ወደ የመን ለመሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚጠባበቁበት የኦቦክ የባሕር ዳርቻ
የምስሉ መግለጫ,ወደ የመን ለመሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚጠባበቁበት የኦቦክ የባሕር ዳርቻ

ከ 6 ሰአት በፊት

“እንዴት ናችሁ?”. . . . . . “Akkam jirtu?”

በጎናችን እያለፉ ለነበሩት ስደተኞች ያቀረብነው ሰላምታ ነበር።

በጂቡቲ በረሃ በየጥጋ ጥጉ ተስፋ ቆርጠው ለተቀመጡ እና ነገ የሚያመጣውን ለማይገምቱ፣ ቀጣዩ ምግባቸውን ማን እንደሚመጸውታቸው ለማያውቁ ኢትዮጵያውያን ይህ ሰላምታ ያልጠበቁት ነበር።

በቀይ ባሕር ዳርቻዋ የጂቡቲ ከተማ ኦቦክ ነው የምንገኘው። ይህቺ ከተማ የመንን አሻግረው ለሚያልሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሸጋገርያ ናት።

በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የተሻለ ሕይወት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር በማሰብ በጂቡቲ በኩል ያቋርጣሉ።

እንደ ዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት መረጃ መሠረት ካለፈው ዓመት ጥር እስከ 2016 ኅዳር ድረስ ብቻ በጂቡቲ አድርገው 95 ሺህ ፍልሰተኞች የመን ደርሰዋል።

በኦቦክ የባሕር ዳርቻ ሰላምታ የሰጠናቸው ስደተኞች፣ የእንዴት ናችሁ ጥያቄያችንን ሲሰሙ፣ ዐይናቸው በደስታ በርቶ እጅ ነሱን።

በቀይ ባሕር ዳርቻ በተንጣለለችው እና ለየመን በቅርብ ርቀት በምትገኘው የጂቡቲዋ ኦቦክ ከተማ፣ አናት በሚበሳ ፀሐይ መካከል ላይ ታች ሲሉ የሚታዩት ኢትዮጵያ ስደተኞች ብቻ ናቸው።

አገሬው በሙሉ ከፀሐይ ለመሸሽ በየቤቱ ከቷል።

ኦቦክ፣ ነዋሪዎቿ ሀዩ በማለት የሚጠሯት ከተማ ነች። ወደ የመን ለመሄድ የሚሹ እና ከየመን የሚመለሱ የሚገናኙባት ከተማም ናት።

ኦቦክ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የማያውቁትን አገር ናፍቀው የሚሰደዱ የኢትዮጵያ አፍላ ወጣቶችን ታስተናግዳለች።

ያነጋገርናቸው አብዛኞቹ ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ናቸው።

እንኳን አገር ሊያቋርጡ፣ ከቀያቸው ርቀው የሚያውቁ አይመስሉም። የረባ ጫማ አላደረጉም። ልብሳቸው ነትቧል። ሰው በሞላበት ከተማ ውስጥ ከሰው ተነጥለው ይኖራሉ።

እስር ሸሽተው ወይንም በፖለቲካ አይደለም ከአገር የወጡት። ግጭት ከሚያስጨንቃት ኢትዮጵያ ሥራ አጥተው የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በነዳጅ ወደ ናጠጠችው ሳዑዲ አረቢያ ያማተሩ ናቸው።

እነርሱም “ሠርተን ለመኖር ነው የወጣነው” ሲሉ ይሰማሉ።

ከሐረርጌ፣ ከጅማ፣ ከአርሲ፣ ከወሎ እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነው የመጡት።

ቀይ ባሕርን ፊት ለፊቱ ካደረገ አንድ ቤት አጥር ጥግ ሰብሰብ ብለው ተቀምጠው በኦሮምኛ ያወራሉ። የተወሰኑት እራፊ ጨርቅ ዐይናቸውን ሸፍነው በጀርባቸው ተንጋለዋል። ሰላም ስንላቸው ከተኙበት ለመነሳት ፍላጎት ያላሳዩም ነበሩ።

ካጠገባቸው ካለ ድንጋይ ላይ ደግሞ ከአስር በላይ የሚሆኑት ተቀምጠዋል።

ጂብሪል* ገና አፍላ ወጣት ነው። እንባ ባዘለ ድምጽ “በሺህዎች የሚቆጠሩ እየመጡ የተወሰነው ይሰምጣል፣ ሌላው በረሃብ ይሞታል። እዚህ ልናልቅ ነው። ለመንግሥታችን አቤት በሉልን” ይላል።

