ ጽኑ” በማለትም መልዕክቱን አስተላልፏል።