የአውሮፕላኑ ስብርባሪ
የምስሉ መግለጫ,እአአ 1988 በስኮትላንድ ሰማይ ላይ ፈንድቶ ለ270 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን ስብርባሪ

ከ 6 ሰአት በፊት

የዛሬ 35 ዓመት፤ ለፈረንጆች ገና ሦስት ቀን ሲቀረው አንድ አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ ፈነዳ።

በውጡ የነበሩ 259 ተሳፋሪዎች በሙሉ አለቁ። ከ82 ዓመት ሽማግሌ ጀምሮ እስከ ሁለት ወር ጨቅላ ድረስ ነው የሞቱት። አንድም የተረፈ የለም።

እንኳንስ አውሮፕላኑን ተሳፍረው የነበሩት ይቅርና፣ አገር ሰላም ብለው በስኮትላንድ ገጠር ይኖሩ የነበሩ 11 ሰዎችም ሞተዋል። አውሮፕላኑ ‘ላያቸው ላይ ተከስክሶባቸው።

ከሟቾቹ ሁለት ሦስተኛው አሜሪካውያን ናቸው። 44ቱ ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ዜጋ ናቸው።

የበረራ ቁጥር ‘ፓን አም 103’ የመንገደኞች አውሮፕላን ከለንደን ወደ ኒው ዮርክ እየበረረ ነበር የዛሬ 35 ዓመት በሎከርቢ ሰማይ ላይ የጋየው።

ማን አጋየው? እስከ ዛሬም በማያሻማ እርግጠኝነት የወንጀሉ አቀነባባሪ በውል አይታወቅም። ይሁንና አንድ ተጠርጣሪ አገር አለች – ሊቢያ።

በተጨማሪም ሁለት ቁልፍ ተጠርጣሪዎች አሉ። መግራሂ እና መስዑድ።

የ72 ዓመቱ መስዑድ በአሜሪካ እስር ቤት ውስጥ አለ። በቅርቡ የፍርድ ሂደቱ ይጀመራል።

መስዑድ ቦምቡን ሠርቶታል ተብሎ ነው ከሊቢያ ወደ አሜሪካ የጋዳፊን ሞት ተከትሎ የተወሰደው።

ሁለተኛው ሰው መግራሂ ይባላል። ከረዥም የፍርድ ሒደት በኋላ ተፈርዶበት ነበር። ከዚያም ተፈታ። በካንሰር ታሞ ለመኖር ጥቂት ወር ነው የቀረበው በሚል ነው የተለቀቀው። ሦስት ዓመት ኖረና ሞተ።

መግራሂም እንደ መስዑድ ሊቢያዊ ነው። ነገር ግን እጁ የለበትም የሚሉ መላምቶች አሉ። አንዳንድ የተጎጂ ቤተሰቦች ሳይቀሩ የመግራሂን ንጽህና ይመሰክሩ ነበር።

በእርግጥ መግራሂ በሎከርቢው ጥቃት እጁ አለበት? ታሪኩ ረዥም ነው።

የምርመራው ውስብስብነት

ይህ ግዙፍ አውሮፕላን የወደቀባት የስኮትላንድ ገጠር ከተማ የዓለም ሁሉ ትኩረት የሆነችው በድንገት ነበር።

የጋየው አውሮፕላን 319 ቶን ስብርባሪ ወደቀባት። ፍንጥርጣሪው 845 ስኩዌር ማይል የሚሆን ቦታን ሸፈነ። እያንዳንዷ ፍንጣሪ ደግሞ መመርመር ነበረበት። አለበለዚያ ፍንጭ ከየት ይገኛል?

ከአደጋው በፊት በቀን በአራት ፖሊሶች የምትጠበቀው ይቺ የስኮትላንድ መንደር በአንድ ጊዜ ሺህ ፖሊስ ፈሰሰባት። ትልቋ የወንጀል ምርመራ ስፍራ ተብላም ተሰየመች።

ቀን ተሌት ምርመራው ቀጠለ። በመንደሯ የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ባልደረቦች ተሰማሩባት።

አንድ ሺህ አንድ መቶ መርማሪዎች እያንዳንዷን ስብርባሪ መልቀም ጀመሩ።

ሂደቱ ለሳምንታት ቀጠለ።

በአውሮፕላኑ አፍንጫ ሥር አካባቢ፣ ሻንጣ መጫኛው ላይ የፍንዳታ ምልክት ተገኘ።

የስኮትላንድ ፖሊስ እና ኤፍቢአይ ሰፊ ምርመራ ካደረጉ በኋላ አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን ቻሉ።