የወጣትነት ተስፋው እና አቅሙ አብሮት የለም። ክዶታል። ከአገር ርቆ ቋንቋ ተቸግሮ፣ የሚበላው አጥቶ በችግር ላይ ነው ያለው።

እነዚህ ወጣቶች እንደሚሉት ከ25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ለደላላ ከፍለው ከአገር ቢወጡም፣ ደላላው የውሃ ሸታ ሆኖ ተስፋቸው እንደ ጉም በኖ ቀርቷል።

ለዚያ ነው በኦቦክ ባሕር ዳርቻ ላይ ‘በረንዳ አዳሪ’ ሆነው የቀሩት።

“ረሃብ ነው ያስቸገረን”

በነዳጅ የበለጸጉት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ስደተኞቹን ላለመቀበል በራቸውን ሲዘጉ፣ ኦቦክ ግን ስደተኞችን በመቀበል እና በማስተናገድ በመልካም ትጠራ ነበር።

አሁን ግን የተሰላቸች ይመስላል።

ካሳደጓቸው ቤተሰቦች በላይ ሕገወጥ አዘዋዋሪ ደላላዎችን አምነው፣ የማያውቁትን ናፍቀው ከቀያቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንም ይህንን የተረዱ ይመስላል።

ያነጋገርናቸው ሁሉ ስለ ረሃብ ነው የሚያወሩት።

ለወላጆቻቸው ሸክም ላለመሆን ቀያቸውን ጥለው ተሰድደው እዚህ የባዕድ ሕዝብ ሸክም ሆነዋል።

ሙክታር* የአዳባ ልጅ ነው። ደላላ ከአዳማ ነበር የወሰደው። “ከሰው ቤት እየለመንን ነው እየበላን ያለነው።” ይላል።

ከጅማዋ ሲግሙ የመጣው አብዲም* “ምንም ሥራ የለንም። ሰው በሚሰጠን ነው የምንኖረው” ሲል ይናገራል።

ከእርሱ አጠገብ የተቀመጠው ሙህዲን ደግሞ ከጌራ ነው የመጣው።

“በረሃብ እና በጥም ውስጥ ነው እዚህ የደረስነው። ደላላ ደግሞ ገንዘባችንን በልቶ ጠፍቶብናል። ሰዉ ከኢትዮጵያም፣ ከየመንም መጥቶ እዚህ ፈስሷል።”

እነዚህ ስደተኞች እዚህችው ትንሽ ከተማ ውስጥ ሠርተው እንዳይበሉ ያስቸገራቸው ፖሊስ እንደሆነ ይናገራሉ።

ፖሊስን ሲሸሹም የተጎዱ እንዳሉ ያስረዳሉ።

“ይኸው እጄን ሰበሩኝ። አሁን መዘርጋት አልችልም” ሲል ያክላል እጁን እያሳየ።

በኦቦክ ከተማ ውስጥ በመምህርነት የሚያገለግሉት መሐመድ አሚን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለዓመታት ታዝበዋል።

“ብዙ ችግር ነው ያለባቸው። ብዛታቸው አንድ በል። በየቤቱ እየሄዱ በር እየቆረቆሩ ምግብ ይጠይቃሉ። ጠዋት፣ ቀን፣ ማታ አይሉም። ሁለተኛ ምግብ ቤት ገብተህ ምግብ አዘህ ልትበላ ስትል አስር ሆነው ሲመጡ ስታይ መብላት ይቸግርሃል፤ ያሳዝኑሃል።”

ከባሌ ደሎ መና ከአምስት ወራት በፊት የወጣው አብዱል ናስርም* በቀን አንዴ መብላት አቅቶታል።

“የሆድ ነገር አስቸጋሪ ነው። የሰው በር እየቆረቆርን ሰዉ ሊጠላን ነው። መሻገርም አልቻልንም። ደላላ ገንዘባችንን በልቶ መና ሆነን ቀርተናል።

“እነዚህ ስደተኞች በቀን አንዴ የማይበሉበትም ጊዜ አለ። አንዳንዱ ይሰጠናል። አንዳንዱ ያባርረናል። ሰዉ የተቻለውን ያህል ይሰጠናል። ለምሳሌ ሰባት ሰው የአንድን ሰው በር ያንኳኳል። ከሰባቱ የሚያገኘው አንድ ሰው ነው። ሌላው በልቶ ሲውል ሌላው ባዶ ሆዱን በባሕር ዳርቻው ድንጋይ ላይ ይተኛል” ሲል የነዋሪውን አስተያየት ያጠናክራል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቀን የማይሰጥ ሆድ ሆኖባቸው የሚያደርጉት ነገር እነርሱንም አሳቋቸዋል። ግን ደግሞ ከመሞት መሰንበት ብለው ገፍተውበታል።

