ታጋች ጌርኮ ቫን ዴቨንተር

ከ 5 ሰአት በፊት

ከአል- ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው እስላማዊ ታጣቂዎች ከስድስት ዓመታት በፊት በሊቢያ ታግቶ የነበረውን ደቡብ አፍሪካዊ የድንገተኛ አደጋ የህክምና ባለሙያ ማስፈታታቸውን አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ።

ጊፍት ኦፍ ዘ ጊቨርስ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ለረዥም ጊዜ ታግቶ ቆይቷል ያለውን፤ ታጋቹን ጌርኮ ቫን ዴቨንተር “ያለ ቅድመ ሁኔታ” እንዲለቀቅ ማመቻቸቱን አስታውቋል።

እ.ኤ.አ. በ 2017 በሊቢያ ውስጥ ስሙ ባልተገለጸ ቡድን ተይዞ ከአንድ ዓመት በኋላ በማሊ ውስጥ ላሉ እስላማዊ ታጣቂዎች ተሽጦ “ወደ አልጄሪያ” መለቀቁን ድርጅቱ ገልጿል።

የማሊ የጸጥታ ምንጭ የ48 ዓመቱ ቫን ዴቨንተር ከእስር መፈታቱን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል አረጋግጧል።

የዜና ወኪሉ የሰብአዊ ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው የህክምና ባለሙያው በማሊ እና በአልጄሪያ ድንበር ላይ ተፈትቷል።

እ.ኤ.አ. በ2011 በኔቶ የሚደገፉ ሃይሎች ሊቢያን ለረዥም ጊዜ የገዟትን ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣን ካስወገዱ እና ከገደሉ በኋላ በአብዛኛው የሊቢያ ክፍሎች ውስጥ ስርዓት አልበኝነት ነግሷል።

ማሊ በበኩሏ እስላማዊ አማጽያንን እና ተገንጣይ አማጽያን ኃይሎችን በሰሜናዊ ግዛቷ በኩል እየተዋጋች ነው።

ተቀማጭነቱን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ጊፍት ኦፍ ዘ ጊቨርስ የተሰነው የበጎ አድራጎት ድርጅት የአልጄሪያ የደህንነት ኤጀንሲዎች ቫን ዴቬንተር ከእስር ከተፈታ በኋላ ለጤና ምርመራ ወደ ሆስፒታል ወስደውታል ብሏል።

“ከባለቤቱ ሸሪን እና ከልጁ አሸር ጋር ይገናኝ ዘንድ ወደ ቤት ለማምጣት በጤናው እና በዝግጅቱ ላይ ቀጣዩን ሂደት እንጠብቃለን። ስድስት አስጨናቂ ጸሎት ፣ ትዕግስት እና ተስፋ ዓመታት ነበሩ” ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል ።

በደህንነት ኩባንያ ውስጥ በድንገተኛ አደጋ ህክምና ስራ ተሰማርቶ የነበረው ቫን ዴቬንተር የታገተው በአውሮፓውያኑ ህዳር 3 ቀን 2017 በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በስተደቡብ 1,000 ኪ.ሜ (600 ማይል) ርቀት ላይ ወደሚገኝ የኃይል ማመንጫ ግንባታ ቦታ በመሄድ ላይ ሳለ ነበር።

አብረውት የታገቱት ሶስት የቱርክ መሀንዲሶች ከሰባት ወራት በኋላ ነፃ ቢወጡም እሱ ግን በእገታ ላይ ቆይቷል።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ቤተሰቦቹ ከእገታው እንዲለቀቅ አዲስ ተማጽኖ አቅርበዋል።

ቀደም ሲል በሳህል አካባቢ ታግተው የነበሩትን ቫን ዴቬንተር እና ሌሎች ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጊፍት ኦፍ ዘ ጊዘቨር ተሳትፏል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የአልቃይዳ አጋር የሆነው ዣማት ናስር አል ኢስላም ወል ሙስሊሚን በ2018 የ3 ሚሊየን ዶላር የማስለቀቂያ ገንዘብ ጠይቆ የነበረ ሲሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ገንዘቡን ወደ 500 ሺህ ዶላር ዝቅ እንዲል ተደራድሮ ነበር።

ሆኖም የቫን ዴቨንተር ቤተሰቦች እና ቀጣሪ ድርጀት ገንዘቡን ለመክፈል ባለመቻላቸው በመጨረሻ ታጣቂዎቹ ቅዳሜ ዕለት “ያለ ቅድመ ሁኔታ” እንደለቀቁት ገልጿል።

አልቃይዳ በኢስላሚክ ማግሬብ (AQIM) የተሰኘው ታጣቂ ቡድን እና በሰሜን እና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ሌሎች አክራሪ ቡድኖች አፈናን እና የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅን እንደ ገንዘብ ማሰባሰብያ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

በ1990ዎቹ በአልጄሪያ በተካሄደው መራር የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ የሆነው ይህ ቡድን ከሰሃራ በረሃ በስተደቡብ በሚገኘው የሳህል ክልል እና በማሊ እና በቡርኪናፋሶ ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

እ.ኤ.አ. በ2013 የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ቡድኑን እና አጋሮቹን ለመፋለም 5,000 ወታደሮችን ወደ ማሊ የላከች ሲሆን በ2020 የAQIM መሪ አብደልማሌክ ድሮክደልን ገድላለች።