እየተመገቡ ያሉ አረጋውያን

ከ 6 ሰአት በፊት

በሆላንድ በ70ዎቹ የሚገኙ ሴት ከሞቱ ከአስር ዓመት በኋላ አስከሬናቸው በቤታቸው መገኘቱ አገሪቷ ብቸኝነትን ለመቅረፍ ለጀመረችው ብሔራዊ ዘመቻ መነሻ ሆኗል።

የአገሪቱ ፖለቲከኞችም እያንዳንዱ ዜጋ በማኅበረሰቡ ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው ይገባል በሚል በርካታ ተነሳሽነቶች ጀምረዋል።

አሳዛኝ ክስተቱ የተፈጠረው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነበር።

የ74 ዓመቷ ቤፕ ደ ብሩን አስከሬን በሮተርዳም በሚገኘው ቤታቸው ተገኘ።

አስከሬናቸው ሲገኝ አስር ዓመታትን አስቆጥሮ ነበር። ያን ሁሉ ዓመታትም መሞታቸውን ያወቀ ሰው አልነበረም።

በወቅቱ ደች ኢንዲስ ይባል በነበረው ስፍራ የተወለዱት እኒህ ግለሰብ በአስራዎቹ ዕድሜ እያሉ ወደ ኔዘርላንድ አቀኑ።

የስሜት መቃወስ ያጋጠማቸው ግለሰቧ ከአንድ ልጃቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትም ሙሉ በሙሉ በማቋረጥ ብቻቸውን ቀሩ።

ለዚያም ነው በአውሮፓውያኑ 2003 ሲሞቱ ማንም ያላወቀው።

ከግዛቲቷ የሚያገኙት የጡረታ ገንዘብ በቀጥታ ወደ ባንክ ሒሳባቸው ይገባል። የቤት ኪራያቸውም ቀጥታ ከሒሳባቸው ይቆረጣል።

ግለሰቧ መሞታቸው የታወቀው እና ለአስከሬናቸው መገኘት ምክንያት የሆነው የጋዝ መሐንዲሶች የሚጠግኑት ጉዳይ ኖሮ አፓርታማቸው ውስጥ መግባት ስለነበረባቸው ነው። ፖሊሶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ያልተከፈቱ እና የተከማቹ ፖስታዎችን አግኝተዋል።

ግለሰቧ መቼ እንደሞቱም ለማወቅ እነዚህ ክምር ፖስታዎች ጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋል።

የግለሰቧ በብቸኝነት መሞት እና አስከሬናቸው ለረጅም ዓመታት አለመገኘቱ ከተማዋን አስደንግጧል። ማስደንገጥ ብቻ ሳይሆን ብቸኝነትን ለመቅረፍ ወደ ተግባር እንዲገባም አነሳስቷል።

ሁጎ ደ ጁንግ የተሰኙ የአካባቢው ፖለቲከኛ ለአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ “በዚህ ትልቅ ከተማ ውስጥ ብቸኝነት ምን ያህል እንደተሰራፋ የሚያሳይ አሳዛኝ ምስል ነው” ሲሉም ተናግረው ነበር በወቅቱ።

ፖለቲከኛው ዕድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ የሮተርዳም የዕድሜ ባለጸጎችን የሚጎበኙ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበትን ዕቅድ ያወጡት በዚያን ጊዜ ነው። እነዚህ በጎ ፈቃደኞች የዕድሜ ባለጸጎቹን በመጎብኘት ያጫውቷቸዋል።

የ74 ዓመቷ ቤፕ ደ ብሩን ይኖሩበት የነበረው ቤት
የምስሉ መግለጫ,የ74 ዓመቷ ቤፕ ደ ብሩን ይኖሩበት የነበረው ቤት

ደ ጁንግ የአገሪቱ የጤና፣ ደኅንነት እና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙም ይህንኑ ዕቅዳቸውን በማስፋት ብሔራዊ አድርገውታል። በአገር ደረጃም አረጋውያን የሚያጋጥማቸውን ብቸኝነት ለመቅረፍ በአውሮፓውያኑ 2018 አገራዊ ተነሳሽነትን ጀመሩ።

የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ይህ ብቸኝነትን ለመቅረፍ የተጀመረው ብሔራዊ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደሆነ ነው።

ብቸኝነትን በተመለከተ አስተማማኝ ዓለም አቀፋዊ አሃዞችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት የአውሮፓ ኅብረት ባደረገው የመጀመሪያው ጥናቱ ከስምንት ሰዎች መካከል አንዳቸው አብዛኛውን ጊዜ ብቸኝነት እንደሚሰማቸው ነው።

አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ ቢያንስ አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት እንደሚሰማቸው ጥናቱ ይፋ አድርጓል። ኔዘርላንድስ በአውሮፓ ውስጥ ካሉ አገራት ዝቅተኛ የብቸኝነት መጠን የሚታይባት ናት።

ስዕል እየሳሉ ያሉ አረጋውያን

ብቸኝነት ውስብስብ ችግር ነው። መንስዔዎቹም ደካማ የማኅበራዊ ግንኙነት ክህሎቶች፣ በሕይወት ላይ የሚከሰቱ ከፍተኛ ለውጦች እና መገለሎች ሊሆኑ ይችላሉ።

በተጨማሪም በአእምሮ እና በአካላዊ ጤንነት እክሎች እና በብቸኝነት መካከልም ከፍተኛ ቁርኝት አለ። በኔዘርላንድስ ለአስር ዓመታት ተግባራዊ የሆነው ብቸኝነትን የመቅረፍ ዕቅድ በርካታ ተቋማትን የሚያሳትፍ ነው። አማካሪዎች ከእያንዳንዱ ማዘጋጃ ቤቶች ጋር በመጣመር ዕቅዶችን እንዲነድፉ ድጋፍ ይሰጣሉ።

በተጨማሪም ማዘጋጃ ቤቶች የጤና ባለሙያዎች፣ በጎ ፈቃደኞች እና የንግድ ማዕከላትን ያሳተፉ የፀረ ብቸኝነት የትስስር መድረኮች እንዲመሰርቱ ያበረታታሉ።

በዚህም ምክንያት ብቸኝነትን የሚታገል ብሔራዊ ጥምረት የተፈጠረ ሲሆን፣ አባላቱም ባንኮችን፣ ሱፐር ማርኬቶችን፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን፣ የስፖርት ክለቦችን እና የባህል ተቋማትን ያካተተ ነው። ብሔራዊ ጥምረቱም ሃሳቦችን ለመለዋወጥ እና በጋራ ለመሥራት በዓመት ሁለት ጊዜ ትልልቅ ጉባዔዎችን ያካሂዳል።

መጨዋወት የሚችሉባቸው መደብሮች

ብቸኝነትን ለመታገል የታቀደው ብሔራዊ መነሳሳት በርካታ አዳዲስ መንገዶችንም አምጥቷል።

ለምሳሌ ጃምቦ የተሰኘው ትልቁ የመገበያያ መደብር በበርካታ ቅርንጫፎቹ ‘ክሌትስካሳ’ የተሰኘ ሃሳብን አስተዋውቋል።

ይህም በመደብሩ ውስጥ ጊዜያቸውን እየተጨዋወቱ ማሳለፍ ለሚፈልጉ ከገንዘብ ተቀባዮች ጋር የሚነገጋገሩበት ነው።

በአገሪቱ ባሉ መደብሮች ውስጥ ለመሸመት ገንዘብ ተቀባይ አያስፈልግም፤ ማሽኖቹ ይህንኑ ያደርጋሉ። በእነዚህ የመገበያያ መደብሮች ግን ከማሽኖቹ በተጨማሪም ገንዘብ ተቀባዮች ተመድበው አንዳንድ ነገሮችን መጨዋወት ይችላሉ።

