

ማኅበራዊ ከከተማ አስተዳደር እስከ ወረዳ ያሉ ሠራተኞች ፈተና ወስደው እንደ አዲስ ሊመደቡ ነው
ቀን: December 17, 2023
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ሥር የሚገኙ ሠራተኞች በብቃት መመዘኛ ፈተና ሊለዩ እንደሆነ ተነገረ፡፡ በመጀመርያ ዙር ፈተናውን የሚወስዱ ተቋማት የተለዩ ሲሆን፣ እስከ ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የተለዩት ቢሮዎች ሁሉም ሠራተኞች ለፈተናው ዝግጁ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ከከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እስከ ወረዳ ባለው ተዋረድ የከተማ አስተዳደሩን አዲሱን የመዋቅር ማሻሻያ የአደረጃጀት ጥናት ያደረጉ ቢሮዎች፣ ሁሉም ሠራተኞች ፈተናውን እንደሚወስዱ ተረጋግጧል፡፡
ከነዚህ መካከልም የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት፣ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር፣ የመሬት ልማት አስተዳደር፣ የሥራ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት፣ የኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
በቀጣይ ዙር ደግሞ የመዋቅር አደረጃጀታቸውን አጠናቀው የሚጨርሱ ተቋማት ሠራተኞች ወደፈተና ይገባሉ ተብሏል፡፡ ፈተናውን ማስፈጸሚያ መመርያ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡
ይህን የብቃት ፈተና ማለፍ ያልቻሉ ሠራተኞች በሚመጥናቸው ቦታ ይመደባሉ ተብሏል፡፡ የሚመደቡበትን ቦታ የማይፈልጉ ደግሞ የመቋቋሚያ ገንዘብ ተከፍሏቸው ሥራውን መልቀቅ የሚችሉበት አሠራር ተበጅቷል ነው የተባለው፡፡
ከሰሞኑ የከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ይፋ እንዳደረገው፣ በተመረጡ 16 ተቋማት ሥር ባሉ 105 የሥራ መደቦች ላይ የሠራተኞች ድልድል እንደሚኖር ገልጿል፡፡
በእነዚህ 105 የሥራ መደቦች ላይ የሚደረገው የሥራ ድልድልም በውድድርና በፈተና እንደሚካሄድ ነው ቢሮው የተናገረው፡፡
የዚህ ድልድል ዋና ዓላማ በከተማ አስተዳደሩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት ማረጋገጥ እንደሆነ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮው አክሎ ገልጿል፡፡
ቢሮው ይህን ቢልም በፈተናው የማለፊያ ውጤት ላላመጡ ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ክህሎት የማሳደግ ሥራ ይሠራል ነው ያለው፡፡