አውሮፕላኑ የፈነዳው በቶሺባ ራዲዮ ካሴት ማጫወቻ ውስጥ በተቀመጠ ቦምብ ነው። ቦምቡ ደግሞ በሳምሶናይት ሻንጣ ውስጥ ነበር የተቀመጠው።

መግራሂ
የምስሉ መግለጫ,እድሜ ልክ እስራት ተደፈርዶበት በእስር ላይ የቆየው ዋነኛው ተጠርጣሪ መግራሂ

ዋና ተጠርጣሪዎች ኢራን እና ፍልስጤም

አውሮፕላኑ በቦምብ መጋየቱ ከተደረሰበት በኋላ ማን ነው ከጥቃቱ ጀርባ ያለው? የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነበር።

የመጀመሪያዋ ተጠርጣሪ ኢራን ነበረች።

ለምን ከተባለ ከዚያ ቀደም ብሎ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በስህተት የኢራን አውሮፕላንን መትቶ ጥሏል። በዚህም 290 ኢራናውያን ተገድለዋል።

ስለዚህ ኢራን ይህንን ለመበቀል የሰነዘረችው ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ተገመተ።

ይህ የሎከርቢ ጥቃት ከመፈጸሙ ሦስት ወራት በፊት ደግሞ የምዕራብ ጀርመን ፖሊስ የፍልስጤም ነጻ አውጪዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቡድኖች መኖሪያ ቤት ላይ ድንገት አሰሳ አድርጎ ነበር።

ይህ ቡድን በራዲዮ ካሴት ማጫወቻ ቦምብ ሲያዘጋጅ ተደርሶበታል። ስለዚህ የሎከርቢው ጥቃት ፍልስጤሞች ያቀነባበሩት ይሆን?

ምርመራው ቀጠለ።

ድንገት ወደ ማልታ የሚወስድ አንድ ምልክት ተገኘ።

ለጨቅላ ሕጻናት የሚገዛው ቱታ የሚመስል ልብስ በሳምሶናይቱ ውስጥ ተገኝቶ ነበር። ከዚህ ልብስ ሌላ ደግሞ ዮኪ የሚል የንግድ ምልክት የያዘ ሱሪ ተገኘ።

ይሄ ሱሪ ከማልታ እንደተገዛ ተደረሰበት።

መርማሪዎች ወደ ማልታ በረሩ።

ልብሱ ስሊማ በሚባል ጎዳና ካለ አንድ ሱቅ ለአንድ ግለሰብ መሸጡ ታወቀ።

መርማሪዎቹ ባለሱቁን አገኙት።

ባለሱቁ በሚያስደንቅ ሁኔታ ልብሱን ለማን እንደሸጠው ያስታውሳል።

ባለሱቁ የገዛኝ ሰውዬ ሊቢያዊ ነው። ተራ ልብሶችን እና ዣንጥላም ገዝቶኝ እንደሄደ አስታውሳለሁ አለ።

የመግራሂን ፎቶ አሳዩት። ሰውዬው እራሱ መሆኑን አለ ባለሱቁ አረጋገጠ።

ይሄ መግራሂ የተባለው ሊቢያዊ ደግሞ ማልታ ሄዶ እንደነበር ተደረሰበት።

ማልታ ለምን ሄደ? ለዚያውም በሐሰተኛ ፓስፖርት። መግራሂ ተጠርጣሪ መሆን አለበት።

የመጀመሪያው ፍርድ

መግራሂ “እኔ ማልታ አልሄድኩም” አለ። ነገር ግን ማልታ መሄዱ እና ሐሰተኛ ፓስፖርት መጠቀሙ ተረጋገጠ።

ኮሎኔል ጋዳፊ መግራሂን አሳልፈው ይስጡ ተባሉ።

በፍጹም ዜጋዬን አልሰጥም ሲሉ ጥያቄውን ተቃወሙ።

በዚህም ምክንያት ምዕራባውያን ከፍተኛ ማዕቀብ ሊቢያ ላይ ጣለባት። ኔልሰን ማንዴላ እና የተባበሩት መንግሥታት ሽምግልና ገቡ።

በቃ ጉዳያቸው በገለልተኛዋ ኔዘርላንድስ ይታይ በሚል ስምምነት ተደረሰ።

ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤትም መግራሂን ጥፋተኛ ነው ብሎ የዕድሜ ልክ እስር በየነበት። ነገር ግን አሁንም ድረስ እንግሊዛውያን የሟች ቤተሰቦች መግራሂ ቦምቡን አልቀመመም፣ ንጹሕ ነው የሚል ግምት አላቸው። ከወንጀሉ ጀርባም ያሉት ኢራን እና ፍልስጤም እንደሆኑ ነው የሚያምኑት።