የአገሪቱም ብሔራዊ የፓስታ አገልግሎት ከብቸኝነት ጋር እየታገሉ ያሉ ሰዎችን ለመለየትም የበጎ ፈቃደኞች ሠራተኞችን አሰማርቷል።

ሠራተኞቹ የነዋሪዎች የቤት መጋረጃ ካልተገለጠ፣ በቤታቸው አካባቢ ፖስታዎች ተከማችተው ከሆነ በመለየት የነዋሪዎቹን ዝርዝር በቅጾች ይሞላሉ። ይህም መረጃ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተላልፎ እንዲሰጥ ይደረግ እና እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል።

ይህ መርሃ ግብር በአሁኑ ወቅት በ19 ማዘጋጃ ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ቤፕ ደ ብሩይን የተባሉት ግለሰብ አስከሬን የተገኘበትን ስፍራ ጨምሮ በሮተርዳም ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች እርዳታ እንዲያገኙም ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጥቆማ ተልኳል።

 የ74 ዓመቱ ቲዎ ኒየንጂስ ከውሻዋ ጋር

ባለ አራት እግር ጓደኞች

ብቸኝነትን ለመከላከል የተቋቋመው ድረ ገጽ ውጤታማ የሆኑ ማኅበራዊ ድርጅቶችንም ያስታዋውቃል እንዲሁም ማዘጋጃ ቤቶች በዕቅዳቸው ውስጥ እንዲያካትቱም ያበረታታሉ።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ኦኦፖህ አንዱ ሲሆን በኔዘርላንድ ከሚገኙት አራት ትልልቅ ከተሞች የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ ያገኛል።

ይህ ድርጅት ሥራ የሚበዛባቸው የውሻ ባለቤቶች ከቤት እንስሳቶች ጋር ጊዜያቸውን ማሳለፍ የሚፈልጉ ወይም እንስሳቱን መንከባከብ የሚፈልጉ አረጋውያንን የሚያገናኝ ድረ ገጽ አለው። ለአዛውንቶቹ ነጻ ሲሆን ለውሻ ባለቤቶቹ አነስተኛ ገንዘብ ያስከፍላል።

ለአረጋውያኑ ከውሾቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍም የአካላዊ እና አዕምሯዊ ጤንነታቸውን እንደሚረዳ የድርጅቱ ዳይሬክር ኤለን ግሮነማን ይናገራሉ።

ድርጅቱ ከተመሠረተ ጀምሮ 4500 አረጋውያንን ከውሾቹ ባለቤቶች ጋር አገናኝቷል። የ74 ዓመቱ ቲዎ ኒየንጂስ ከጄኔት እና ከውሻዋ ቢኬል ጋር በዚህ ድርጅት አማካኝነት ተገናኝተዋል።

“በ70ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ ስትደርስ የነበሩህን ሰዎች፣ የመሠረትካቸውን ግንኙነቶች ልታጣ ትችላለህ” ይላሉ ቲዎ።

“ቢኬል ትንሽዬ ተወዳጅ ውሻ ነው፤ የሰዎችንም ቀልብ ይስባል። በርካቶች አሁን ያውቁኛል። ሲያልፉም ሰላም ይሉኛል። ከውሻው ባለቤት ጄኔትም ጋር መልካም ግንኙነትን መሥርተናል። ችግር ቢያጋጥመኝ ቀድሜ የምደውልላት ለእሷ ነው” ይላሉ።

በርካታ የዚህ ድርጅት ተጠቃሚዎች ከውሾቹ ባለቤቶች እና ከእንስሳቱ ጋር ከተገናኙ በኋላ የአካል ጤንነታቸው እና ማኅበራዊ ግንኙነታቸው መሻሻሉንም ገልጸዋል።

