
18 ታህሳስ 2023, 14:20 EAT
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚያቀርቧቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን አዲስ ሰብሳቢ ሹመት ነገ ማክሰኞ ታኅሣሥ 9/2016 ዓ.ም. ሊያጸድቅ ነው።
ከወራት በፊት በፈቃዳቸው ሥራቸውን የለቀቁት ብርቱካን ሚደቅሳን የሚተኩትን የቦርዱን ሰብሳቢ ምክር ቤቱ በነገው መደበኛ ስብሰባው ላይ ሹመቱን እንደሚጸድቅ የቢቢሲ ምንጮች አረጋግጠዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ከቦርዱ ሰብሳቢ ሹመት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሹመት ይጸድቃል።
ለቦርዱ ሰብሳቢነት ሁለት ዕጩዎች ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ኅዳር 22/2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መቅረባቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ጨምሮ የቦርዱ አባላት የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ ቦርዱን ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ባለው ግነኙነት የመወከል ሥልጣን አላቸው። ከዚህ በተጨማሪም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አመራርን ስብሰባ የመጥራት እና የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ለቦርዱ ሰብሳቢ እንዲሆኑ በዕጩነት የቀረቡት ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ እና አቶ ታደሰ ለማ ናቸው። ሁለቱን ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻ ዕጩነት ያቀረበው ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዋቀሩት፤ የዕጩ መልማይ ኮሚቴ ነው።
- ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት በዕጩነት የቀረቡት ግለሰቦች እነማን ናቸው?4 ታህሳስ 2023
- ብርቱካን ሚደቅሳ ከምርጫ ቦርድ ኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው እንደሚለቁ አሳወቁ26 ሰኔ 2023
- የኢትዮጵያን ምርጫ የሚመሩት የቀድሞዋ የፖለቲካ እስረኛ ማን ናቸው?20 ሰኔ 2021
ኮሚቴው ለአስር ቀናት ዕጩዎችን ሲቀበል የቆየ ሲሆን፣ በእነዚህ ቀናት የ56 ዕጩዎች ጥቆማዎች ቀርበውለት ከመካከላቸው አራቱ ብቻ ነበሩ ሴቶች።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ የሚመሩት ዕጩ መልማይ ኮሚቴ በሦስት ዙሮች አምስት ዕጩዎችን ለይቶ ነበር። ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴው በመጨረሻ ሁለት ዕጩዎችን ለይቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል።
ለቦርዱ ሰብሳቢ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱም ግለሰቦች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነት አዲስ አይደሉም። ሁለቱም ዕጩዎች ቦርዱን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።
ወይዘሮ ሜላትወርቅ ለሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሠርተዋል። አቶ ታደሰ በበኩላቸው የምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።
ለቦርዱ አዲስ ሰብሳቢ የሚሾምለት ቦርዱን ለአራት ዓመት ከመንፈቅ የመሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጤናቸውን “በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት” እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ከኃላፊነት በመልቀቃቸው ነው።
ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በመሾም አራተኛው ግለሰብ ናቸወ። ነገ ሹመታቸው የሚጸድቅላቸው ተሿሚ አምስተኛው/ዋ የቦርዱ ሰብሳቢ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን መጽደቅ ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት አቶ ከማል በድሪ ናቸው። አቶ ከማል ቦርዱን ለአስራ አንድ ዓመታት አገልግለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩት መርጋ በቃና በ1999 ዓ.ም. አቶ ከማል በድሪን ተከትው በቦርዱ ሰብሳቢነት ተሹመዋል።
ፕ/ር መርጋ ከአስር ዓመታት የቦርዱ ሰብሳቢነት በኋላ በ2009 ዓ.ም ሥልጣናቸውን ለመጀመሪያዋ የቦርዱ ሴት ሰብሳቢ ሳሚያ ዘካሪያ አስርክበዋል።
የሳሚያ ዘካሪያ የሥልጣን ዘመን ከአንድ ዓመት የዘለቀ አልነበረም። በ2011 ዓ.ም. የቀድሞዋ ፖለቲከኛ ብርቱካን ሚደቅሳ መንበሩን ከሳሚያ ዘካሪያ ተረክበዋል።
በአራት ዓመት ከመንፈቅ የብርቱካን ሚደቅሳ የሥልጣን ቆይታ ቦርዱ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን አካሂዷል።