ሙሳ አደም ሚገኔ፣ የኦቦክ ከተማ አስተዳዳሪ ናቸው። አስተዳዳሪው በኦቦክ ስደተኞች ከከተማ እንዲርቁ መደረጋቸውን ያውቃሉ።

“ከኢትዮጵያ መጥተው እዚህ ሠርተው የሚኖሩ አሉ። ስደተኞቹ ግን በዙ፤ ሥራ ብቻ ሳይሆን ልመናው በዛ። ምግብ ቤት ስትሄድ አስር ሆነው ቆመው ታያቸዋለህ። የምግብ ቤት ባለቤቶች ለአስተዳደሩ አቤቱታ ያቀርባሉ። ባለሱቆችም እንዲሁ” በማለት የመከልከላቸውን ምክንያት ያስረዳሉ።

“የሞቱትን መሰብሰብ ያስቸግራል። ነገር ግን ዛፍ ስር፣ መንገድ ዳር፣ ቤት ስር እንዲሁም ባህር ውስጥ ሰምጠው የሚሞቱት ብዙ ናቸው።” የኦቦክ ከተማ አስተዳዳሪ
የምስሉ መግለጫ,“የሞቱትን መሰብሰብ ያስቸግራል። ነገር ግን ዛፍ ስር፣ መንገድ ዳር፣ ቤት ስር እንዲሁም ባህር ውስጥ ሰምጠው የሚሞቱት ብዙ ናቸው።” -የኦቦክ ከተማ አስተዳዳሪ

“እየቀበርን ነው እዚህ የደረስነው”

ከድር* ከአገር ሲወጡ ከድሬዳዋ በሲኖትራክ ከተሳፈሩት ወጣቶች መካከል አንዱ እንደ ሞተባቸው ያስታውሳል።

“ዛፍ ስር ነው ትተነው ያለፍነው። የሆነ መንገድ ላይም አንድ የሞተ ልጅ አግኝተን እርሱንም ቀብረን አለፍን። አፈር ምሰን፣ ድንጋይ ከበንበት ነው የምናልፈው። ሲታመሙ በሰው ሸክም መጓዝ ከባድ ስለሆነ፣ በዛፍ ጥላ ስር እየተውናቸው ነው የምናልፈው።”

እነዚህ ታዳጊዎች በትውልድ መንደራቸው የሰው ቀብር ላይ እንኳ መገኘታቸው ያጠራጥራል።

በስደት መንገድ ግን እነርሱው አስታማሚ፣ እነርሱው የሞተ ገናዥ፣ ለሟች የመጨረሻውን ማረፍያ ጉድጓድ ማሽ፣ እንዲሁም ቀብር ፈጻሚ ሆነው ያውቃሉ።

ሟችን አፈር ከማልበሳቸው በፊት እንደየ እምነታቸው ጸሎት አድርሰው፣ አልቅሶ መቅበር እና ጉዞን መቀጠል የዕጣ ክፍላቸው አካል ሆኗል።

ከድር “ደላላ እንደሚዋሸው አይደለም። ብዙ ሰው መንገድ ላይ ሞተብን። በረሃብ፣ በጥም ከአጠገባችን መንገድ ላይ የቀሩ አሉ” ይላል።

ኢትዮጵያውያን በስደት መንገድ ላይ በመኪና አደጋ፣ በበሽታ እንዲሁም በረሃው በርትቶባቸው መንገድ ላይ የሚቀሩ ብዙ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ጅቡቲ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት በእጥፍ የጨመረ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።

በዚሁ ዓመት ብቻ በሚጓጓዙበት ትራንስፖርት ላይ በህመም እንዲሁም በአስከፊ የአየር ጠባይ፣ ባሕር ላይ በመስመጥ እና በግጭት የተነሳ 89 ስደተኞች መሞታቸው አልያም መጥፋታቸው ተመዝግቧል።

ከዚህ የሚልቀው ሞት እና መሰወር ደግሞ ሳይመዘገብ እንደቀረ ይታመናል።

ካለፈው ዓመት ሐምሌ እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 54 ስደተኞች ጂቡቲ ውስጥ መሞታቸው እንደተመዘገበ የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

23 ስደተኞች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

በተለያዩ ምክንያቶች እንደወጡ የቀሩ ስደተኞች የቀብር ስፍራ
የምስሉ መግለጫ,በተለያዩ ምክንያቶች እንደወጡ የቀሩ ስደተኞች የቀብር ስፍራ

“የሞቱትን መሰብሰብ አስቸግሮናል”

