የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ

ከ 8 ሰአት በፊት

የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ 89.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፋቸውን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

አል ሲሲ በሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸውም ለቀጣዩ ስድስት ዓመታት አገሪቷን የሚመሩ ይሆናል።

የቀድሞው የጦር አዛዥ አል ሲሲ ብዙም ዕውቅና የሌላቸውን ሶስት የፕሬዚዳንት ዕጩዎቻቸውን በሰፊ ድምጽ ማሸነፋቸው ተነግሯል።

በዚህ ምርጫ አል ሲሲን በሁለተኛነት የተከተሉት ዕጩ ያገኙት ድምጽ 4.5 በመቶ ብቻ ነው።

የተቃዋሚው መሪ አህመድዘ ታንታውይ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ዛቻ እንዲሁም በቡድናቸው ላይ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል በሚልም ከወራት በፊት ከምርጫው ራሳቸውን አግልለው ነበር።

የግብፅ የምጣኔ ኃብት ማሽቆልቆል እንዲሁም የጋዛ ጦርነት የምርጫው ቁልፍ ጉዳዮች ነበሩ።

የ69 አመቱ ሲሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣንን የተቆናጠጡት በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን ከአመት በፊትም የአገሪቱን ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲን ከስልጣን ያወገደው መፈንቅለ መንግሥትንም መርተዋል።

ፕሬዚዳንት ሲሲ በቀጣዩ በተደረገው 2018 ምርጫም በድጋሜ ማሸነፍ ችለዋል። አሁን በተደረገው ምርጫ ያሸነፉት አል ሲሲ አገሪቱን እስከ አውሮፖውያኑ 2030 ድረስ የሚመሩ ይሆናል።

በእርሳቸው የስልጣን ዘመን አገሪቷ ለትላልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሳለች።

ሰፋፊ መንገዶች ተዘርግተዋል፣ ረጃጅም ድልድዮች ተገንብተዋል እንዲሁም በካይሮ አቅራቢያ ቢሊዮኖች ዶላር የፈጀ አዲስ መዲናም ተቋቁሟል።

ይህም የአገሪቱን አብዛኛውን ኃብት በማሟጠጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ እዳ በመዝፈቅ ምጣኔ ኃብቷን አሽመድምዶታል በማለትም ይተቿቸዋል።

በዋጋ ግሽበት እየተፈተነች ያለችው ግብጽ የመገበያያ ገንዘቧ ፓውንድም እያሽቆለቆለ ይገኛል።

የግብፅ ምጣኔ ኃብት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ሲሆን መሰረታዊ የሸቀጥ ፍጆታዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ንሯል እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያም ተስፋፍቷል።

ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከግብጽ 100 ሚሊዮን ህዝብ 30 በመቶው የሚጠጋው ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር ነው። ከምጣኔ ኃብት ተግዳሮት በተጫማሪ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር የጠበበ ነው ሲሉ ይተቻሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አገሪቷ የጣለቻቸው ጥብቅ የጸጥታ ገደቦች የመብት ጥሰቶችን ለመመዝገብ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላሉ። የግብጹ ባለስልጣናት ክሱን ያስተባብላሉ።