በብሔራዊ ደረጃ የተፈጠረው ብቸኝነትን የሚታገለው ተነሳሽነት እንደ ቲኦ ያሉ አረጋውያንን ለመርዳት ያለመ ነበር። ይሁን እንጂ ብቸኝነት በዕድሜ ባለጸጎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የዕድሜ ደረጃዎች ውስጥ ስር የሰደደ መሆኑ ግልጽ ሆነ።

ኦማ ሶዬፕ የተባለው ሾርባ የሚሸጠው ድርጅት ከትርፉ ግማሹን ምግብ የማብሰል ትምህርቶችን በነጸ ይሰጣል። በእነዚህ ክፍለ ጊዜዎችም ላይ አረጋውያኑን ከበጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ጋር ያጣምራል።

“ፕሮጀክቱን የጀመርነው በዕድሜ የገፉ በብቸኝነት የሚሰቃዩ አረጋውያንን ለመርዳት ነበር። ነገር ግን ከአረጋውያኑ በተጨማሪ በርካታ ብቸኝነት የሚሰማቸው ወጣቶች እንዳሉ ተረዳን። ለምሳሌ ለትምህርት ወደ ሌሎች ከተሞች የሚጓዙ ተማሪዎች በብቸኝነት ይጠቃሉ” በማለት ከድርጅቱ ባለቤቶች አንዷ ማርትጂን ካንተርስ ያስረዳሉ።

ምግብ በማብሰል የተጣመሩ አረጋውያን እና ወጣቶች

ለዚህም ነው በአገሪቱ የተቋቋመው ፀረ ብቸኝነት መርሃ ግብር ባለፈው ዓመት መላውን ሕብረተሰብ የሚያካትት ጥምረት የሆነው።

“ብቸኝነትን በአረጋውያን ላይ ብቻ መታገል ውስን መሆኑን ባለድርሻ አካላቱ ነግረውናል። ብቸኝነት በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል” ሲሉም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ሚሻ ስቱበኒትስኪ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት መደበኛ ያልሆኑ እንክብካቤ ሰጪዎችን፣ አረጋውያን ስደተኞችን እና ታዳጊዎችን ጨምሮ ሌሎች ለብቸኝነት ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎችን ለመመልከት ፕሮጀክቶች ተወጥነዋል።

የቀድሞ የወጣቶች አማካሪ ዮላንዳ ቫን ጊርዌ ታዳጊዎች ብቸኝነትን እየታገሉ ስለመሆናቸው መንግሥት ዕውቅና መስጠቱ መልካም እንደሆነ ትናገራለች። ከጥቂት ዓመታት በፊት ትርጉም ያለው ጓደኝነት መመሥረት ትግል የሆነባቸውን ወጣቶች የሚረዳ ‘ጆይን ዩ’ የተሰኘ የወጣቶች ክብብም አቋቁማለች።

“ወጣቶች በራሳቸው ላይ ያላቸውን አሉታዊ እሳቤዎችን እንዲያስወግዱ እንዲሁም በራስ የመተማመን እና ማኅበራዊ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንረዳቸዋለን” ትላለች።

እነዚህ ክፍለ ጊዜዎች በሠለጠኑ ባለሙያዎች የሚካሄዱ ሲሆን፣ አባላቱም ግቦቻቸውን እንዲያስቀምጡ ይረዷቸዋል።

“ከሰዎች ጋር መገናኘትም ሆነ መነጋገር ችግር ነበረብኝ። ከፍተኛ ጭንቀትም ይሆንብኝ ነበር። የምደውልለት ወይም የማወራው ሰው ሳይኖር በርካታ ምሽቶችን አሳልፍ ነበር” ሲል የ23 ዓመቱ ሉክ ያስረዳል።

“ጊዜ የማሳልፍበት ቦታ እንዳገኝ እንዲሁም ስለ ራሴ መልካም ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገኝ ቦታ ነው።” የሚለው ሉክ ቡድኑ እጁን ከፍቶ እንደተቀበለውም አስረድቷል።