ከኦቦክ ከተማ ወደ በረሃው መውጫ ላይ የቀብር ስፍራ ይገኛል።

እግር ጥሎት የመጨረሻውን እስትንፋስ በዚህች ከተማ የተነፈሰ መጤም ሆነ ነዋሪው የሚቀበረው እዚህ ነው።

የቀብር ስፍራን ከከተማዋ ነዋሪዎች እና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ሄደን ከጎበኘን በኋላ፣ ምን ያህል ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ በስፍራው ተቀብረው እንደሆ የተጠየቁት የኦቦክ ከተማ አስተዳዳሪ ስሜታቸው ተለዋወጠ።

ጥያቄያችንን ከመመለሳቸው በፊት መንገሽገሽ ታየባቸው።

ከዚያም ንግግራቸውን የጀመሩት በምሬት ነው “የሞቱት ብዙ ናቸው። ብዙዎችን ቀብረናል። ትክክለኛውን ቁጥር ማወቅ ያቃተን ተራራ ተራራውን የሚሄዱ ስደተኞች ሞተው ከሳምንት ወይንም ከወር በኋላ ገጠር የሚኖሩ ነዋሪዎች ነግረውን ለመሰብሰብ ስለምንሄደው ነው። እንደዚያም ሆኖ የሞቱ እና የተቀበሩ ብዙ ናቸው።”

የቢቢሲ ባልደረቦች በጂቡቲ ኦቦክ ከተማ የሚገኘውን የቀብር ስፍራ በተመለከቱበት ወቅት መረዳት እንደቻሉት፣ አገሬው በቀኝ በኩል፣ በግራ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚቀበሩ ነው።

“የሞቱትን መሰብሰብ ያስቸግራል። ነገር ግን ዛፍ ስር፣ መንገድ ዳር፣ ቤት ስር እንዲሁም ባሕር ውስጥ ሰምጠው የሚሞቱት ብዙ ናቸው። የታመመ ወይንም የሞተ ካለ እየሄደች የምታመጣ አንድ መኪና አለችን” ይላሉ የከተማዋ አስተዳዳሪ።

የከተማዋ አመራሮች ባሕር ውስጥ ሰጥመው የሞቱ ኢትዮጵያውያንን ፎቶ አውጥተው ካሳዩን በኋላ፣ በቅርብ ጊዜ የተቀበሩ ስምንት ኢትዮጵያውያን ዝርዝርም ከማኅደራቸው አውጥተው አነበቡልን።

የኦቦክ ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህር፣ የሞቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አይተዋል፤ ቀብረዋልም።

“ሲሞቱ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው። ዛፍ ስር የሚሞቱ አሉ። ከቤት ጀርባ ሲሞቱ ሽታው ያስቸግራል” ይላሉ በምሬት።

መግቢያ የሌላቸው ስደተኞች ማዳበሪያን የመሳሰሉ ነገሮችን ተጠልለው በረሃው ላይ ይገኛሉ
የምስሉ መግለጫ,መግቢያ የሌላቸው ስደተኞች ማዳበሪያን የመሳሰሉ ነገሮችን ተጠልለው በረሃው ላይ ይገኛሉ

“’እዚሁ ነው የምናድረው. . .”

መኖሪያቸውንም ሆነ ማደርያቸውን ከቀይ ባሕር ዳርቻ ያደረጉት ስደተኞች አፋቸው ደርቆ፣ ፊታቸው ጠውልጎ፣ ኑሯቸው እና ውሏቸው ከባሕር ዳርቻው ላይ አድርገዋል።

ለማደርያቸው ሸራ፣ ማዳበርያ፣ ካርቶን የተቆራረጠ ልብስ እና የላስቲክ ኮዳ ከቀይ ባሕር ዳርቻ ባለው ድንጋይ ውስጥ ደልድለው ይታያል።

ቢቢሲ- እዚሁ ነው የምታድሩት

እዚሁ ነው የምናድረው።

ቢቢሲ- ከዘነበስ?

መሄጃ የለንም።

ከሚያድሩበት ብዙም ሳይርቁ ይጸዳዳሉ። የከተማዋ ነዋሪ ስደተኞቹ ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ የሚከለክልበት ምክንያት አንዱ ተላላፊ በሽታን ፈርቶ መሆኑን ነዋሪው “ልጆች አሉን፤ ተላላፊ በሽታ ሊያጠቃን ይችላል” ሲሉ ነግረውናል።

ቢቢሲ ቦታውን በጎበኘበት ወቅትም የኮሌራ ወረርሽኝ በከተማዋ ተከስቶ ነበር።

በባሕር ዳርቻው አካባቢ ያለው ድንጋይ ጉርብጥብጥ ያለ ነው።

“እዚሁ ባሕር ዳርቻ የተቀዳደደ ልብስ አንጥፈን ድንጋይ ውስጥ እየኖርን ነው። በሞት እና በሕይወት መካከል ነው ያለነው” አለ ከመካከላቸው አንዱ።

ያሉበትን ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው ነግረው ይሆን?