አሜሪካውያን የሟች ቤተሰቦች ደግሞ ጋዳፊ ናቸው ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው አሉ።

በአውሮፓውያኑ 2003 ሊቢያ ዜጎቿ ፈጽመውታል ለተባለው ጥቃት ኃላፊነቱን እንደምትወስድ በይፋ አሳወቀች።

በተጨማሪም በአውሮፕላኑ መጋየት ለሞቱ ሰዎች ካሳ እከፍላለሁ ብላ በመስማማትም 1.7 ቢሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ወሰነች።

ነገር ግን ይህም ጥያቄ አስነሳ። ሊቢያ በእርግጥ በጥቃቱ እጇ ስላለበት ነው ኃላፊነት የወሰደችው ወይስ ማዕቀቡ እንዲነሳላት?

የጋዳፊ ልጅ ከዓመታት በኋላ ይፋ እንዳደረገው፣ አባቱ ኃላፊነቱን የወሰዱት እጃቸው ስላለበት ሳይሆን ማዕቀቡ እንዲነሳ ስለፈለጉ ነው።

በሦስት ወር ይሞታል የተባለው መግራሂ ሦስት ዓመት ኖሮ ሞተ
የምስሉ መግለጫ,በሦስት ወር ይሞታል የተባለው መግራሂ ሦስት ዓመት ኖሮ ሞተ

የዋናው ተጠርጣሪ ሞት

መግራሂ በአውሮፓውያኑ 2008 በእስር ላይ ሳለ በካንሰር ታመመ። ሐኪሞቹ ቢበዛ ሦስት ወር በሕይወት ቢቆይ ነው አሉ።

የተቀሩትን በሕይወት የሚቆይባቸውን ወራት ከእስር ቤት ውጭ እንዲያሳልፍ፣ የስኮትላንድ መንግሥት በሐዘኔታ ከእስር እንዲፈታ ወሰነ።

አሜሪካውያን የሟች ቤተሰቦች ግን ይህ ውሳኔ ከፍተኛ ብስጭት ላይ ጣላቸው።

መግራሂ አገሩ ሊቢያ ሲገባ የጀግና አቀባበል ተደረገለት። የስኮትላንድ ሐኪሞች ሦስት ወር ብቻ ነው የቀረህ ያሉት መግራሂ ሦስት ዓመት ኖረ።

እሱ በሕይወት እያለ ጋዳፊ በሕዝባዊ አመጽ ከሥልጣን ተወግደው በጠላቶቻቸው እጅ ተገደሉ።

መግሃሪ በመጨረሻ በፈረንጆቹ 2012 ሕይወቱ አለፈ።

አዳዲስ ተጠርጣሪዎች

የጋዳፊ መሞት አዲስ የምርመራ በር ከፈተ።

የስኮትላንድ መንግሥት የጋዳፊን ሞት ተከትሎ ከሊቢያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት የጀመረው ጊዜ ሳያጠፋ ነበር። አሜሪካውያን መርማሪዎች ከአጋሮቿ ጋር በመሆን በፍጥነት ወደ ሊቢያ አቀኑ፤ አዲስ መረጃን ፍለጋ።

ሁለት አዳዲስ ተጠርጣሪዎች ተገኙ።

አንዱ መስዑድ ነው። ሌላኛው አልሳኑሲ ነው። አልሳኑሲ የጋዳፊ የደኅንነት ሹም ነው።

ይህ የምርመራ ሂደት ሊቢያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ስትገባ ተደናቀፈ።

በ2017 (እአአ) የመግራሂ ቤተቦች ይግባኝ አሉ። መግራሂ ከሞተ አምስት ዓመት ቢያልፈውም ስሙ ጠፍቷል ብለው ነው የከሰሱት።

ጉዳዩን የተመለከተው ኮሚሽን እንዲያውም መግራሂ በፓን አም ቦምብ እጁ እንዳለበት አዲስ መረጃ አግኝቻለሁ አለ።

ቦምቡን የሠራው መስዑድ ይሆን?

በሎከርቢ አደጋ 32ኛ ዓመት ላይ አሜሪካ በሊቢያ እስር ቤት የሚገኘው መስዑድ የሎከርቢን ጥቃት እኔ ነኝ ያቀነባበርኩት ብሎ አምኗል አለች።

መስዑድ በጋዳፊ ተቃዋሚዎች ላይ በሰነዘረው ጥቃት እስር ቤት ነው ያለው።

መስዑድ በሊቢያ እስር ቤት ሆኖ ተናዘዘ እንደተባለው ቦምቡን የሠራው ከመግራሂ ጋር ተባብሮ ነው።

አሜሪካ እንደምትለው መስዑድ በሊቢያ የደኅንነት ተቋም ውስጥ ይሠራ የነበረ ሰው ሲሆን፣ ቦምቡን ያዘጋጀው በጋዳፊ ትዕዛዝ እንደሆነ እና አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላም ጋዳፊ እንኳን ደስ ያለህ እንዳሉት በምርመራ ወቅት ተናዟል።

ጋዳፊ እጃቸው ካለበት ለምን ጥቃቱን መፈጸም ፈለጉ? ምን ለማሳካት?

የአሜሪካ እና ስኮትላንድ መርማሪዎች ምናልባት የጋዳፊ እርምጃ በቀል ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

ሊቢያ እና አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ እና 80ዎቹ ላይ በጠላትነት ይፈላለጉ ነበር።

በምዕራብ በርሊን አንድ የአሜሪካ ወታደሮች የሚያዘወትሩት መዝናኛ ቤት ነበር። በ1986 (እአአ) ቦምብ ፈነዳ እና 229 ሰዎች ቆሰሉ።

የያኔው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ለጥቃቱ ሊቢያን ተጠያቂ አደረጉ። ከ10 ቀናት በኋላ የበቀል እርምጃ ወሰዱ።

የአሜሪካ አየር ኃይል ትሪፖሊን እና ቤንጋዚን ደበደበ። ጥቃቱ ጋዳፊን ለመግደል ያለመ እንደነበር ይገመታል። ጋዳፊ ግን ተረፉ። ሌሎች 15 ሰላማዊ ሰዎች ሞቱ። ጋዳፊ በጉዲፈቻ የሚያሳድጓት ሕጻን ተገድላ ነበር፤ በዚህ የአሜሪካ የበቀል ጥቃት።

ምናልባት ጋዳፊ የሎከርቢውን ጥቃት በዚህ በቀል ተነሳስተው ፈጽመውት ይሆን?

አጊላ መስኡዲ ቦምቡን እኔ ነኝ የቀመምኩት ሲል ተናዟል ትላለች አሜሪካ
የምስሉ መግለጫ,አጊላ መስዑድ ቦምቡን እኔ ነኝ የቀመምኩት ሲል ተናዟል ትላለች አሜሪካ

የመጨረሻው ፍርድ

34ኛው የሎከርቢ የአውሮፕላን የቦንብ ፍንዳታ ጥቃት ሊታሰብ ዋዜማ አሜሪካ አንድ ዜና አሰማች።

እኔ ነኝ የፈጸምኩት ሲል ተናዟል ያለችው ሊቢያዊ መስዑድ ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠቱን።

መስዑድ ከሊቢያ ለአሜሪካ የተሰጠበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል። ስኮትላንድ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ነው ብትልም፤ የመስዑዲ ቤተሰቦች ግን ከተኛበት አልጋ ተጎትቶ ነው የተወሰደው ይላሉ።

መስዑዲ ሃይማኖተኛ እና በሎከርቢው ጥቃት እጁ የሌለበት ሰው ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

አሜሪካ ከተወሰደ በኋላም ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኝነቱን ክዶ ተከራክሯል።

መስዑዲ ቦምቡን የሠራሁት እኔ ነኝ ሲል ተናዘዘ ያሉት የሊቢያ ባለሥልጣናት ነበሩ።

መስዑዲ በአሜሪካ ፍርድ ቤት መሞትን የሚመርጥ አይመስልም። እጁ እንዳለበት መናዘዙ ምን ያተርፍለታል?

ምናልባት ስለ ሎከርቢ ጥንቅቅ ያለ መረጃ ያለው ሰው አብደላ ሳኑሲ ነው። ሳኑሲ የሊቢያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ የነበረ ሰው ሲሆን፣ ያለእርሱ እውቅና ብርጭቆ አትሰበርም የሚባልለት ሰው ነው።

አሁን የሚገኘው ደግሞ በሊቢያ እስር ቤት ውስጥ ነው።

ይህ 35 ዓመት ሙሉ ያልተመለሰው ጥያቄ ቀጥሏል። የሎከርቢ የአውሮፕላን ፍንዳታን ማን አቀነባበረው?