አየር ማረፊያ ተውጦ፤ አዞዎች ከተማ መሐል የታዩበት የአውስትራሊያዋ ክዊንስላንድ ጎርፍ

ከ 5 ሰአት በፊት

በታሪክ ከፍተኛው በተባለው ዝናብ ምክንያት የአውስትራሊያዋ ክዊንስላንድ ግዛት በጎርፍ ተጥለቅልቃለች።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥፍራው እንዲለቁ ሲደረግ በርካቶች አሁንም መንቀሳቀሻ አጥተው ተቀምጠዋል።

ትሪፒካል ክሎን በተባለ የአየር ንብረት ክስተት የተከሰተው ዝናብ በአንዳንድ ሥፍራዎች ከፍተኛ ጎርፍ አስከትሏል።

ከአካባቢው የሚወጡ ምስሎች በካይርንስ አየር ማረፊያ ያሉ አውሮፕላኖች በከፊል ተውጠው፤ መሐል ከተማ አዞዎች ሲዋኙ እና ነዋሪዎች በታንኳ ሲሸሹ አሳይተዋል።

እስካሁን ድረስ በጎርፉ ምክንያት የሞቱ አሊያም የጠፉ ሰዎች አልተመዘገቡም።

ለሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ከፍተኛ ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ይጠበቃል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥፍራው እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን ቤቶች በጎርፍ ተውጠዋል፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጧል፣ የሚጠጣ ውሃ ማግኘትም ዘበት ነው።

የክዊንስላንድ ፕሬዝደንት ስቲቨን ማይልስ ለአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሰጡት አስተያየት ተፈጥሯዊውን አደጋ “በሕይወት ዘመኔ አስፈሪው” ብለውታል።

ፕሬዝደንቱ አክለው እንደ ዉጃል ውጃል ያሉ ራቅ ብለው በሚገኙ ሥፍራዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ቀድሞ ማስወጣት የመጀመሪያ ሥራቸው ነበር።

አንድ ሕመምተኛ ሕፃንን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሊደርሱላቸው ስላልቻሉ ለሊቱን ከአንድ ሆስፒታል ጣራ ላይ አሳልፈዋል።

በሚቀጥለው ቀን ሰዎቹ ወደ ሌላ ሥፍራ የተዘዋወሩ ቢሆንም ፕሬዝደንቱ አሁንም በርካታ ሰዎች ከሥፍራው መልቀቅ አለባቸው ይላሉ።

“የሚጠጣ ውሃ ነገር አሳስቦናል። የቆሻሻ ማስተላለፊያዎች፣ የኃይል እና ቴሌኮሚዩኒኬሽን እንዲሁም መንገድ ጉዳይ አሳሳቢ ሆነዋል። አብዛኛዎቹ መንገዶች ተዘግተዋል፤ በአየር እርዳታ መስጠት ደግሞ አዳጋች ነው።”

የአየር ንብረት ትንበያ የሚሰጡ ዝናቡ ሰኞ ዕለትም የሚቀጥል እንደሆነ ጠቁመው ከከፍተኛ ወጀብ ጋር መምጣቱ ዝቅተኛ ሥፍራ ላሉ ሰዎች አደጋ ነው ብለዋል።

ዝናቡ ማክሰኞ ዕለት ቀዝቀዝ ይላል ቢባልም ወንዞች ደግሞ ለቀናት ያክል ሞልተው እንደሚፈሱ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 1997 ተመሳሳይ ዝናብ ተከስቶ በርካታ ወንዞች ሞልተው እንደነበር ይታወሳል።

ዴይንትሪ የተባለው ወንዝ ባለፉት 24 ሰዓታት በጣለው 820 ሚሊ ሜትር ዝናብ ምክንያት መጠኑ ከሁለት ሜትር በላይ ደርሷል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ዝናቡ ያስከተለው አደጋ ከአንድ ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር [670 ሺህ የአሜሪካ ዶላር] ኪሳራ እንደሚያደርስ ይጠብቃሉ።

ምስራቃዊ አውስትራሊያ በቅርብ ዓመታት በተደጋጋሚ በጎርፍ አደጋ የተጠቃች ሲሆን ኤል-ኒኖ የተባለው በአየር ንብረት መቀያየር ሳቢያ የሚከሰተው አደጋም ዱላዋን እያሳረፈ ይገኛል።

አውስትራሊያ ባለፈው ጥቂት ዓመታት ተፈጥሯዊ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ክፍለ ዓለማት አንዷ ናት።

ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጎርፍ፣ ከፍተኛ ድርቅ፣ የእሣት አደጋ እና ሌሎችም ተፈጥሯዊ አደጋዎችን አስተናግዳለች።

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በጊዜ የማይገታ ከሆነ ሌሎችም ተመሳሳይ አደጋዎች አውስትራሊያን እንደሚጎበኟት የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥት ፓነል ያስጠነቅቃል።