
ከ 5 ሰአት በፊት
የእስራኤል መከላከያ ተኩሶ የገደላቸው እስራኤላዊ ታጋቾች እርዳታን የሚማጸኑ ጽሁፎች በጨርቅ ላይ ጽፈው ነው ተባለ።
ጽሁፎቹንም ለማስፈር የተራረፈ ምግብ መጠቀማቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
አርብ እለት የተገደሉት ሶስቱ እስራኤላዊ ታጋቾች በነጭ ጨርቅ ላይ እርዳታን የሚጠይቅ ጽሁፎች አስፍረው እንዲሁም እያውለበለቡ ነበር ተብሏል።
ሶስቱ ታጋቾች ተተኩሰው በተገደሉበት ህንጻ ለተወሰነ ጊዜ ቆይተው ሊሆን እንደሚችል ባለስልጣናቱ ያምናሉ።
እሁድ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ታጋቾቹ በተገደሉበት ህንጻ ባደረገው ፍተሻ በዓለም አቀፍ ደረጃ እርዳታን ለመጠየቅ የሚጠቀሙበትን ‘ኤስኦስ’ ቃል እንዲሁም ‘እባካችሁ እርዱን ሶስት ታጋቾች’ የሚሉ ጽሁፎች የሰፈሩበት ጨርቅም አግኝቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል እየፈጸመችው ባለችው የማያባራ የአየር ጥቃት 90 ሰዎች በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ እሁድ እለት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ቢቢሲ የሟቾቹን ቁጥር ማረጋገጥ አልቻለም።
በዚህ ጥቃት ሁለት ቤተሰቦችን ያስጠለለ የመኖሪያ ህንጻ መመታቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሐማስ እንዲሁም በሌሎች አጋር ቡድኖች የተያዙ 120 የሚሆኑ ታጋቾች ይገኛሉ።
የታጋቾቹ መገደልንም ተከትሎ በጋዛ የቀሩት ታጋቾችም እንዲለቀቁ ከስምምነት ላይ እንዲደረስ በባለስልጣናቱ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና በርትቷል።
እስራኤል ሶስት የታገቱ ዜጎቿን ተኩሳ የገደለችው በስህተት መሆኑንም አስታውቃለች።
የእስራኤል ባለስልጣናት ነጭ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ የነበሩ ግለሰቦችን ተኩሶ መግደል“ከጦሩ አሰራር ጋር የሚቃረን ነው” ብለዋል።
ታጋቾቹ የተወሰዱት ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል በከፈተው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች በተገደሉበት ወቅት ነው።
- የእስራኤል ጦር ታጋቾችን ተኩሶ በገደለበት ወቅት ነጭ ጨርቅ እያውለበለቡ እንደነበር አስታወቀ17 ታህሳስ 2023
- የእስራኤል ጦር ሦስት ታግተው የነበሩ የገዛ ዜጎቹን በስህተት መግደሉን አስታወቀ16 ታህሳስ 2023
- ከ10 ዓመት በኋላ አስከሬናቸው በተዘጋ ቤት በተገኘው ሴት ሞት የተጋለጠው የሆላንዳውያን ብቸኝነትከ 6 ሰአት በፊት
እስራኤል ሐማስን አጠፋለሁ በሚል ምላሽ የማያባራ እና የተቀናጀ ጥቃት የከፈተች ሲሆን በዚህም ከ18 ሺህ ፍልስጤማውያን በላይ ተገድለዋል።
ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት መሆናቸውንም የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል።
በእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ሼጃይያ ሰፈር የተገደሉት ታጋቾች የ28 አመቱ ዮታም ሃይም፣ የ22 ዓመቱ ሳመር ታላላካ እና የ22 አመቱ አሎን ሻምሪዝ ናቸው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለስልጣን እንደተናገሩት ከወገባቸው በላይ እርቃናቸውን የነበሩት ሶስት ታጋቾች ከህንጻ ሲወጡ መታየታቸውን ነው።
ከሶስቱ አንዱ በዱላ ላይ የተጠመጠመ ነጭ ጨርቅ እያውለበለበ እንደነበርም የእስራኤል መከላከያ የመጀመሪያ ምርመራው ግኝት ያሳያል ብለዋል።
ታጋቾቹ በአስር ሜትሮች ርቀት ላይ የነበሩ ሲሆን ከእስራኤል ወታደሮች አንዱም “አሸባሪ” ሲል ተኩስ እንደከፈተባቸው እኚሁ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል። ሁለቱ ወዲያውኑ ሲገደሉ ሶስተኛው ቆስሎ ወደ ህንጻው ተመልሷል።
የድረሱልኝ እርዳታ ጩኸት በዕብራይስጥ ቋንቋ መሰማቱንም ተከትሎ የጦሩ አዛዥ ወታደሮቹ መተኮሳቸውን እንዲያቆሙ አዘዙ።
የቆሰለው ታጋች እንደገና ብቅ ባለበትም ወቅት በጥይት ተመትቶ መገደሉንም ባለስልጣኑ አስረድተዋል።