“እንዳይደነግጡ ቆንጆ ነው እንላቸዋለን። አሁን ያለንበትን ቤተሰባችን አያውቅም። ገንዘብ ላኩ ስንላቸው ከዚህ ቀድመ የላክነውስ? እያሉ እየላኩልን አይደለም” ይላሉ።

በአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን በርካታ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ የሚሻገሩባቸው መስመሮች
የምስሉ መግለጫ,በአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን በርካታ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ የሚሻገሩባቸው መስመሮች

“መመለስ እንፈልጋለን”

ቢቢሲ በኦቦክ የባሕር ዳርቻ ያገኛቸው ስደተኞች ወደ የመን መሻገር ወይም ደግሞ ወደ አገር መመለስ ተቸግረዋል።

“መመለሻው ቸግሮኝ ነው እንጂ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እፈልጋለሁ” ይላል ጂብሪል።

ኦቦክ ካገኘናቸው ውስጥ ሁሉም አዲስ ተጓዥ አልነበሩም። ወደ ሳዑዲ ተሻግረው የተመለሱም አሉበት።

ተማም* አንድ ዓመት የመን ቆይቷል።

“የሳዑዲ ድንበር ላይ ስደርስ በመሳርያ ሰው እየጨረሱ ነው። እጃቸው እና እግራቸው ተመትቶ እዚያው የቀሩ አሉ። ይህንን ሳይ ፈርቼ ነው ወደ ኋላ የተመለስኩት። ይኸው ከየመን ብመለስም አገር ቤት መግባት ቸግሮኝ እዚህ ተቀምጫለሁ።”

እነዚህ ስደተኞች በእግራቸው ለሳምንታት ተጓዘው ጂቡቲ የደረሱ ቢሆኑም፣ ለመመለስ ግን እንደ አመጣጣቸው ሊደፍሩ አልፈለጉም።

በከተማዋ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት መጠለያ ቢኖርም የማስተናገድ አቅሙ ከ300 ስደተኞች አይበልጥም። ስለዚህ በከተማዋ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑትን፣ የሚበሉት ያጡትን እና መመለስ የሚፈልጉትን ስደተኞች ሁሉ ለማስተናገድ አልቻለም።

ወደ አገር ለመመለስም ለደላላ ገንዘብ ከፍለው ለመሄድ የተቸገሩ እንዳሉ የሚናገሩ ስደተኞች ገጥመውናል።

ደላላ እንዲመልሳቸው ገንዘብ ከፍለው ተቸግረዋል።

ተማም “መንገዱ ሩቅ ሆኖ እንጂ መመለስ እንፈልጋለን። ከዚህ ለመግባት የምንከፍለው ገንዘብ የለንም። ሁለት ዙር ገንዘብ የከፈልን አለን። ልንሞት ደርሰናል ስንል ቤተሰብ ገንዘብ ይልካል፤ ያ ገንዘብ ግን ተበልቶ የት አንደሚደርስ አናውቅም። እኛ ግን ከዚህ አልራቅንም” ሲል ይናገራል።

ከሁሉም ስደተኞች ዝም ብሎ የንግግራችን ፍሬ ነገር የሚገመግም የሚመስለው ሌላው ወጣት፣ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ ከአገር መውጣቱን ይናገራል።

“እንደ ሰው ሠርተን እንለወጣለን ብለን ከአገር ራቅን፤ ችግሩ ግን ከእኛ ቀድሞ እዚህ ጠበቀን” ይላል ያለበትን ሁኔታ ሲያስረዳ።

በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቹን እደግፋለሁ ብሎ የወጣው ይህ ወጣት፣ ሃሳቡ ከሌሎች ስደተኞች ይለያል።

“አንድ ዕድል እሞክራለሁ። ምክንያቱም ወደ አገር ቤት ብመለስ ከቤተሰቤ የማገኘው ምንም ነገር ስለሌለ ትርፉ መረጋገም ይሆናል” በማለት መቆየት እንደሚፈልግ ይናገራል።

አንድ ዕድል ያለውስ የየመን ጉዞ ባይሳካስ. . .

*በዚህ ጽሁፍ ላይ ታሪካቸውን ያጋሩን ግለሰቦች ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀይሯል።