ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

18 ታህሳስ 2023, 16:50 EAT

ግዙፉ ነዳጅ አምራች ቢፒ (ብሪቲሽ ፔትሮሊየም) በደኅንነት ስጋት ምክንያት ነዳጅ የጫኑ መርከቦቹ በቀይ ባሕር በኩል ለተወሰነ ጊዜ ማለፋቸውን እንደሚያቆሙ አስታወቀ።

ኩባንያው ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ በቀይ ሕር የሚያደርጉት ጉዞን ለማቋረጥ የወሰነው በቅርቡ በሁቲ አማጽያን መርከቦች ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነው።

ይህን ውሳኔ በጊዜያዊነት ያስተላለፈው በአካባቢው ያለው “የደኅንት ሁኔታ አስጊ ስለሆነ ነው” ሲል አብራርቷል።

በየመን በሁቲ አማጺያን ዒላማ መሆናቸውን ተከትሎ ሌሎች ዓለም አቀፍ የባሕር ጭነት አመላላሽ ድርጅቶች መርከቦቻቸው በቀይ ባሕር በኩል እንዳያልፉ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።

ከግዙፍ የመርከብ ጭነት አጓጓዦች መካከል አንዱ የሆነው ተቋም የእስራኤልን ካርጎ በቀይ ባሕር በኩል ማስተላለፍ ማቋረጡን አስታውቋል።

ኤቨር ላየን የተባለው ተቋም መርከቦች “ተጨማሪ ትዕዛዝ እስከሚተላለፍ ድረስ” ጉዞ እንዲያቋርጡ መወሰኑን ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።

ለነዳጅ እና ጋዝ እንዲሁም ቁሳቁስ ዝውውር የቀይ ባሕር መስመር ከሚመረጡ መንገዶች ዋነኛው ነው።

በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጽያን ባብ አል-ማንዳብ ወይም ‘ጌት ኦፍ ቲርስ’ በሚባለውን እና 32 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚሆነው መተላለፊያ ሰርጥ በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ።

አማጽያኑ ሐማስን እንደሚደግፉ የገለጹ ሲሆን፣ ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦችን በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እና በሚሳኤል ዒላማ እንዳደረጉም አስታውቀዋል።

መርከብ

በየመን አማጺ ቡድን ጥቃት የተፈጸመባቸው የጭነት መርከቦች ወደ እስራኤል እየተጓዙ ያሉ መሆናቸው ግን ግልጽ አይደለም።

ቢፒ “የሠራተኞቻችን ደኅንነት አደጋ ውስጥ ስለወደቀ እና በቀይ ባሕር የደኅንነት ጥበቃ አስጊ ስለሆነ ለጊዜው በቀይ ባሕር በኩል ማለፍ አቁመናል። በቀጠናው ያለው ሁኔታ ሲለወጥ ጉዳዩን መልሰን እንገመግማለን” ብሏል።

በዓለም ሁለተኛው ግዙፍ የመርከብ ጭነት አጓጓዥ ድርጅት የሆነው መርስክ ሁኔታውን “አሳሳቢ” ሲል ባለፈው ሳምንት አርብ ገልጾታል።

ይህን ያለው መርከቦቹ ከተቃጣባቸው ጥቃት “ለጥቂት ካመለጠ” በኋላ ነው።

ሜዲትራኒያን ሺፒንግ ካምፓኒ (ኤምኤስሲ) የተባለው የዓለም ግዙፍ የመርከብ ጭነት መጓጓዣ አገልግሎት ሰጪ መርከቦቹን በዚህ መንገድ ማሳለፍ እንደሚያቆም ገልጿል።

ኤምኤስሲ ፕላቲንየም የተባለው መርከቡ ከቀይ ባሕር ሲወጣ ባለፈው ሳምንት አርብ ጥቃት ደርሶበታል።

ሀፓግ-ሎይድ እና ሲኤምኤ-ሲጂኤም የተባሉ ተቋሞችም በቀይ ባሕር በኩል የሚያደርጉትን ጉዞ አቋርጠዋል።

ሀፓግ-ሎይድ ስለ ሁኔታው አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

ኤቨርግሪን ላየን እንዳለው በእስያ እና በሜድትራኒያን እንዲሁም በአውሮፓ እና በአሜሪካ ምሥራቃዊ መዳረሻ በኩል ያለውን ጉዞ አቋርጧል።

ረጅም ርቀት ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በተባለ መስመር መርከቦቹ እንደሚጓዙም አስታውቋል።

መርከቦች በቀይ ባሕር በኩል የባብ አል-ማንዳብ መተላለፊያን መጠቀም ሲያቆሙ ረዥም በሆነው የደቡብ አፍሪካ መስመር ለመጓዝ ይገደዳሉ።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው የሠራተኞች እና መርከቦችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል እንደሆነ እና በቀጠናው ያለው ሁኔታ ክትትል እንደሚደረግበትም ተገልጿል።