
ከ 8 ሰአት በፊት
ከሩስያ ጋር ጦርነት ላይ ያለችው ዩክሬን ከሌሎች ሀገራት የሚደረግላት ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት የተወሰኑ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለመቀነስ እየተገደደች መሆኑን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ወታደሮች “በሁሉም የውጊያ ግንባር” የተተኳሽ ጥይት እጥረት ስላጋጠማቸው “ትልቅ ችግር” እየተፈጠረ መሆኑን የዩክሬን ከፍተኛ ጄነራል የሆኑት ኦሌክሳንደር ተርናቭስኪ ተናግረዋል።
ዩክሬን ይህ ችግር ያጋጠማት ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ህብረት በድጋፍ ልታገኝ የነበረው የቢሊዮኖች ዶላር ድጋፍ በፖለቲካዊ አለመግባባት ምክንያት ተይዞ በመቆየቱ ነው።
ዩክሬን በምዕራባውያን ሀገራት እርዳታ የራሷን ጥይት በማምረት ክምችቷን ከፍ ለማድረግ እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።
ነገር ግን ከሩስያ ጋር የምታደርገው ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ የተመሰረተው ከምዕራባውያኑ ሀገራት በሚቀርብላት የጦር መሳሪያዎች ላይ ነው።
በተለይም የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች እና የአየር መከላከያ ስርዓት አቅርቦት የምታገኘው ከእነዚሁ ሀገራት ነው።
ዩክሬን በተለይም በሶቪየት ህብረት ጊዜ አንስቶ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ላሉት ከባድ የጦር መሳሪያዎች የሚሆን ተተኳሽ እጥረት መኖሩን ጄነራል ተርናቭስኪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
“ካለን ፍላጎት አንጻር ያለን የተተኳሽ ብዛት በቂ አይደለም” ያሉት ጄነራሉ፤ “በዚህም የተነሳ ያሉንን መልሰን እያከፋፈልን ነው። ልንተገብር ላሰብናቸው ተግባራት [ጥይት] ማቅረብ ስላለብን ያስቀመጥናቸውን እቅዶች መልሰን እየከለስን እና መጠናቸው እንዲቀንስ እያደረግ ነው” ሲሉ ያጋጠመውን ችግር ገልጸዋል።
የውጭ ሀገራት የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ መቀነሱ በውጊያ ሜዳ ላይ ተጽእኖ እያደረሰ መሆኑን እና የውጊያ ስልት ለውጥ እንዲደረግ እያስገደደ መሆኑንም ጄነራሉ አክለዋል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የሚያደርጉት ድጋፍ ላይ እቀባ አድርገዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሪፐብሊካን ለዩክሬን ሊሰጥ ታስቦ የነበረን የ60 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አግደዋል።
- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 50 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በማስተማር ዕቅውና የተሰጣቸው ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማከ 9 ሰአት በፊት
- የግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ለሶስተኛ ጊዜ አሸነፉከ 8 ሰአት በፊት
- ግዙፉ ነዳጅ አምራች ኩባንያ በቀይ ባሕር በኩል ነዳጅ ማመላለስ አቋረጠ18 ታህሳስ 2023
ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ለሀገሪቱ ሊሰጥ የነበረውን 55 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ሀንጋሪ እንዲታገድ አድርጋዋለች። ይሁንና የህብረቱ አመራሮች ዩክሬን ያለ ምንም ድጋፍ እንደማትቀር ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት እስከ መጪው መጋቢት ወር ድረስ አንድ ሚሊዮን ተተኳሽ ጥይት ለማቅረብ ቃል ቢገባም እስካሁን ማቅረብ የቻለው 480 ሺህ ያህሉን ብቻ ሲሆን ከዚህ ውስጥም የተወሰነው በሂደት ላይ ነው።
አሜሪካ ሁለት ሚሊዮን ባለ 55 ሚሊ ሜትር ጥይት ለዩክሬን ማቅረብ ብትችልም አሁን ላይ የምታቀርበው የተተኳሽ አይነት ላይ ለውጥ አድርጋለች።
ዩክሬን ያላት የተተኳሽ ፍላጎት አጋሮቿ የሆኑ ሀገራት ማቅረብ ከሚችሉት አቅም በላይ ነው። እንደ ኢስቶኒያ መከላከያ ሚኒስቴር ገለጻ ዩክሬን በሩስያ ላይ የበላይነቱን ለመቀናጀት በየወሩ ቢያንስ 200 ሺህ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾች ያስፈልጓታል።
ሩስያ፤ ዩክሬን ያጋጠማትን የወታደራዊ ድጋፍ እጥረት እንደ ጥሩ እድል በመውሰድ ምጣኔ ኃብቷን ወደ ጦርነቱ በማዞር በተራዘመ ጦርነት ለማሸነፍ ልትሰራ ትችላልች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ባለፈው ሳምንት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲክ ጦርነቱ የሚጠናቀቀው ሩስያ “ግቧን ስታሳካ ነው” ብለው ነበር።