December 17, 2023 

መሳይ መኮንን ፦ በአየር ሃይል ቀን የኤሜሬትስ የአየር ትርዒት ቀርቧል። አብዛኛው ትዕይንት በውጭ ሀገር አየር ሃይል ትርዒት የታየበት ነው። የተወሰኑ ሄሊኮፕተሮች በሰማዩ ላይ ከመብረራቸው በቀር የታየው የኤሜሬትስ ሾው ነው። ለምን እንደዚያ ማድረግ እንዳስፈለገ ግራ የሚያጋባ ነው። ከበዓሉ አከባበር ጀምሮ መላ ቅጡ የጠፋበት ቀን ሆኖ ነው የዋለው። በመሰረቱ 88ዓመት ማክበር ለምን አስፈለገ? 10ኛ፥ 25ኛ፥ 50ኛ፥ 75ኛ እና 100ኛ እየተባለ በተለምዶ የብር፥ የወርቅ፥ የአልማዝ ኢዩቤልዩ በሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ቀናት መከበራቸው አዲስ ነገር አይደለም።

88ኛ ዓመት ምንድን ነው? ለምን በተለየ ሁኔታ ተመረጠ? 87ኛ ለምን አልተከበረም? በሚቀጥለው ዓመት 89ኛው ቢከበርስ ምን ልዩነት አለው? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ የላቸውም። አብይ አህመድ የተዘፈቀበትን ቀውስ በትርዒት ጋጋታ የሚያመልጥ መስሎት ያዘጋጀው ትርጉም የለሽ ግርግር መሆኑ ምናልባት የቀረበ ምክንያት ይሆናል።

የአየር ሃይል ነባር ሰዎችን አነጋግሬ በዛሬው ግርግር ላይ ትልቅ ጥያቄ እንዳላቸው ገልጸውልኛል። አንደኛ ታሪኩ ልክ አይደለም። አየር ሃይል እንዴት ጀመረ? መቼ ጀመረ? የሚሉትን ጉዳዮች በተዛባ መልኩ የቀረበበት መሆኑ እጅግ አሳዝኖአቸዋል። ሁለተኛ የኤሜሬትስ የአየር ትርዒት እንዴት በኢትዮጵያ አየር ሃይል ቀን እንዲታይ ይደረጋል? የክብር ጉዳይ እንዴት ይታያል? በሰው ወርቅ መድመቅ ይቻላል ወይ? ያሳፍራል። አብይ አህመድ ከኤሜሬትስ ጓዳ መንጎማለል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱን ገመና አደባባይ እርቃኑን አስጥቶታል። ያለነሱ አይተነፍስም። በኢትዮጵያ ስም በኪሱ የሚሸጉጡለት ዶላር ስለሀገር ክብር ደንታ እንዳይኖረው አድርጎታል።

በተረፈ በትርዒት የሚቀለበስ የህዝብ ትግል የለም። የተነቃነቀ ጥርስ መውለቁ አይቀርም። የአሜሪካን ኔቪ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ቢመላለስ እንኳን የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ተጋድሎ የሚያስቆመው አይሆንም። ይኸው ነው!

መሳይ መኮንን