EthiopianReporter.com 

ዳዊት ታዬ

December 17, 2023

ከመተዳደሪያ ደንባቸውና ከተቋቋሙበት አዋጅ ውጪ የጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ሳያካሂዱ የቆዩት ሁሉም የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንዲያካሂዱ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትዕዛዝ መስተላለፉ ተገለጸ፡፡

ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማሳሰቢያ የተሰጠው ኅዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲሆን፣ ጠቅላላ ጉባዔያቸውንም እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስቧቸዋል፡፡

‹‹ያልተጠበቀ ነው›› የተባለው ትዕዛዝ፣ ንግድ ምክር ቤቶቹ በተቋቋሙበት አዋጅ መሠረት ወቅቱን ጠብቀው ባለማካሄዳቸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጣልቃ ሊገባ መቻሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዘዘ በተባለው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን የሚያካሂዱት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ ምርጫ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት በተለይ ምንም ጠቅላላ ጉባዔ ሳይጠራና ምርጫ ሳይካሄድ ወደ ስምንት ዓመታት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. መካሄድ ባለበት ጠቅላላ ጉባዔ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ የቦርድ አባላት ምርጫ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ‹‹ያልተጠበቀ›› የተባለው ትዕዛዝ በብዙዎቹ ምክር ቤቶች ድንጋጤ የፈጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከጥቂት ወራት በፊት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ለአባል ምክር ቤቶች አስተላልፎ በነበረው ጥሪ፣ ከሁለት ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች በስተቀር ጠቅላላ ጉባዔ አካሄደው፣ በአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለመወከል አንችልም በማለታቸው፣ ጠቅላላ ጉባዔው መሠረዙ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ምክር ቤቶቹ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አንችልም ያሉት የራሳቸውን ጠቅላላ ጉባዔ አካሄደው፣ ተወካይ ለመላክ ጊዜ የማይበቃቸውና የገንዘብ እጥረት አለብን በሚል መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትዕዛዝ ከተላለፈ በኋላ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ታኅሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን እንደሚያካሂድ፣ ለአባላቱ የመገናኛ ብዙኃን ጥሪ እያስተላለፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም ከታኅሳስ አጋማሽ በኋላ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው ተብሏል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አባላቶች በርካታ ጉዳዮችን ያነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተሉ ካሉ አባላት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡ አንዱ ጉዳይም ‹‹ንግድ ምክር ቤቶች ከደንብና ከሥርዓት ውጪ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂዱ ለምን ቆዩ?›› የሚለው አንዱ ነው፡፡

በሌሎች አሉ በሚባሉ ችግሮች ዙሪያም አባላት ይሞግታሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ምርጫ ከተደረገም ብዙ ለውጥ የሚኖር ስለመሆኑ ምንጮቹ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሥሩ 18 አባል ምክር ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም ምክር ቤቶች በርካታ አባላት እንዳላቸው የሚነገረው የአማራና የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው፡፡